ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን ሩምቤክ ሀገረ ስብከት ያደረጉት ጉብኝት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን ሩምቤክ ሀገረ ስብከት ያደረጉት ጉብኝት 

ካርዲናል ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን ፍርሃትን በፍቅር በማሸነፍ ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል ገለጹ

በደቡብ ሱዳን የአራት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ፍርሃትን በፍቅር በማሸነፍ ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል ገልጸው፥ ሁሉም ሰው ለሀገር ጥቅም ሲባል በሰላም እና በእርቅ ጎዳና እንዲጓዝ ጋብዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን በሚያደርጉት ጉብኝት ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 11/2015 ዓ. ም. ወደ ሩምቤክ ከተማ ገብተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስቀድመው ቤተ ክርስቲያን በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ለተሰደዱት እና ለተፈናቀሉት ሰዎች ያላትን ቅርበት ለመግለጽ በደቡብ ሱዳን ሰሜናዊት ከተማ በሆነች ማላካል ውስጥ የሁለት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሩምቤክ ሀገረ ስብከት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሩምቤክ ሀገረ ስብከት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት

የጸሎት እና የአንድነት ጊዜ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ዛሬ ሐሙስ ወደ ሩምቤክ ሲደርሱ ባደረጉት ንግግር፥ ከአንድ ዓመት ጥቂት በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ ደቡብ ሱዳንን ለሦስተኛ ጊዜ በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ብጹዕነታቸው ደቡብ ሱዳንን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኟት እንደ ጎርጎርሳውያኑ በሐምሌ 2022 ዓ. ም. እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን ሊያደርጉት ያቀዱትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በጤና ምክንያት ለማራዘም ከተገደዱ በኋላ እንደሆነ ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በኋላም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው በደቡብ ሱዳን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከየካቲት 3-5/2023 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ብፁዕ ካርዲናል ሐሙስ ጠዋት በሩምቤክ በተደረገላቸው የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥያቄ መሠረት በደቡብ ሱዳን ለሦስተኛ ጊዜ የሚያደርጉት ጉብኝት የሰላም ሂደቱን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። ብጹዕነታቸው በማከልም የሩምቤክ ጉብኝታቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ በሚከናወነው የእምነት፣ የጸሎት እና የአንድነት ጊዜ ለመካፈል ዕድል እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል።

በፍፁም ፍቅር የሚወገድ ፍርሃት

በሩምቤክ ለሰላም እና ለእርቅ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን ያቀረቡት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ንባብ ላይ በማሰላሰል ባቀረቡት ስብከት፥ ከትንሣኤው በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍርሃት ውስጥ ወደነበሩ ደቀ መዛሙርት ዘንድ እንደመጣ አስታውሰው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍርሃት ውስጥ የሚገኙ ደቀ መዛሙርትን እንዳረጋጋላቸው ሁሉ፥ ወደ እኛም በመምጣት በእርሱ እንድንታመን ይጋብዘናል” ብለዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን ስብከታቸውን በመቀጠል፥ እግዚአብሔር ለሕይወታችን ባለው ዕቅድ ላይ ከመታመን ይልቅ ብዙውን ጊዜ በራሳችን ጥንካሬ ወይም ዓለማዊ ኃይል ለመታመን እንፈልጋለን ብለው፥ “ፍርሃት ሰዎችን ደካማ እና ሌሎችን እንዳያምኑ በማድረግ  ወንድማማችነትን መገንባት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል” ብለዋል። ሆኖም ግን “ፍርሃት በፍጹም ፍቅር ይወገዳል” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ አክለውም “ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር በመታመን ለእውነት እና ለፍትሕ በመሥራት ፍርሃታቸውን ወደ ጎን መተው ይችላሉ” ብለዋል።

የልባችንን ትጥቅ ማስፈታት

እንደ ክርስቲያኖች እርስ በርስ በመተጋገዝ እና ቅዱስ ወንጌልን በማገልገል ግዴታ ላይ ያስተነተኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የማስታረቅ ኃላፊነትን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠ በመሆኑ፥ ይህ ተግባር የክርስቲያናዊ ተልዕኳችን አስፈላጊ አካል ስለሆነ ሁሉም ሰው ለእርቅ እንዲሠራ” በማለት አሳስበዋል። “የልባችንን ትጥቅ ፈትተን ልዩነቶቻችንን ወደ ጎን የማናደርግ ከሆነ ራሳችንን እናጠፋለን” ብለው፥ “ሰላም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ዓይነት ልዩነት እና መከፋፈል ለማሸነፍ ብቸኛው መንገድ ነው” በማለት አስረድተዋል። አክለውም ደቡብ ሱዳን ከሁሉም ልዩነቶች ባሻገር፥ የኅብረተሰቧ መከፋፈል የሚፈውስበትን መንገድ መፈለግ አለባት ብለዋል።

ቅዱስ ቁርባን የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው እንደሚገኝ ተገንዝቦ የሰላምን መንገድ እንዲቀበል ጥሪ አቅርበው፥ ፍትህን እና ሰላምን በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት እግዚአብሔር የሚናገረውን ማድመጥ እንደሚገባ አሳስበው፥ "ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠን የሰላም መልዕክት ነው" ብለዋል።

የሰላም ሂደቱን እንደገና መጀመር

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ለመንግሥት መሪዎች የተናገሩትን መልዕክት በመድገም፥ “ከቃላት ወጥተን ወደ ተግባር የምንሸጋገርበት ጊዜ አሁን ነው" በማለት፥ አስቸኳይ እና አስፈላጊ ለውጥ ለማድረግ ቁርጠኝነትን የሚገልጹበት ጊዜ እንደሆነ በመናገር፥ “የሰላም እና የዕርቅ ሂደት ዘወትር አዲስ ጅምር ይጠይቃል” ብለዋል።

 

17 August 2023, 17:13