ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሱዳናውያን ስደተኞችን ወደ ማላካል በሚያጓጉዘው ጀልባ ላይ ሆነው። ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሱዳናውያን ስደተኞችን ወደ ማላካል በሚያጓጉዘው ጀልባ ላይ ሆነው። 

የማላካሉ ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የደቡብ ሱዳን ጉብኝት ተስፋን ይሰጣል አሉ።

ጳጳስ እስጢፋኖስ ንዮዶ አዶር ማይዎክ የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከሱዳኑ የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽተው የተሰደዱ ስደተኞችን ባነጋገሩበት ሀገረ ስብከት ሲደርሱ ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ በማለት አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጳጳሱ ‘ምንም የቀረ ነገር በሌላቸው" በብዙ ስደተኞች ስም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን ማላካል ከተማ ያደረጉት ጉብኝት “በእውነቱ ከሆነ ለእኛ እጅግ ጠቃሚ ነው” ያሉት የማላካል ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ኒዮዶ አዶር ማይዎክ ናቸው።
ጳጳሱ ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የብፁዕ ካርዲናል ጉብኝት ተስፋን የሚሰጥ እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሥቃይ ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ያላትን ፍቅር፣ ቅርበት እና አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል።
የብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ጉብኝት የሃገሬው ህዝብ በተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል ተቀናጅቶ በመስራት ወደ ፊት ለመራመድ ፥ አገራቸውን፣ ከተማቸውን እና ሀገረ ስብከታቸውን ለመገንባት ትልቅ ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው እንዲረዱ ያግዛል ብለዋል።
ጳጳስ ንዮዶሆ የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከማክሰኞ ዕለት ጀምረው በክልላቸው ባደረጉት ጉብኝት እርሳቸውና መላው ሀገረ ስብከቱ ስላደረባቸው ትልቅ ተስፋ ተናግረዋል።
ካርዲናሉ እሮብ ጧት በሱዳን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ሸሽተው በጀልባ ተሳፍረው የመጡትን ስደተኞች ተቀብለው እስከ ማቆያ ማእከሉ ድረስ አጅበው ሄደዋል። ከዛ ቀደም ብለው ማክሰኞ ዕለት በማላካል ካቴድራል ውስጥ መስዋዕተ ቅዳሴን ካሳረጉ በኋላ በመቀበያ ማዕከሉ ውስጥ ከስደተኞች ጋር ተገናኝተው ነበር።

ጦርነትን መሸሽ

ከ42,000 በላይ ስደተኞች በደቡብ ሱዳን ሰሜናዊ ምስራቅ በምትገኝ ማላካል ከተማ የገቡ ሲሆን ፥ የጳጳስ ኒዮዶ ሀገረ ስብከት የላይኛው ናይልን፣ ጆንግሌይን እና ወደ 35,000 የሚጠጉ በተለይም የቤተሰብ አባላት ያሏቸው ስደተኞች ያሉባቸው ዩኒቲ ስቴቶችን ያጠቃልላል። አብዛኞቹ ስደተኞች ባለፉት ዓመታት ውስጥ ወደ ካርቱም የሄዱ እና አሁን ሸሽተው የመጡ ደቡብ ሱዳናውያን ናቸው። በድምሩ አንድ ሚሊዮን ተኩል የሚሆኑ ደቡብ ሱዳናውያን ሱዳን እንደሚገኙ ፥ ነገርግን በርካቶች አሁን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ለማምለጥ ወደ ደቡብ ሱዳን እየተመለሱ እንደሆነና ፥ በዚህም የተነሳ ወደ 200,000 የሚገመቱ ሰዎች ወደ ደቡብ ሱዳን እንደተመለሱ ለማወቅ ተችሏል። እነዚህ ስደተኞች ወደዚህ ሥፍራ ሲደርሱ ሁል ጊዜ ማለት ይቻላል የዘራፊዎች ሰለባ ይሆናሉ ተብሏል።
በርካቶቹ ስደተኞች የደቡብ ሱዳን ድንበር ከደረሱ በኋላ ወደ ማላካል የሚጓዙት በሀገረ ስብከቱ የእህል ማመላለሻ የእቃ መጫኛ ጀልባ ነው። ከሁለት እስከ ሶስት ቀናት በሚቆይ ጉዞ ከ400 እስከ 800 የሚደርሱ ስደተኞች በጀልባ ይጓዛሉ። ካርዲናል ፓሮሊን ረቡዕ ዕለት ከነዚያ ጀልባዎች በአንዱ ተሳፍረው ነው ስድተኞቹን የተቀበሉት። እስከ አሁን ድረስም ሦስት ሺህ ሰዎች በዚህ ሥርዓት ተጓጉዘዋል።

