ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በእምነት፣ በጸሎት እና በንስሐ ክፉን መንፈስ እናሸንፋለን”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እሑድ የካቲት 14/2013 ዓ. ም በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ንባብ ላይ በማስተነተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ከማር. 1፡12-15 ተወስዶ የተነበበውን የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ንባብ መሠረት በማድረግ፣ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት ምዕመናን ስብከታቸውን አቅርበዋል። በስብከታቸው ባስተላለፉት መልዕክት “በጾም ወቅት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በእምነት በምናቀርበው ጸሎት አማካይነት በጠላታችን ዲያቢሎስ ላይ ድልን እንደምንቀዳጅ የእግዚአብሔር ጸጋ ያረጋግጥልናል” ብለዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን አስተንትኖ ሙሉ ትርጉም ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ረቡዕ የካቲት 10/2013 ዓ. ም. በአመድ የመቀባት ሥነ- ሥርዓትን በማካሄድ የአብይ ጾምን ጀምረናል።  በአምልኮ ስርዓታችን መሠረት ዛሬ የምናከብረው የአብይ ጾም የመጀመሪያ እሑድ እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ መታሰቢያ በዓል ድረስ የምናደርገውን አርባ የአብይ ጾም ቀናትን በፍሬያማነት እንድንጓዝ መንገድ ያሳየናል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ የተጓዘበትን መንገድ የሚገልጽ፣ የማር. ምዕ. 1፡12-15 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከት አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ወደ በረሐ በመሄድ አርባ ቀናት በሰይጣን መፈተኑን የሚገግልጽ ክፍል ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ማር. በምዕ. 1፡12 ላይ “ወዲያው ወደ በረሓ እንዲሄድ መንፈስ ቅዱስ አነሳሳው” በማለት ይነግረናል። ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይ መውረዱን እናስታውሳለን። ይኸው መንፈስ ቅዱስ ወደ “በረሐ” እንዲሄድና ፈታኙን እንዲንገጥም ይገፋፋዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ሙሉ በሙሉ እርሱን በሚያነቃቃ እና በሚመራው በእግዚአብሔር መንፈስ ቁጥጥር ስር ሆኖ እናያለን።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነውን እና በምሳሌነት የተጠቀሰውን እና “በረሐ” የተባለ የተፈጥሮ አካባቢ ትርጉም አንድ ጊዜ ቆም ብለን እንመልከት። በረሐ፣ እግዚአብሔር ከሰው ልጅ ጋር በጸሎት የሚገናኝበት እና ለጸሎቱም መልስን የሚያገኝበት ቦታ ነው። በረሐ ከዚህ በተጨማሪ የሰው ልጅ የሚፈተንበት፣ ሰይጣን የሰውን ደካማነት በመጠቀም፣ ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ የራሱን የውሸት መልዕክት እንደ አማራጭ የሚያሰማበት ሥፍራ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በበረሐ በቆየባቸው አርባ ቀናት ውስጥ በኢየሱስ እና በሰይጣን መካከል የተጀመረው ቅራኔ፣ ኢየሱስን በመስቀል ላይ በደረሰበት ስቃይ ተጠቃልሏል። የኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎት በሙሉ ከሰይጣን ጋር ባደረጋቸው የተለያዩ ትግሎች የታጀበ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ፥ ሰዎችን ከሕመማቸው መፈወስ፣ አጋንንትን ማውጣት እና ኃጢአትን ይቅር ማለት ነበሩ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚቀርብለት የተለያዩ ፈተናዎች የሰጣቸው መልሶች በእግዚአብሔር ኃይል የታገዙ ናቸው። የእግዚአብሔር ልጅ ተነጥሎ ብቻውን ሲቀር እና በመጨረሻም ተይዞ የሞት ፍርድ ሲፈረድበት፣ ዲያብሎስ የበላይነትን ያገኘ መሰለው። በእውነቱ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት፣ ሰይጣንን ለማሸነፍ እና እኛን ከሰይጣን ቀንበር ነጻ ለማውጣት የተጓዘበት የመጨረሻው የ “በረሐ” ጉዞ ነበር።    

በየዓመቱ በአብይ ጾም ወራት መጀመሪያ፣ ኢየሱስ በበረሐ እንደተፈተነ የሚያስታውሰን የቅዱስ ውንጌል ክፍል፣ ክርስቲያኖችም የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት በመከተል ከክፉ መንፈስ ጋር መታገል እንዳለብን ያሳስበናል። ይህ የወንጌል ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈተና ራሱን አሳልፎ የሰጠው በፍላጎት መሆኑን እና ፈተናውንም አሸንፎ መውጣቱን ይነግረናል። በሌላ ወገን ዲያቢሎስ እንዲፈትነን እኛ ዕድል መስጠታችንን ያስረዳል። ዘለዓለማዊ ቅጣትን እንድንቀበል፣ ዘወትር ወደ ውድቀት የሚመራን፣ በእርሱ እንድንሸነፍ የሚፈልግ ጠላታችንን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በእምነት በምናቀርበው ጸሎት አማካይነት በጠላታችን ላይ ድልን እንደምንቀዳጅ የእግዚአብሔር ጸጋ ያረጋግጥልናል።

ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ በረሐ እንደመራ ሁሉ በአብይ ጾም ወቅት እኛን ወደ “በረሐ” ይመራናል። ይህ በረሐ በአካል እንደምናየው በረሐ ሳይሆን፣ ዝም ብለን የእግዚአብሔርን ቃል መስማት የምንችልበት፣ በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ለውጥን የምናሳይበት የሕይወት ልኬት ነው። በምስጢረ ጥምቀት የተቀበልነውን ጸጋ በማደስ፣ ሰይጣንን፣ ሥራዎቹን እና ባዶ ተስፋዎቹን ሁሉ በመካድ እግዚአብሔርን እንድንከተል ተጠርተናል። ለዚህም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታግዘን በማለት የእርሷን እናታዊ አማላጅነት እንለምናለን"።

23 February 2021, 15:03

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >