ፈልግ

የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባን የተካፈሉት የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች እና ሌሎች እንግዶች የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባን የተካፈሉት የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች እና ሌሎች እንግዶች 

ካርዲናል ፓሮሊን፥ ዓለማችን ተስፋን እና ወንድማማችነትን በመፈለግ ላይ እንደሚገኝ ተናገሩ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ ዓለማችን ተስፋን እና በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነት እንዲኖር መፈለጉን ገልጸዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ሆስፒታል ገብተው የሕክምና ዕርዳታን በማግኘት ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና ሕክምናቸውን ጨርሰው ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው ለመመለስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች፣ ለአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች፣ ለትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች፣ አቅመ ደካሞች ለሆኑ ድሃ ማኅበረሰብ እና ለተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች ባደረጉት ንግግር፥ የዓለም አቀፍ ወንድማማችነት ስብሰባን የሚካፈሉት ግለሰቦች የተስፋ ምልክት እንደሆኑ እና “በኅብረት የተገኙት የተስፋ ምልክቶች በመሆናቸው ነው” ብለዋል።

ብጹዕነታቸው ሠላሳ ለሚደርሱ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች እና ለአገራት መሪዎች ባደረጉት ንግግር፥ “በወንድማማችነት መንፈስ በኅብረት መንቀሳቀስ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባሕልን ለማስፋፋት በተጠሩት አካላት ሊደናቀፍ የማይችል ሃላፊነት ነው” ብለው፥ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በነበራቸው የሕይወት ተሞክሮዎች ውይይቶች እንደሚቋረጡ እና ግንኙነቶች የሚበላሹ መሆኑን አስታውሰው፥ “ወንድማማችነት ያለበት አንድነት ከመከፋፈል እና ከልዩነት የበለጠ ጠንካራ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች ቁርጠኝነት

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባን ከተካፈሉት ሠላሳ የሚደርሱ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች መካከል የቀድሞው የኮሎምቢያ ፕሬዚደንት አቶ ዩዋን ማኑኤል ሳንቶስ ከቫቲካ የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ አገራት የውይይት እና የትብብር ዘዴን እንደሚያገኙ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ ወንድማማችነትን ለመገንባት ብቸኛው መንገድ ይህ እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም "የኮሎምቢያ የሰላም ሂደት ምንም ዓይነት ግጭቶች ሊፈቱ እንደሚችሉ አስተምሮኛል” ብለው “በዚህ አስተሳሰብ ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚፈጠሩ ብዙ ግጭቶችን መፍታት እንደምንችል አምናለሁ” ብለዋል።

የቀድሞው የኮስታሪካ ፕሬዝዳንት አቶ ኦስካር አርያስ ሳንቼዝ፥ “በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እጅግ አሰቃቂ እንደሆነ ገልጸው፥ በግጭቱ ውስጥ ሁለቱም ወገኖች ለመደራደር ምንም ፍላጎት እንደሌላቸው በሐዘን ስሜት ገልጸዋል።

የባንጋላዴሽ የምጣኔ ሃብት ሊቅ ሙሐመድ ዩኑስ በበኩላቸው፥ ቫቲካን ሰብዓዊ ወንድማማችነትን መሠረት ያደረገ ስብሰባ መጥራቷ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ ዓለም ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚናገር ክፍል ሊኖር ይገባል ብለዋል።

የየመን የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ወ/ሮ ታዋኮል ካርማንም በበኩላቸው፥ እንደ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባን የመሰሉ ሌሎች ስብሰባዎችም መልዕክቶችን ማሰራጨት ብቻ ሳይሆን መልእክቶችን በከፍተኛ ቁጥር ማሰራጨት እና ሰዎች የወንድማማችነትን ትክክለኛ ትርጉም እንዲገነዘቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ወ/ሮ ታዋኮል በማከልም እሴቶችን የሚያጠቁ መሪዎችን ሳይሆን ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ እና ለሰላም የሚታገሉትን እና መስዋዕትነት የሚከፍሉ ወገኖችን መደገፍ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

