ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን አቀባበል ሲደረግላቸው ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን አቀባበል ሲደረግላቸው 

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የሠላም ሂደቱን ለማበረታታት ደቡብ ሱዳን ገቡ

የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን ለ4 ቀናት የሚቆይ ጉብኝት ጀምረዋል። የካርዲናሉ ጉብኝት ዋና ዓላማ ቤተክርስቲያኒቷ በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋ ለተመታችው የማላካል ክልል አጋርነቷን ለማሳየት እና ሀገሪቱ ለሰላም የምታደርገውን ጥረት ለማበረታታትም ጭምር ነው ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የቫቲካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከነሐሴ 8-11 2015 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን ጉብኝት ለማድረግ ሰኞ ማለዳ ጁባ ገብተዋል። ካርዲናሉ ጁባ ከመግባታቸው በፊት ጥቂት ቀናትን በአንጎላ ቆይታ ያደረጉ ሲሆን ፥ እዚያም የሊቀ ጳጳስ ፔነሞቴን የጵጵስና ሹመት ሥነ ስርዓትን መርተዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ሰኞ ዕለትን ጁባ ያሳለፉ ሲሆን ፣ ለሁለት ቀናት ደግሞ በማላካል ሀገረ ስብከት ቆይታ አድርገው ከዚያም ሐሙስ ዕለት በሌላኛዋ የደቡብ ሱዳን ከተማ በሩምቤክ የጉብኝታቸው ማጠቃለያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጁባ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት እስጢፋኖስ አሜዩ ማርቲን ሙላ የጁባ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የካቶሊክ ሬድዮ ጣቢያ ከሆነው 'ራዲዮ ባሂታ' ጋር ያደረጉትን ቆይታ እና ጣብያው በፌስ ቡክ ገጹ ባስተላለፈው ቃለ ምልልስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ደቡብ ሱዳንን የሚጎበኙበትን ዓላማ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከማላካል ሀገረ ስብከት ጋር አንድነትን ማጠናከር

ሊቀ ጳጳስ አሜዩ እንደተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ቆይታ ዋና ዓላማ የማላካል ጳጳስ የሆኑት አቡነ እስጢፋኖስ ኒዮዶዶ አዶር ማጅዎክ ለካርዲናሉ እዚያ ያለውን ሁኔታ በራሳቸው ለማየት እንዲችሉ ስለጋበዟቸው የማላካል ሀገረ ስብከትን መጎብኘት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳሱ "በማላካል ያለውን ሁኔታ ሁላችንም እናውቃለን ፥ የተፈጥሮ አደጋዎች ፣ የጎርፍ ማጥለቅለቅ እና ሌሎች ብዙ ነገሮች ከሰው ሰራሽ አደጋዎች ጋር ተዳምረው እንደጎዷት እናውቃለን ፥ ነገር ግን አሁን የሰላም እድል መስኮት ተከፍቷል” ብለዋል።
ሊቀ ጳጳስ አሜዩ አክለውም እንደተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ላሉ ቤተ ክርስቲያናት እና የፖለቲካ መሪዎች በአደራ የሰጡትን የሠላም ሂደቶች እየተከታተሉ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ብቻቸውን በመሆን ለሁለተኛ ጊዜ በአፍሪካ ሀገር ያደረጉት ጉብኝት መሆኑን ገልጸው ፥ ይህም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ያላቸውን ፍቅር መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል።

"ለሰላም በጋራ እንስራ"

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የካቲት ወር 2015 ዓ.ም. በቤተክርስቲያን በኩል በተቀናቃኞቹ መካከል ሰላም እንዲወርድ ሰፊ ጥረት ካደረጉ በኋላ አገሪቱን ጎብኝተው እንደነበር ይታወሳል።
የጁባ ሊቀ ጳጳስ አሜዩ የደቡብ ሱዳን መንግስት እና ህዝብ በጋራ እንዲሰሩ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያቀረቡትን ጥሪ በማስታወስ ፥ ብጹዕነታቸው “አንድ ላይ ፥ በአንድነት ፥ በአንድነት" የሚሉትን ቃላት ሶስት ጊዜ ደጋግመውታል ፥ ምክንያቱም አንድነት ማለት ህብረት ማለት ነው ፥ በአንድነት ሆነን በመካከላችን ሰላምን ማግኘት እንችላለን" ብለዋል።
እየተካሄደ ያለውን የሰላም ሂደት በተመለከተ ሊቀ ጳጳስ አሜዩ እንዳሉት ሁሉም ሰው በሰላሙ ስምምነት ፕሮቶኮሎች እንዲጸኑ እና ፖለቲከኞች በሀገሪቱ የህብረተሰብ መዋቅር ውስጥ ሰላም እንዲፈጥሩ ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ ለማበረታታት ትፈልጋለች በማለት አሳስበዋል።
"በህዝቦቻችን መካከል ሰላምና እርቅን እውን ለማድረግ ብዙ ሚናዎችን መጫወት እንደሚገባን ህዝቡን እናሳውቃለን" ያሉት ጳጳሱ  “እንደ ምጽአት ቀን ነቢያት አንጮህም ፥ ጸጥ ባለ ዲፕሎማሲ ውስጥ መሳተፍ እንፈልጋለን” በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል።
ሊቀ ጳጳስ አሜዩ አጠቃላይ የሃገሪቷ ምርጫ እ.አ.አ. 2024 ከማለቁ በፊት እንደሚካሄድ ተናግረው ፥ ምርጫው “የታደሰው የሰላም ስምምነት አንዱ አካል ነው” ብለዋል።
"ምርጫ በእውነትም ጠንካራ ግፊት እንደሚሰጠን አውቃለሁ ፥ መሪዎች በህዝብ እና ለህዝብ ሲመረጡ ጠንካራ አቋም ይኖረናል" ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

