ፈልግ

በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በእርሻ ሥራ ላይ በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በእርሻ ሥራ ላይ   (renzo blasetti)

ሰብዓዊ ክብርን የሚያስጠብቅ ሁሉ አቀፍ የግብርና ሥርዓት ማስፈለጉ ተነገረ

በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች በግብርናው ዘርፍ በብቃት እንዲሳተፉ የማስተዋወቅ አስፈላጊነትን በማስመልከት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ እና በምግብ ፕሮግራም የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕከተኛ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ፣ በሮም ከተማ በተካሄደው የአውታረ መረብ ሴሚናር ላይ አንዳንድ ጠቃሚ ሃሳቦችን ማጋራታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሴሚናሩ ወቅት በገጠራማው አካባቢ በሚኖሩ አርሶ አደሮች መካከል ለሕይወት አስጊ የሆኑ የሥራ ዓይነቶች መኖራቸው፣ የግዳጅ ሥራ እና የወጣቶች ሥራ አጥነት በስፋት መኖሩ ተመልክቷል። እስከ አውሮፓዊያኑ 2030 ዓ. ም. ድረስ “ሰብዓዊ ማንነትን የሚያስከብር የሥራ ዕድል ለሁሉ ሰው እንዲኖር” በሚል ርዕሥ ካለፉት ቀናት ወዲህ በሮም የአውታረ መረብ ላይ ሴሚናር ሲካሄድ መቆየቱ ታውቋል። ይህን ሴሚናር በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች መሳተፋቸው ታውቋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ እና በተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ በሴሚናሩ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በገጠራማው አካባቢ በሚኖር ማኅበረሰብ ዘንድ ሰዎች ሳይገለሉ ሰብዓዊ ማንነትን በሚያስከብር የእርሻ ሥራ ላይ መሳተፍ መቻል እንዳለባቸው ገልጸው ይህን ዓላማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በማኅበራዊ አስተምህሮዋ ከፍተኛ ትኩረት የምትሰጥ መሆኑንም አስታውሰዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ አስተምህሮአቸው “ሰብዓዊ ክብር” ለሚለው ቃል ትልቅ ሥፍራን መስጠታቸውን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ፌርናንዶ ኪካ፣ የሥራ ክቡርነትን በሚገልጽ ንግግራቸው በተለይም ለወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት እና ድጋፍን መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል።  

መብትን ማስጠበቅ ትክክለኛ የሥራ አቅርቦት ሰንሰለት ይፈጥራል

ቅድስት መንበር የእርሻ ሥራን በማስመልከት ባቀረበችው አስተያየት፣ በእርሻው ዘርፍ የሰውን ልጅ ማዕከል ያደረገ ባሕልን መመስረት እና ማሳደግ መሠረታዊነት ያለው ጉዳይ መሆኑን ገልጻለች። “የሠራተኞችን መብት ማስጠበቅ ትክክለኛ የሥራ አቅርቦት ሰንሰለት ለመፍጠር ያግዛል” የሚለው የቅድስት መንበር አቋም በተለይም በአነስተኛ ገበሬዎች መካከል ማኅበራዊ አንድነትን እና መግባባትን ይፈጥራል ብሏል።

ግብርና፣ በ 2030 አጀንዳ ማዕከላዊ ሥፍራን ይዟል

ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድን በመወከል መልዕክታቸውን ያተላለፉት ዶ/ር ፌደሪካ ቼሩሊ፣ በግብርና ዘርፍ ያለው ዘላቂነት የአካባቢን ወይም ኢኮኖሚያዊ ዘላቂነትን ብቻ የሚያረጋግጥ ሳይሆን ማህበራዊ ዘላቂነትንም የሚያረጋግጥ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የግብርናው ዘርፍ በ 2030 አጀንዳው ላይ ማዕከላዊ ሥፍራን መያዙን ያስታወሱት ዶ/ር ፌደሪካ ቼሩሊ፣ ግብርና በእርግጥ እንደ ሥራ ዘርፍ ለአብዛኛው ድሃ ማኅበረሰብ የሥራ ዕድልን የሚያመቻች ነው ብለዋል።

የገጠራማ አካባቢ ወጣቶችን ማሰብ

በጣሊያን ውስጥ በሚገኙ የእርሻ ጣቢያዎች በተሰማሩት ስደተኞች ላይ የሚፈጸም የጉልበት ብዝበዛን ያስታወሱት ዶ/ር ፌደሪካ ቼሩሊ ባቀረቡት ጥሪ፣ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ለዜጎቻቸው የሥራ ዕድልን በእርሻው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሥራ ዘርፎችንም እንዲያመቻቹ እና ዕርዳታን እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በእርሻው ዘርፍም ቢሆን ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀሙ ማበረታታት፣ ከገንዘብ ተቋማት ጋር እንዲገናኙ ማድረግ እና ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲለዋወጡ ማገዝ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብርናን በማሳደግ ረገድ ሴቶች ትልቅ ሚና ይጨወታሉ

ሴቶችን የመሬት ባለቤት ማድረግ የድርጅታቸው ዓላማ እና የሥራ ድርሻ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፌደሪካ ቼሩሊ፣ በአሁኑ ጊዜ በእርሻው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ቁጥር 70 ከመቶ መሆኑን አስታውሰው ነገር ግን የእርሻ መሬት ባለቤትነት መብት ያላቸው ከ10 – 20 ከመቶ የማይበልጡ መሆኑን አስረድተዋል። ስለሆነም ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር፣ ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ሚናን እንዲጫወቱ ማበረታታት ያስፈልጋል ብለዋል።   

ትናንሽ ገበሬዎችን መደጎም

በገጠራማው አካባቢዎች የሚኖሩ ትናንሽ ገበሬዎችን ያስታወሱት ዶ/ር ፌደሪካ ቼሩሊ፣ በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎች የግብርና ሥራቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ እንዳይችሉ የሚያደርግ የድጋፍ ውስንነት መኖሩን ገልጸው፣ ትናንሽ ገበሬዎች ልምዳቸውን እና እውቀታቸውን በመጠቀም፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሉ የእርሻ ዘዴዎችን ከመከተል ይልቅ የተፈጥሮ ሃብትን በማይጎዳ መልኩ የግብርና ሥራቸውን እንዲያካሂዱ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሁሉ አቀፍ የምግብ ስርዓቶች መኖር

ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ተወካይ ዶ/ር ፌደሪካ ቼሩሊ፣ ከተለያዩ መንግሥታት መሪዎች ጋር በሚያደርጉት ውይይት፣ ከድርጅታቸው የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ለፖለቲካ ዓላማን ወይም በሌሎች ዘርፎች መዋል እንደሌለበት ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ ዕርዳታው ትናንሽ ገበሬዎችን ለማገዝ፣ ወጣቶችን፣ ስደተኞችን፣ ሴቶችን እና የአካል ጉዳተኞችን በግብርናው ዘርፍ የሚያሳትፍ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።   

14 July 2021, 12:56