ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሰላምታ ሲያቀርቡ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሰላምታ ሲያቀርቡ  

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በትህትና ማገልገል ‘የበቀል ስሜትን ማሸነፍ ይችላል' አሉ

የቫቲካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን ማላካል ከተማ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት እንደተናገሩት ሁሉም ሰው የበቀል ሃሳቦችን ወደ ጎን በመተው ሰላምን ወክሎ የትህትና አገልግሎትን እንዲቀበል አሳስበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን እያደረጉት ባለው ጉብኝታቸው ማክሰኞ ዕለት ሁለተኛ ቀናቸው ሲሆን ፥ ወደ ሰሜን ወደምትገኘው የላይኛው ናይል ግዛት ማላካል ከተማ ተጉዘው በቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል መስዋዕተ ቅዳሴን አሳርገዋል።
የቫቲካን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ካርዲናሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የሃገሪቱ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ለበርካታ ዓመታት ሲያደርጉት የነበረውን የሰላም ሂደት ለማበረታታት በሚል ባለፈው ነሃሴ 8/ 2015 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት በአፍሪካ ሀገር የ4 ቀናት ጉብኝታቸውን መጀመራቸው ይታወቃል።

የር ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ እና የሁለንተናዊት ቤተክርስቲያን ቅርበት

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በቅድስት ድንግል ማርያም ክብረ በዓል ላይ ባደረጉት ስብከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ለደቡብ ሱዳን ህዝብ የላኩትን የሰላምታ መልዕክት እና ያላቸውን ቅርርብ አጋርተዋል።
“ቅዱስ አባታችን በዚህ ዓመት ጥር ወር ውስጥ ወደ ደቡብ ሱዳን ያደረጉትን ሃዋሪያዊ ጉብኝታቸውን አሁንም ድረስ በግልጽ ያስታውሱታል” ያሉት ካርዲናሉ ፥ “ይህችን ውብ አገር፣ ሕዝቦቿን፣ ችግሮቿና ቁስሎቿን በልባቸው ውስጥ ተሸክመዋል ፥ በዛውም ልክ ሃገሪቷ ወደፊት የሚጠብቃትን ሠላም እና ተስፋም ያስባሉ” በማለት ተናግረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ወደ አገሪቱ ያደረጉት ጉብኝት ደቡብ ሱዳን ‘ከዓለም አቀፉን ቤተክርስቲያን ጋር ያላትን ኅብረት እና አንድነት’ ላማሳየት እንዲሁም ደቡብ ሱዳናውያን ሁላችንም በክርስቶስ አንድ ስለሆንን ማንም ክርስቲያን ብቻውን እንዳልሆነ ለማሳሰብ ነው ብለዋል።
“አንዱ አካል ፈተና ቢደርስበት እሱ ወይም እሷ ከሌሎቹ የበለጠ ትኩረት፣ እንክብካቤ፣ ፍቅር የማግኘት መብት አላቸው” ብለዋል። በማከልም "ዛሬ ጠዋት የመላው ቤተክርስትያን ትኩረት፣ እንክብካቤ እና ፍቅር እንዲሰማችሁ እፈልጋለሁ!" በማለት አረጋግጠውላቸዋል።

‘የበቀል ስሜትን በእምነት፣ በተስፋ፣ በበጎ አድራጎት ማሸነፍ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የደቡብ ሱዳንን የርስ በርስ ጦርነትን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጦርነቶች በሰዎች ላይ በሚያደረሱት በርካታ ችግሮች ማዘናቸውን ተናግረዋል።
ብጹዕ ካርዲናሉ በግጭት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተሰደዱትን በርካታ ሰዎች አስታውሰው ፥ “ማኅበረሰቦቻችሁን እያጠፋችሁ ነው” ፥ በዚህም የተነሳ “ትልቅ የበቀል መቅሰፍትን እየዘራችሁ ነው” በማለት የግጭት መንስኤ የሆኑትን ባለድርሻ አካላትን አሳስበዋል።
ይሁን እንጂ ይላሉ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በማከልም ፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከቶች ክርስቲያኖችን የሚያሳስበው ነገር ቢኖር ክፋት ፈጽሞ የመጨረሻ ቃል እንደሌለው እና ሌሎችን የሚያዋርዱ ሰዎች ኩራታቸው፣ መሣሪያቸውና ገንዘባቸው አያድናቸውም” በማለት አሳስበዋቸዋል።
በተለይ ክርስቲያኖች ተስፋችንን ከእምነት ጋር በማዋሃድ ሰላምን ወክሎ ከሚደረግ የትህትና አገልግሎት ጋር በተያያዘ በእግዚአብሔር ላይ ያለን ተስፋ ፈጽሞ የማያሳፍር መሆኑን እንዲያስታውሱ እና የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ወደ ክርስቶስ እና ወደ እናቱ እንዲመለከቱ አበረታቷቸዋል።
“እምነት፣ ልግስና፣ ትህትና/ዝቅ ማለት” ይላሉ ካርዲናሉ ፥ “የወንጌል መንገዶች ናቸው ፤ ማርያም የተራመደችበት መንገድ እና ወደ ውብ ስፍራ የመራት እና እንደ ንግስት በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ ለዓለም ሁሉ የመጽናናት እና የተስፋ ምልክት ይሁኑ ዘንድ ያስቀመጣት ነው” ብለዋል።