የካርዲናል ፓሮሊን ጉብኝት ፕሮግራም

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን የጉብኝታቸው የመጀመሪያ ቀን በዋና ከተማዋ ጁባ ቆይታ አድርገዋል ፥ በማግስቱ ወደ ማላካል በማቅናት የሁለት ቀናት ቆይታ ካደረጉ በኋላ በመጨረሻም በሩምቤክ ከተማ የጉብኝታቸው ማጠቃለያ ያደርጋሉ።
ነሃሴ 8/ 2015 ዓ.ም. ዕለተ ሰኞ የካርቱም ሊቀ ጳጳስ ከሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ገብርኤል ዙቤይር ዋኮ ጋር በጁባ በሚገኘው ሐዋርያዊ ጉባኤ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን ፥ ከዚያም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከጥር 26-28 2015 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን ያደረጉትን ሃዋሪያዊ ጉዞ የሚያስታውስ የመታሰቢያ ሐውልት መርቀዋል። ከሰዓት በኋላ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ፣ ከቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻር እና ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ አሜዩ ጋር ተገናኝተዋል።
ማክሰኞ ዕእት ብፁዕ ካርዲናል ወደ ማላካል በማቅናት በካቴድራሉ ሥርዓተ ቅዳሴን በማሳረግ እና ከተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመገናኘት እንዲሁም ከሱዳን የሚመለሱ ስደተኞችን መቀበያ ማዕከል በመጎብኘት ቆይታ ያደርጋሉ።
በሚቀጥለው እሮብ ዕለት ካርዲናል ፓሮሊን በማላካል በሚገኘው የጳጳሳት መኖሪያ ቤት የሚደረገውን ሥርዓተ ቅዳሴ በማሳረግ ፥ በመቀጠልም የቅዱስ ቻርለስ ሉዋንጋ ትምህርት ቤት እና አነስተኛ ሴሚናርን ይጎበኛሉ ፤ ከዚያም ከ ‘ላይኛው ናይል ባሕላዊ አለቆች’ ማኅበረሰቦች ጋር ይገናኛሉ። ከሰዓት በኋላ ባለው መርሃግብር ፥ በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (UNMISS) ባለስልጣናት እና ሰራተኞች ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ ከማላካል ሀገረ ስብከት ካህናት፣ ከገዳማዊያን እና ከገዳማዊያት እንዲሁም ከሴሚናሮች ጋር ቆይታ ያደርጋሉ።
ሐሙስ ዕለት ፥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ወደ ራምቤክ በመጓዝ በዚያም ለሰላምና እርቅ የሚደረግ ቅዳሴን በማሳረግ የደቡብ ሱዳን ጉብኝታቸውን ያጠናቅቃሉ።

የካርዲናል ፓሮሊን የአንጎላ ጉብኝት ማጠቃለያ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በፓኪስታን ሐዋርያዊ መሪ አድርገው የሾሙትን የአንጎላ ተወላጅ የሆኑትን ሊቀ ጳጳስ ጀርመኖ ፔኔሞቴ የጵጵስና ሹመት ሥነ ስርዓት ላይ በመገኘት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በአንጎላ ያደረጉትን የሶስት ቀናት ጉብኝት እሁድ እለት አጠናቅቀዋል።
በተጨማሪም ካርዲናሉ እሁድ እለት በሉዋንዳ ሥርዓተ ቅዳሴን በማሳረግ እና የአንጎላ የፖለቲካ እና የቤተክርስቲያን መሪዎችን ላደረጉላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል አመስግነዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በአንጎላ የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያን “በፈተና ጊዜ የታደጋት የበለፀገ መንፈሳዊ ትውፊት ባለቤት ናት” ሲሉ አወድሰዋታል።
የአንጎላ ክርስቲያኖች በችግር እና በተስፋ መቁረጥ ውስጥም ቢሆን ሁሉንም ፍርሃት ለማሸነፍ እንዲጥሩ እና ትክክለኛ ትስስርን እንዲፈጥሩ ካርዲናሉ አበረታተዋቸዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመጨረሻም “እግዚአብሔርን በመሻት ብቻ ሕይወታችሁ ሙሉ ትሆናለች እንዲሁም ዕውቀታችሁም ዘላለማዊነትን ትጎናፀፋላችሁ” ብለዋል።
 

15 August 2023, 11:42