የወንድማማችነት መንገዶች

“Not alone” ወይም “ብቻችን አይደለንም” በሚል ተነሳሽነት “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለው የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ምርህ በመከተል የተካሄደውን ስብሰባ በኅብረት ያዘጋጁት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት እና የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ አስተዳደር ሲሆኑ፣ የስብሰባው ዓላማም የወንድማማችነት፣ የውይይት እና የሰላም ባሕልን ለማሳደግ ሲሆን፥ ስብሰባውን ከመላው ዓለም የተውጣጡ የተለያዩ ግለሰቦች እና ወጣቶች ተካፍለውታል። ስብሰባው ባሁኑ ጊዜ ጦርነት ውስጥ ከሚገኙ ሩሲያ እና ዩክሬን በመጡ ሁለት ወጣቶች መድመቁን የተናገሩት የቫቲካን ከተማ ረዳት አስተዳዳሪ እና የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ፥ ሁለቱ ወጣቶች ዓለም አቀፋዊ መሆን የሚፈልግ የዚህ መድረክ አካል እንደሆኑ እና የመድረኩ ዋና ዓላማም “ወንድማማችነት” የሚለውን ቃል በህሊና ውስጥ ለመቀስቀስ እንደሆነ ተናግረዋል።

ቅዱስነታቸው ከሕመማቸው በማገገም ላይ ይገኛሉ

ከጠዋቱ የስብሰባ ጊዜ አስቀድመው ከጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልል ያደረጉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ስለ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጤንነት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፥ ቅዱስነታቸው በመልካም የማገገም ሂደት ላይ እንደሚገኙ እና ሕክምናቸውን ጨርሰው ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው ተመልሰው ሥራቸውን ለመቀጠል እንደሚፈልጉ እና ይህም ጥሩ ምልክት እንደሆነ ተናግረዋል።

ቅድስት መንበር በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ አተኩራለች

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬን ስላለው ጦርነት ሲናገሩ፥ “ብፁዕ ካርዲናል ዙፒ ኪዬቭን በጎበኙበት ወቅት የተፈጠረውን ነገር በማስመልከት ለቅዱስነታቸው ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ገልጸው፥ “ከዚያ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለብን አብረን እናሰላስላለን” ብለዋል። የጣሊያን ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ በዩክሬን የነበራቸው ተልዕኮ ጥሩ ነበር ገልጸው፥ ብጹዕነታቸው ከፕሬዝደንት ዜለንስኪ ጋር ያደረጉት ውይይት እንደ ተራ ነገር ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም” ብለዋል። አክለውም “ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ  ከዚህ ቀደም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በገለጹት ሃሳብ መሠረት የሰላም ውይይቱን በጥልቀት የማዳበር ዕድል እንዳለ ጠቁመው፥ “እነዚህም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰፊ ድጋፍን ለማግኘት የሚፈልጉ የሰላም እቅዶችን ያጠቃልላል” ብለዋል።

በካርዲናል ዙፒ እና በፓትርያርክ ኪሪል መካከል ሊኖር የሚችል ውይይት

በካርዲናል ማቴዮ ዙፒ እና በሞስኮው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪሪል መካከል ውይይት ሊካሄድ ይችል እንደሆን ተጠይቀው ሲሰጡ፥"ስለ ሞስኮ ጉብኝት እስካሁን አልተነጋገርንም፤ ነገር ግን አስቀድመን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መነጋገር እና ያሉት ዝንባሌዎች ምን እንደሆኑ መመልከት አለብን” ብለዋል። “ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ኪሪል ጋር ለመገናኘት የሚከለክል ምንም እንቅፋት የለም” ያሉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊው፥  በግዳጅ ወደ ሩሲያ የተወሰዱ ሕጻናት ሁኔታ በተመለከተ “ጉዳዩ አሳሳቢ ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው፥ “ጉዳዩ ቀላል ባለመሆኑ የተነሳ መፍትሄን ለማግኘት መሥራትን እንቀጥላለን” ብለዋል።

የወንድማማችነት ጎዳና

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በቃለ ምልልሳቸው ማጠቃለያ ላይ ከኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች ጋር ስላደረጉት ስብሰባ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ "በሰብዓዊ ወንድማማችነት ስሜት ለመሥራት በሁሉም ዘንድ ቁርጠኝነት አለ" ብለው፥ ግጭቶችን ለማሸነፍ የሚያስችል ተጨባጭ ቁርጠኝነት ሊኖር እንደሚገባ እና ይህ ቁርጠኝነት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 

12 June 2023, 17:47