የሰላም እና የእርቅ ፍላጎት

ጳጳስ ኒዮዶ አዶር ማይዎክ ለቫቲካን ዜና እንደተናገሩት ፥ ሀገረ ስብከቱ በተፈጥሮ አደጋዎች በጣም ከተጎዱት እና በጦርነትም ከወደሙት አከባቢዎች ውስጥ አንዱ እንደሆነና ፥ አሁን ደግሞ ሀገረ ስብከቱ በሱዳን ያለውን ጦርነት ሸሽተው የሚመጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እያስተናገደ ሲሆን ይህም ትልቅ ፈተና ሆኖበታል ብለዋል።
ከሱዳን ድንበር ወደ ማላካል የሚጓዙ ስደተኞችን ለማድረስ እንደ ድልድይ በመስራት የማላካል ሀገረ ስብከት ቀዳሚ እርዳታ ካደረጉት መካከል አንዱ ሆኖ እንዴት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚሁ ዓመት ጥር ወር ውስጥ ወደ ደቡብ ሱዳን በመጡበት ወቅት እንደተናገሩት “እዚህ ያሉት ሰዎች ሰላምና እርቅ እንዲሁም አንድነት ያስፈልጋቸዋል” ብለው ነበር።
ጳጳስ ኒዮድሆ እንደገለፁት የብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ጉብኝት ለሁሉም ሰው በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸው ፥ ምንም እንኳን ነገሩ ቀላል ባይሆንምና እነዚህ ሰዎች በግጭቶቹ ወቅት እርስ በርስ ሲዋጉ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ ቢታወቅም አንድነትን ለማምጣት እና ወደፊት ለመራመድ እንድንችል ጥንካሬ እንዲኖረን ያደርጋል በማለት አብራርተዋል። እነሱን ለማሰባሰብ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድም አክለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጉብኝት ትልቅ ጥንካሬ እና በአባይ ህዝቦች መካከል እርቅ እንዲፈጠር ተስፋ የሰጠ ሲሆን ይህም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውሰዋል።

ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተደረገ ጥሪ

ጳጳስ ኒዮድሆ አዶር ማይዎክ "እዚህ እኛ ዘንድ ምንም የቀረ ነገር የለም ፥ ለስደተኞቹ የሚሆን ብዙ ነገር ዬለንም ፥ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ወደዚህ የሚደርሱትን ሰዎች እንዴት መርዳት ትችላላችሁ?" በማለት ወቀሳ እና ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ጳጳሱ ጦርነት ከውድመቱና ከዝርፊያው ጋር ተዳምሮ ምን እንዳመጣ እና ለመሰደድ የሚሞክሩትን ስደተኞችን ትግል አብራርተዋል። ሰዎችን ከድንበር ወደ ማላካል ለማድረስ በአንድ ጉዞ ለነዳጅ ብቻ ከሰባት እስከ ስምንት ሺህ ዶላር የሚፈጅ ሲሆን ፥ ከዚያ በኋላ ምግብ እና መጠለያ ሊያገኙ ይገባል ፥ ከዚህም አልፎ አሁን ደግሞ በሽታ እየተከሰተ ነው ብለዋል።
ጳጳሱ "ዝም ብለን መቀመጥ አንችልም ፥ ለዚህም ነው እንደአቅማችን የምንችለውን ለማድረግ ወደ ፊት ለመራመድ እየሞከርን ያለነው" በማለት ፥ በማከልም “ሰዎች ከዝናብ ራሳቸውን የሚከላከሉበት ምንም ነገር እንደሌላቸው እና ህጻናትና አረጋውያን ብዙ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው” በመጠቆም ፥ በዚያ ላይ አሁን የዝናብ ወቅት ስለሆነ ምን ያህል ስቃዩን እያወሳሰበ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ጳጳስ ኒዮዶ በማጠቃለያቸው ፥ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ለበጎ አድራጊ አጋሮቻቸው እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ምክንያቱም ደግም ይላሉ “እዚህ ያለው ሁኔታ በእውነቱ በጎ ፈቃድ ያላቸውን ሰዎች ይፈልጋል፣ ሰብአዊነትንም ይጠይቃል” በማለት ህዝቡ ከዚህ መከራ እንዲተርፍ እና ህይወታቸውን እንደገና እንዲገነቡ አስፈላጊው እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
 

17 August 2023, 15:40