በተፈናቃዮች መካከል የሚፈጠር የእርስ በርስ ግጭት

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ካርዲናል ፓሮሊን ከሱዳን የሚመለሱ ስደተኞች የሚቆዩበትን ማዕከል ጎብኝተዋል። የማላካል ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ሰዎችን ለህልፈትና ለከፍተኛ የንብረት ውድመት ያደረሱ የእርስ በርስ ግጭቶችን አስተናግዳለች። ባለፈው ሳምንት በአንድ ካምፕ በተፈጠረ ግጭት በትንሹ 13 ሰዎች ሲሞቱ ከ20 በላይ ቆስለዋል።
ክስተቱ የተከሰተው በደቡብ ሱዳን የመንግስታቱ ድርጅት የሠላም ማስከበር ተልእኮ በሆነው ተቋም በሚመራው የተባበሩት መንግስታት የሲቪሎች ጥበቃ ጣቢያ (PoC) ውስጥ ነው ነው። በዚህም ጣብያ ውስጥ ከ37,000 በላይ የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች በማላካል ካምፕ ከታህሳስ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እየኖሩ ይገኛሉ።

ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር መገናኘት

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሰኞ ዕለት በዋና ከተማዋ ጁባ ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር እንዲሁም የካርቱም ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ገብርኤል ዙበይር ዋኮ እና የጁባ ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ አሜዩ ማርቲን ሙላ ጋር ተገናኝተዋል።
የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ‘የቅዱስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን የወዳጅነት የሠላምታ መልዕክትን’ አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ እና ካርዲናሉ በሚቀጥለው ዓመት ሊደርግ በታቀዱት አጠቃላይ ምርጫዎች የተመለከቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊንም በአገሪቱ ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ ማኅበረሰብ ለመገንባት የደቡብ ሱዳን ሕዝብ የሰላምና የእርቅ መንፈስን እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል።

በጁባ ካቴድራል የዛፍ ተከላ ሥነ ሥርዓት

ብፁዕ ካርዲናሉ የደቡብ ሱዳናውያን ሕዝቦች በአገራቸው ሰላም እንዲሰፍን ያላቸውን ፍላጎት ለማመላከት ባለፈው ሰኞ በጁባ በሚገኘው የቅድስት ቴሬዛ ካቴድራል ሰበካ የችግኝ ተከላ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተሳትፈዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት አጭር ንግግር ፥ በደቡብ ሱዳን ለሦስተኛ ጊዜ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት በአካባቢው ማህበረሰብ ስለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋቸዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቀደም ብለው ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ በደረሰባቸው የጤና ዕክል ምክንያት ሐዋርያዊ ጉዟቸውን ለሌላ ጊዜ ካስተላለፉ በኋላ ሃምሌ 2014 ዓ.ም. ወደ አገሪቱ መጥተው እንደነበር ተናግረዋል። ካርዲናሉ ር.ሊ.ጳ. ፍራንቺስኮስ በጥር 26-28 2015 ዓ.ም. ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዟቸው ከብጹዕነታቸው ጋር አንድ ላይ ሆነው ድጋሚ ወደ ደቡብ ሱዳን መጥተው እንደነበርም ይታወቃል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ደቡብ ሱዳናውያን ‘ለዚች ውብ ሃገር ሰላምና እርቅ’ እንዲመጣ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።
በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስም ለሊቀ ጳጳስ አሜዩ እና ለመላው የቅድስት ቴሬዛ ካቴድራል ሰበካ ምእመናን ሰላምታ አቅርበው ፥ ወጣቶች የደቡብ ሱዳን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንደሆኑ እና ማንነታቸውንም አምነው እንዲቀበሉ አበረታተዋል።
ካርዲናል ፓሮሊን ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፥ የዛፍ ተከላ ሥነ ሥርዓቱ ሰዎች ፍጥረትን እንዲንከባከቡ ተምሳሌታዊ ጥሪ ይሆናል ብለዋል።
በተለይ ወጣቶች “የዚህች አገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ የዓለም የወደፊት ዕጣ በመሆናቸው ይህንን የጋራ ቤት ለመጠበቅ ከፍተኛ ቁርጠኝነት ሊሰማቸው ስለሚገባ የጋራ ቤታችንን እንድንንከባከብ ተጠርተናል” ብለዋል።
 

16 August 2023, 18:27