ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓርፕሊን ከኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓርፕሊን ከኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች የሰብዓዊ ወንድማማችነት ጥሪን እንቀበላለን አሉ

ቫቲካን ውስጥ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ስብሰባን የተካፈሉት ሠላሳ የኖቤል ተሸላሚዎች በወንድማማችነት ሰነድ ላይ የቀረበውን ጥሪን መቀበላቸውን አስታወቁ። የወንድማማችነት ሰነዱ በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች በሙሉ የወንድማማችነት ጥያቄን እንዲቀበሉ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ ሰነዱን የፈረሙት የኖቤል ተሸላሚዎች “ልጆቻችን እና የወደፊት ሕይወታችን ማደግ የሚችለው ሰላም፣ ፍትህ እና እኩልነት በሰፈነበት ዓለም ብቻ እና ይህም ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ጥቅም ነው” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰነዱን ጥሪ ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም.  በፊርማቸው ያረጋገጡት 30 የኖቤል ተሸላሚዎች ቡድን፥ “እያንዳንዱ ወንድ ወንድማችን፣ እያንዳንዷ ሴት እህታችን ናት” በማለት ገልጸው፥ “ሁላችንም ውብ በሆነች ምድራችን ውስጥ እንደ ወንድሞች እና እህቶች አብረን ለመኖር እንፈልጋለን” ብለው፥ ወንድማማችነት ለሕይወት በሙሉ መሠረታዊ ነው” በማለት አስረድተዋል። የኖቤል ተሸላሚዎቹ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረት በማድረግ ወንድማማችነትን እና ማኅበራዊ ወዳጅነትን ለማበረታታት በቫቲካን የተዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ቀንን ተካፍለዋል።

ዓለማችን በተሳሳተ መንገድ ላይ ነው

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2006 ዓ. ም. የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እና ከግራሚን ባንክ ጋር በመተባበር በባንግላዲሽ ውስጥ የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪ በመሆን የሚታወቁት አቶ መሐመድ ዩኑስ፥ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማትን ለመፍጠር ጥረት ባደረጉበት ወቅት የተመለከቱትን ሲያስረዱ፥ ዓለም በተሳሳተ መንገድ እየተጓዘች ትገኛለች” ካሉ በኋላ በቫቲካን ለተካፈሉት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባ አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቷል።

አቶ መሐመድ ዩኑስ ከቫቲካን ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልስስ፥ “ዓለማችን በተሳሳተ መንገድ እየተጓዘች መሆኗን የሚያሰማ ሕዝብ መኖር አለበት" ብለዋል። አክለውም "አሁን ከምንገኝበት ዓለም ይልቅ አዲስ ንድፍ በማዘጋጀት እና መድረሻችንን በመቀየር ሰላምን ለማምጣት የሚያስችለንን አዲስ ዓለም መገንባት አለብን" ብለዋል። “ሰዎች ድምጻቸውን ሊያሰሙ ይገባል” በማለት ያቀረቡት ጥሪ በመጨረሻው ሰነድ ውስጥም የተካተት ሲሆን፥ ጦርነት ይብቃ! የሰው ልጆችን ዕጣ ፈንታ የሚወስን ሰላም፣ ፍትህ፣ እና እኩልነት ይስፈን! ፍርሃት፣ ወሲባዊ እና የቤት ውስጥ ጥቃት ይቁም! ማንኛውም የትጥቅ ትግል መቆም አለበት! ከእንግዲህ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እና የፈንጂ ምርት ይቁም! የግዳጅ ስደት፣ የጎሳ ማጥፋት፣ አምባገነንነት፣ ሙስና እና ባርነት ይቁም! ቴክኖሎጂን እና ሰው ሠራሽ አዕምሮን ለግል ፍላጎት መጠቀሚያ ማድረግ ይቁም! ከቴክኖሎጂ ዕድገት ይልቅ ወንድማማችነትን እናስቀድም! በማለት በወንድማማችነት ስም ለመላው ዓለም መጮህ እንፈልጋለን” ብለዋል።

