ፈልግ

ከማኅደራችን የተገኘ ከማኅደራችን የተገኘ 

በዓለማችን ውስጥ ረሃብ ሰብዓዊ መብትን የሚጻረር አሳፋሪ ወንጀል መሆኑ ተገለጸ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሮም ከሰኞ ሐምሌ 19-21/2013 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ላለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባ በላኩት መልዕክት፣ በዓለማችን ውስጥ ረሃብ የሚያስከትለውን ስቃይ ማስወገድ የሁላችን ግዴታ ነው ብለው፣ ከዚህም በተጨማሪ ረሃብን ለማስወገድ ቆራጥ እና ትክክለኛ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል። አክለውም በዓለማችን ውስጥ ረሃብ ሰብዓዊ መብትን የሚጻረር አሳፋሪ ወንጀል መሆኑ ገልጸዋል። የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን መልዕክት ለስብሰባው ተካፋዮች ያሰሙት በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለማችንን እያሰቃየ በሚገኝበት ባሁኑ ወቅት አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ ምግብ እጦት ዓለማችንን የሚፈታትን፣ የሚያሳፍር፣ ወንጀል እና ኢፍትሃዊ ነው በማለት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ለሆኑት ለክቡር አቶ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በላኩት መልዕክት ገልጸዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት በሮም ከሐምሌ 19-21/2013 ዓ. ም.  ድረስ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ስብሰባ እስካሁን ተግባራዊ እየሆነ ያለውን የምግብ ሥርዓት በስፋት በማጤን በመጪው መስከረም ወር 2014 ዓ. ም. በአሜሪካ ውስጥ ኒው ዮርክ ለሚካሄደው የመጨረሻው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለመዘጋጀት መሆኑ ታውቋል። ስብሰባው እጅግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነው ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በተለይም በዓለማችን የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሰብዓዊ ቤተሰብ መካከል ያለውን ኅብረት አደጋ ላይ በመጣሉ ነው ብለዋል። በሰው ልጆች ላይ ጉዳትን ከሚያስከትሉት አደጋዎች መካከል ድህነትን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችን ስቃይ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ለዚህም በቅድሚያ የሚጠቀሱት ሃላፊነት የጎደለው የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም እና ለጋራ ጥቅም ከእግዚአብሔር የተሰጡንን የተፈጥሮ ስጦታዎች በተሳሳተ መንገድ መጠቀም መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገናል

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች በላኩት ጥብቅ መልዕክት ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ምድራችን ለሕዝቦቿ የምታቀርበውን የምርት መጠን ለማሳደግ የቴክኖሎጂውን ዘርፍ መመልከት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም ምድራችን በቂ ምርትን እንዳትሰጥ እና የምድራችን በረሃማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲሰፋ የምናደርግ ከሆነ፣ አስተማማኝ እና በቂ ምርት ቢመረትም ዞሮ ዞሮ በርካቶች ዕለታዊ ምግባቸውን ሳያገኙ የሚቀሩ መሆናቸውን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ ምግብ እጦት ደግሞ መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችን የሚጻረር፣ ዓለማችንን ፈተና ውስጥ የሚከት፣ የሚያሳፍር፣ ወንጀል እና ኢፍትሃዊ ነው በማለት ገልጸዋል። ይህን ከወዲሁ ለመከላከል መልካም እና ትክክለኛ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለው፣ ቆራጥነት ያለው ብሔራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ውሳኔ ሊኖር ያስፈልጋል ብለዋል።   

