ፈልግ

አቶ መሐመድ ዩኑስ ከቫቲካን ሬድዮ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት  አቶ መሐመድ ዩኑስ ከቫቲካን ሬድዮ ጋር ቃለ ምልልስ ባደረጉበት ወቅት  

ዓለማችንን ከተሳሳተ አቅጣጫ ለመመለስ በጋራ መሥራት ይገባል ተባለ

በቫቲካን ውስጥ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባን የተካፈሉት 30 የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች፥ ዓለማችንን ከተሳሳተ አቅጣጫ ለመመለስ በጋራ እንደሚሠሩ አስታወቁ። ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተካሄደውን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ስብሰባን የተካፈሉት የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ዓለማችንን ከተሳሳተ አቅጣጫ መመለስ የሚቻለው ድምጻችንን በጋራ በማሰማት ብቻ ነው” በማለት ተማግረው፥ ሁሉም በኅብረት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመሪነት ሚናን እና የሰላም እና የአካባቢ ጥበቃ ጥሪዎችን እንደሚቀበሉ አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ከምንገኝበት ዓለም ይልቅ ሰላም ማምጣት የሚቻልበት አዲስ ዓለምን መገንባት እና ይህን ለማሳካት ሰዎች ድምጻቸውን ማስተባበር ይገባል” በማለት በባንግላዲሽ የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪ በመሆን የሚታወቁት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2006 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የነበሩት አቶ መሐመድ ዩኑስ ተናግረዋል። አቶ መሐመድ ዩኑስ ይህን የተናገሩት ከኢራቃዊቷ ማኅበርሰብ አንቂ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2018 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ከሆኑት ናዲያ ሙራድ ጋር ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባ ላይ እንደነበር ታውቋል።

የወንድማማችነት ዓለም ለመገንባት ሃይማኖቶች የሚጫወቱት ሚና

ብዙ ተፎካካሪ ፍላጎቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ የጋራ መግባባትን እንዴት መፍጠር እንደሚቻል የተጠየቁት አቶ መሐመድ ዩኑስ፥ “ለክርክር እና ለውይይት የሚቀርቡ ርዕሠ ጉዳዮችን በጋራ ለመመልከት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መልካም አጋጣሚዎች ናቸው” ብለዋል። በመቀጠልም ከምድር ገጽ ለአንዴ እና መጨረሻ ጊዜ እንደጠፉ ፍጥረታት ሁሉ፥ ዛሬ የምንጓዝበት መንገድም ለተመሳሳይ አደጋ የሚዳርግ ነው” ብለዋል። “የምንጓዝበት መንገድ የተሳሳተ ነው” በማለት ደጋግመው የተናገሩት አቶ መሐመድ ዩኑስ፥ "አሁን ከምንገኝበት ዓለም ይልቅ አዲስ ንድፍ በማዘጋጀት እና መድረሻችንን በመቀየር አዲስ ዓለም መገንባት አለብን" ብለው፥“በዚህ ረገድ ቫቲካን የሚጫወተው ሚና ጠንካራ ነው” በማለት ገልጸዋል። “ኃይማኖቶች በሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ የገለጹት አቶ መሐመድ ዩኑስ፥ ሁሉም ሃይማኖቶች ወንድማማችነትን ለማጎልበት ሊሠሩ እንደሚገባ እና በዚህ አቅጣጫ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን የመሪነት ሚና እንጠብቃለን” ብለዋል።

የእያንዳንዱ ግጭት መሠረት የወንድማማችነት እጦት ነው!

በኮንጎ ዴማክራሲያዊት ሪፐብሊክ የማህፀን ሐኪም፣ የሴቶች መብት ተሟጋች እና የማኅበረሰብ አንቂ የሆኑት ዶ/ር ዴኒስ ሙኩዌጄ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፥ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ጭብጥ ለፍትሃዊ ዓለም መሠረታዊ እንደሆነ አብራርተው፥ የወንድማማችነት እጦት ለሠላሳ ዓመታት ያህል በኮንጎ ሕዝብ ላይ በተለይም በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የግጭት መነሻው እንደሆነ ተናግረዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2018 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው የሆኑት ዶ/ር ዴኒስ ሙኩዌጄ፥ “የሰው ልጅ እንደ ወንድም እና እህት በሚታይበት ዓለም ምዕራባውያን በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሚገኙትን ብርቅዬ ማዕድናትን በመቀራመት ለደኅንነታቸው እና የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ለማምረት ስለሚፈልጉ ብቻ አንድን ሕዝብ ለሦስት አሥርተ ዓመታት እንዲሰቃይ አንፈቅድም” ካሉ በኋላ፥ “እነዚህን እና ሌሎች የሕዝብ ስቃዮች ቸል የምንለው በወንድማማችነት እጦት ነው" ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።

የጦር መሣሪያ ንግድ ይብቃ!

ለመካከለኛው አሜሪካ ሕዝቦች ባወጡት ውጤታማ የሰላም ዕቅድ እንደ ጎሮሳውያኑ 1987 ለኖቤል የሰላም ሽልማት የበቁት የኮስታ ሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ኦስካር አርያስ በበኩላቸው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ካለው እጅግ ስቃይ ከበዛበት ጦርነት እና ሌሎች ግጭቶች ጋር በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እንገኛለን” ብለው፥ “ከሁሉም በላይ የጦር መሣሪያ አምራቾች ዋና ዓላማ በጦርነት የሚሞቱ ሰዎችን እና የቤተሰቦቻቸውን ስቃይ ከማሰብ ይልቅ በጦር መሣሪያ ንግድ የበለጠ ገንዘብ ማግኘት ብቻ ነው” ብለዋል።

በማዕከላዊ አሜሪካ አገር ኒካራጓ ውስጥ ጳጳሳት እና ካኅናት እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ፥ ገዳማውያን እና ገዳማውያት ከአገር እንዲወጡ እንደሚደረጉ ያስረዱት የኮስታ ሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ኦስካር አርያስ፥ “የታሰሩት እንዲፈቱ እና የሕዝቡን ደኅንነት ለማስከበር ድምጻችንን ማሰማት ያስፈልጋል” ብለዋል።

የሰላም እና የአየር ንብረት ለውጥ ጥሪ መቀብል ያስፈልጋል

"የህልውና ችግሮችን ለመፍታት የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ ውይይት በመሆኑ፥ የዓለም መሪዎች ለስልጣን ከመፎካከር ይልቅ ለውይይት ወደ ጠርጴዛ ዙሪያ መቅረብ አለባቸው ያሉት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2010 እስከ 2018 ዓ. ም. ድረስ የኮሎምቢያ ፕሬዚደንት የነበሩ እና አገራቸው ከእርስ በርስ ጦርነት እንድትወጣ ባደረጉት ጥረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2016 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት አቶ ዩዋን ማኑኤል ሳንቶስ፥ “ለዓለም አቀፍ ግጭቶች ዋና ምክንያት ከሆኑት መካከል የአየር ንብረት ለውጥ እየጨመረ እና የበለጠ ውድመት እያስከተለ ይገኛል” በማለት አስረድተው፣ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ስጋት፣ ወረርሽኞች እና የተሳሳተ የቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም መኖሩን ገልጸው፥ “ለዚህም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስን፣ በተለይም ከተፈጥሮ እና ከአካባቢ ጋር ተስማምቶ በሰላም የመኖር አስፈላጊነትን በማስመልከት የጻፏቸውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናት ማንበብ እና ጥሪያቸውን መቀበል ያስፈልጋል" ብለዋል።

15 June 2023, 17:20