ፈልግ

በሳልቫዶር ከሚካሄድ የእርሻ ስልቶች መካከል አንዱ በሳልቫዶር ከሚካሄድ የእርሻ ስልቶች መካከል አንዱ 

ካርዲናል ታርክሰን፣ ባሕላዊ የምግብ ሥርዓትን መከተል የምግብ ዋስትናን ያረጋግጣል አሉ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በሮም ከሰኞ ሐምሌ 19 - 21/2013 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል። ብጹዕነታቸው ለስብሰባው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር የምግብ ምርት መጠንን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው፣ በገጠራማ አካባቢዎች በአነስተኛ የግብርና ሥራ ላይ ለተሰማሩት ገበሬዎች ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እስከ አውሮፓዊያኑ 2050 ዓ. ም ድረስ ከዘጠኝ ቢሊዮን በላይ ለሚሆን የዓለማችን ሕዝብ የሚቀርብ የምግብ መጠን ሃምሳ ከመቶ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ይህን ማድረግ ከተፈለገ በገጠራማው አካባቢ የሚገኙ ገበሬዎችን የምግብ ሥርዓት ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን አስረድተዋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በመላው ዓለም ከሚገኙ ባሕላዊ የእርሻ ሥራ ተጠቃሚዎች እና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ሕዝባዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጋር በመነጋገር የምግብ እጥረትን ለማስወገድ የሚያስችሉ ምቹ መንገዶችን መቀየስ እንደሚያስፈልግ ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን አሳስበዋል።

የምግብ ሥርዓቶች እና ተፈጥሯዊ የአመጋገብ ዘዴን ማሳደግ

በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ዋና ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን የምግብ ሥርዓትን መጠቀም ያስፈለገበት ምክንያት ሲያስረዱ፣ በተለይም ለአየር ንብረት ለውጥ በተጋለጡ አካባቢዎች የሚታየውን የአየር ጸባይ ለውጥ፣ ድርቅን እና የተፈጥሮ አደጋን ለሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም ማሻሻል ስለሚቻል ነው ብለዋል።

በዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ተለይተው የተቀመጡ የዓለማችን ክልሎች

በዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት በኩል በማኅበራዊ እና ባሕላዊ ሕይወት ልዩነትን በማሳየታቸው ተለይተው የተቀመጡ ሰባት የዓለም አካባቢዎች መኖራቸውን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን እነዚህም አፍሪካ፣ እስያ፣ መካከለኛው አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ካሬቢያን አገሮች፣ አርክቲክ አገሮች፣ መካከለኛው እና ምሥራቅ አውሮፓ፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን፣ መካከለኛው እስያ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ፓሲፊክ አገሮች መሆናቸውን አስታውሰዋል። በማኅበራዊ እና ባሕላዊ የኑሮ ዘዴ ተለይተው የተቀመጡ አገሮች እንደ አመቺነቱ የምግብ ሥርዓቶቻቸውን በተግባር መጠቀም እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ቀደም ሲል ታፍነው የቆዩ አገር በቀል ተቋማት እንደገና ማዋቀር

በዓለማችን ውስጥ አብዛኛው ክፍል ባሕላዊ የእርሻ ዘዴን የሚከተል መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም በእነዚህ የዓለማችን ክፍሎች በተግባር ሲገለገሉባቸው የቆዩ ባሕላዊ እና ተፈጥሮአዊ የእርሻ ዘዴዎችን መልሶ ለመጠቀም ማኅበራዊ ተቋማትን እንደገና ማዋቀር ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህ በፊት በምግብ አቅርቦት ላይ የተደረጉ ጥናቶች እና ምርምሮች የአየር ንብረት ለውጥ ቢኖርም ባሕላዊ እና ማኅበራዊ የተፈጥሮ የእርሻ ዘዴዎች መልካም ውጤቶችን ሲያመጡ የቆዩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። አክለውም በገጠራማው የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ አነስተኛ ገበሬዎች የተለያዩ የእርሻ ዘዴዎችን በመጠቀም የምግብ እጥረትን በማስወገድ ከረሃብ የሚወጡበትን መንገድ ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆናቸውን አስታውስዋል።

የእርሻ ምርት ንግድ የምግብ ዝርያዎችን ይጎዳል

የሃዋይ እና የአውስትራሊያ አነስተኛ ገበሬዎችን የእርሻ ምርት መጠን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በእነዚህ አካባቢዎች በተግባር ላይ የዋሉት ባሕላዊ የእርሻ ዘዴዎች በአገሩ የነበሩ የተለያዩ የእህል ዝሪያዎች ባሕሪያቸውን ሳይቀይሩ ለረጅም ዓመታት እንዲቆዩ ማድረግ የተቻለ መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን በአዲስ መልክ ከሌላ አካባቢ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እንግዳ ሰብሎች፣ ማዳበሪያዎች፣ ተባይ ማጥፊያ እና አረም መከላከያ መድኃኒቶች ለባሕላዊው የእርሻ ዘዴ የሚስማሙ አለመሆናችውን አስረድተዋል። ለንግድ ሲባል አዳዲስ የእህል ዝሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ማስተዋወቅ ከባሕላዊው የእርሻ ዘዴ እና ከቀደመው የእርሻ ሰብል ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን አስረድተዋል። አክለውም ማዳበሪያን መጠቀም ውጤታማ የሚሆነው አፈሩ ሲሞት ብቻ እንደሆነ፣ የተባይ መከላከያ መድኃኒት ውጤታማ የሚሆነው ጤናማ ያልሆኑ ተክሎች ያሉ እንደሆነ፣ ትላልቅ የግብርና ማሽኖችን መጠቀም የሚያስፈልገው ሰፊ የእርሻ መሬትን ማልማት ሲያስፈልግ ብቻ እንደሆነ አስረድተው እነዚህን አላስፈላጊ ዘዴዎችን ለም በሆነ እርሻ ላይ መጠቀም ጉዳት እንጂ ጥቅም የማያስገኝ መሆኑን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ገልጸዋል።    

28 July 2021, 13:23