የሃይማኖት ሚና

ብዙ ተፎካካሪ ፍላጎቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ የጋራ መግባባትን እንዴት መፍጠር እንደሚቻል የተጠየቁት አቶ መሐመድ ዩኑስ፥ “ለክርክር እና ለውይይት የሚቀርቡ ርዕሠ ጉዳዮችን በጋራ ለመመልከት ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መልካም አጋጣሚዎች ናቸው” ብለዋል። በመቀጠልም ከምድር ገጽ ለአንዴ እና መጨረሻ ጊዜ እንደጠፉ ፍጥረታት ሁሉ፥ ዛሬ የምንጓዝበት መንገድም ለተመሳሳይ አደጋ የሚዳርግ ነው” ብለዋል። “የምንጓዝበት መንገድ የተሳሳተ ነው” በማለት ደጋግመው የተናገሩት አቶ መሐመድ ዩኑስ፥ "አሁን ከምንገኝበት ዓለም ይልቅ አዲስ ንድፍ በማዘጋጀት እና መድረሻችንን በመቀየር አዲስ ዓለም መገንባት አለብን" ብለው፥“በዚህ ረገድ ቫቲካን የሚጫወተው ሚና ጠንካራ ነው” በማለት ገልጸዋል። “ኃይማኖቶች በሰው ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ የገለጹት አቶ መሐመድ ዩኑስ፥ ሁሉም ሃይማኖቶች ወንድማማችነትን ለማጎልበት ሊሠሩ እንደሚገባ እና በዚህ አቅጣጫ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስን የመሪነት ሚና እንጠብቃለን” ብለዋል።

ለሰብዓዊ ወንድማማችነት መሥራት እና የመደገፍ ግዴታ

ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. የተካሄደውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባን ከተካፈሉት የኖቤል ተሸላሚዎች መካከል ወ/ሮ ታዋኮል ካርማን ጋዜጠኛ እና ማኅበረሰብ አንቂ ሲሆኑ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2011 ዓ. ም. ሽልማቱን የተቀበሉ የመጀመሪያው የመናዊ እንደነበሩ ይታወሳል።

ወ/ሮ ታዋኮል ካርማን የኖቤል ሽልማቱን ከሌይማ ግቦዌ እና ከኤለን ጆንሰን ሺርሊፍ ጋር በጋራ ያሸነፉት “ለሴቶች ደኅንነት ባደረጉት ሰላማዊ ትግል እና ሴቶች በሰላም ግንባታ ላይ ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እና መብታቸውንም ለማስከበር ባደረጉት ጥረት እንደነበርም ይታወሳል።

ወ/ሮ ታዋኮል ካርማን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፥ “የሰው ልጆች ወንድማማችነትን መደገፍ እና ለዓላማው መሥራት ግዴታችን ነው፤ በዓለም አቀፍ ቀን የተሰበሰብነውም ለዚህ ዓላማ ነው” ብለዋል። “ለሰላም ተገቢውን ትርጉም መስጠት እንደሚገባ፣ አንድ ላይ በመሆን በጋራ መሥራት እና መደጋገፍ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስበንን የሰብዓዊ ወንድማማችነት መፈክርን ወድጄዋለሁ” በማለት ወ/ሮ ካርማን ተናግረዋል።

በተለይ የጋዜጠኞችን ሚና ሲናገሩ “እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ እንደ ጋዜጠኛ፣ በአፈና ሥርዓቶች እና በአምባገነን መንግሥታት ሥር ለነበሩት ሰዎች የበለጠ ጠንካራ ድምጽ የመሆን ሃላፊነት አለብን” በማለት ተናግረዋል። “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ጨምሮ እራሳቸውን በሥልጣን ደረጃ የሚያስቀምጡት የዓለም መሪዎች ሃላፊነት በመሆኑ፥ ይህን ትርጉም እና እሴት ወደ ሁሉ የዓለማችን አካባቢዎች ማዳረስ እንዳለባቸው እና ይህም ማለት ኅብረተሰባቸውን ለሚከፋፍሉ፣ ማኅበረሰባቸውን ለሚገድሉ አምባገነኖች ምንም አይነት ሕጋዊነት መስጠት እንደሌለባቸው የሚጠይቅ በመሆኑ ይህ ሥራ የእኛም ጭምር ነው” ብለዋል።

ለነጻነት እና ለፍትህ የሚታገሉትን መደገፍ

በሰብዓዊ ወንድማማችነት ዓለም አቀፍ ቀን በአንድነት ተሰብስቦ በሰው ልጅ ላይ በሚሰነዝሩ ጥቃቶች እና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በማትኮር መወያየት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት የመናዊ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ወ/ሮ ታዋኮል ካርማንም፥ እንደ ሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባን የመሰሉ ሌሎች ስብሰባዎችንም በማካሄድ መልዕክቶችን ማሰራጨት ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ድምጽ በማጉላት ሰዎች የወንድማማችነትን ትክክለኛ ትርጉም እንዲገነዘቡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው አክለውም እሴቶችን የሚያጠቁ መሪዎችን ከማገዝ ይልቅ ለነጻነት፣ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ እና ለሰላም የሚታገሉትን እና መስዋዕትነት የሚከፍሉ ወገኖችን መደገፍ እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል።

13 June 2023, 17:11