የምግብ ሥርዓቶች ዘላቂ እና የአከባቢ ጥበቃ ያክብሩ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ጠቃሚ ሃሳብ ይሆናል ብለው ባቀረቡት አስተያየት፣ በመጀመሪያ ደረጃ በምግብ ሥርዓቶች ላይ ጥንቃቄ ተደርጎባቸው ትክክለኛ መንገድን በመከተል ለውጦች እንዲደረጉ እና ይህም ዘላቂነት ያለውን የአካባቢ ጥበቃ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ እና ለአካባቢው ባሕልም እውቅና ለመስጠት ያግዛል ብለዋል። የእነዚህ ተግባራት ዋና ዓላማ የአካባቢያዊ ችግሮችን የመቋቋም አቅም ለማሳደግ፣ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር ፣ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል ፣ የምግብ ብክነትን ለመቀነስ እና ጤናማ እና ተደራሽ የሆኑ ምግቦችን ለሁሉም ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። እነዚህ ለውጦች ከሰዎች ልብ ውስጥ መፍለቅ እንዳለባቸው የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ረሃብ የሚወገደው በቂ ምግብን በማዘጋጀት እንዳልሆነ፣ ነገር ግን የጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያስችል አዲስ አዕምሮን በመፍጠር፣ በተለይም ሰብዓዊ ክብርን የሚያስቀድም አዲስ የምግብ ሥርዓቶችን በመገንባት መሆኑንም በማከል አስረድተዋል።

የገጠሩን የግብርና ዘርፍ ማዕከላዊ ማድረግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለስብሰባው ተካፋዮች ባቀረቡት ሁለተኛ ጠቃሚ ሃሳባቸው፣ የሰውን ልጅ ክብር የጠበቀ በቂ ምግብ በዓለም አቀፍ እና በብሔራዊ ደረጃ ሊኖር ይገባል ብለው፣ የዛሬው ዓለም የምግብ አቅርቦት የመጪውን ጊዜ የምግብ አቅርቦት የሚያደናቅፍ መሆን የለበትም ብለዋል። አክለውም የገጠሩን የግብርና ዘርፍ ማዕከላዊነት በማክበር የገጠሩ የግብርና ዘርፍ ወሳኝ በሆኑ የፖለቲካ እና የኤኮኖሚ ሂደቶች ውስጥ በተለይም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን አስረድተዋል። አነስተኛ የአርሶ አደር ቤተሰቦችን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ትክክለኛ ፍላጎታቸውን እና ሃሳባቸውን ለመረዳት የአነስተኛ ገበሬዎች የእርሻ ባሕል ሳይዘነጋ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ቤተሰብ የምግብ ስርዓቶችን ለመዘርጋት የሚያስችል አስፈላጊ አካል ነው

ቤተሰብ የምግብ ስርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዝ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ቤተሰብ የምድርን ፍሬ በአግባቡ መጠቀምን መማር የሚችል እና የደስታ ተቋሽ መሆኑን አስታውሰው፣ ቤተሰብ የግል እና የጋራ ጥቅምን የሚያከብሩ የአኗኗር ዘይቤዎችን ቶሎ ብሎ ለመቅሰም የሚችል የማኅበረሰብ ክፍል መሆኑን አስረድተዋል። ለቤተሰብ ይህ ከተመቻቸለት በገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ የድሃ እናቶች እና ወጣቶች ፍላጎት ውጤታማ የፖለቲካ ውሳኔዎችን በመከተል ምኞታቸውን ማርካት እንደሚቻል ቅዱስነታቸው አስገንዝበዋል።      

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ምኞት ማንም እንዳይገለል ነው

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ክፍል በተለይም ድሃው ማኅበረሰብ ልዩነት ሳይደረግበት በቂ ምግብ፣ ንጹሕ ውሃ፣ መድኃኒት እና የሥራ ዕድል እንዲያገኝ የማድረግ ሃላፊነት የሁሉ መሆኑን ገልጸዋል። ቅድስት መንበር እና መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እነዚህን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ፣ በቅን ፍላጎት በመነሳሳት በጥበብ የተሞሉ ውሳኔዎችን በተግባር ለመግለጽ ዝግጁ መሆናቸውን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ መልዕክታቸውውን ሲያጠቃልሉ፣ የእያንዳንዱ ግለሰብ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉለት እና በዚህም “ሰላማዊ ፣ የበለፀገ” እና በእውነት ላይ የቆመ ወንድማዊ ኅብረተሰብን መገንባት የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል።           

27 July 2021, 15:24