ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ ልባችንን ለኢየሱስ ብርሃን እንክፈት ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እሁድ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ ምዕመናን በለቱ በሚነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በየካቲት 17/2016 ዓ.ም የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በተጀመረው የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት ላይ ከማርቆስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበውና “ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን አስከትሎ ወደ አንድ ረዥም ተራራ ይዟቸው ወጣ፤ ብቻቸውንም ነበሩ፤ በፊታቸውም ተለወጠ፤ ልብሱም በምድር ላይ ማንም ዐጣቢ ዐጥቦ ሊያነጣው በማይችልበት ሁናቴ እጅግ ነጭ ሆነ። ኤልያስና ሙሴም ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።

ጴጥሮስም ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፣ እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ አንድ ለአንተ፣ አንድ ለሙሴ፣ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች እንሥራ” አለው። እጅግ ስለ ፈሩ የሚናገረውን አያውቅም ነበር።

ከዚያም ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ፣ “ይህ የምወድደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። ወዲያውም ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንም አብሯቸው አልነበረም።

ከተራራው ላይ በሚወርዱበትም ጊዜ፣ የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያዩትን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው” በሚለው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተንተርሰው ባደረጉት አስተንትኖ ልባችንን ለኢየሱስ ብርሃን ልንከፍት ይገባል ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው እለት በተጀመረው ሁለተኛው የዐብይ ጾም እለተ ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ታምራዊ በሆነ መልኩ የኢየሱስ መልክ መቀየሩን የሚገልጽ ታሪካ ያቀርብልናል (ማር. 9፡2-10)።

ኢየሱስ ተላልፎ እንደሚሰጥ፣ እንደሚካድ እና ብዙ ፈተና እንደሚደርስበት የሚገልጸውን ሕማማቱን ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገረ በኋላ፣ ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ወጣ፣ እናም በዚያ በአካል በሙሉ በብርሃኑ ተገለጠ። በዚህ መንገድ እስከዚያች ቅጽበት ድረስ አብሮ ከነርሱ ጋር የነበረበትን ትርጉም ገልጾላቸዋል። ስለመንግሥቱ ያደረገው ስብከት፣ የኃጢአት ሥርዬት፣ ፈውሶች እና የተደረጉት ምልክቶች፣ በእርግጥም ከበለጠ የብርሃን ፍንጣሪዎች ማለትም የኢየሱስ ብርሃን፣ ኢየሱስ የሆነው የብርሃን ፍንጣሪዎች ነበሩ። እናም ከዚህ ብርሃን፣ ደቀመዛሙርቱ በተለይ በፈተና ጊዜ፣ ልክ በዚህ ጊዜ በህማማቱ ወቅት እንደተከሰተው ዓይኖቻቸውን ቀና አድረገው መመልከት አልቻሉም።

ይህ የዛሬ መልእክት ነው፣ አይኖችህን ከኢየሱስ ብርሃን ፈጽሞ አትንቀል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ገበሬዎች እርሻቸውን ሲያርሱ ይሠሩት እንደነበረው ማለት ነው፡ ከፊታቸው ባለው ልዩ ነጥብ ላይ አተኩረው ዓይኖቻቸውን እዚያው ላይ እያደረጉ መቆፈራቸውን ይቀጥላሉ።

በሕይወታችን ውስጥ በምንጓዝበት ጊዜ እንደ ክርስቲያን ልናደርገው የተጠራነው ይህንን ነው፡ የኢየሱስን አንጸባራቂ ፊት ሁልጊዜ በዓይኖቻችን ፊት እንድናይ።

ወንድሞች እና እህቶች፣ የኢየሱስን ብርሃን ለመቀበል ልባችን ክፍት ይሁን! እርሱ ፍቅር ነው፣ እርሱ ፍጻሜ የሌለው ሕይወት ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊያሰቃዩ በሚችሉ የሕይወት መንገዶች ላይ፣ በምህረት፣ በታማኝነት እና በተስፋ የተሞላ ፊቱን እንፈልግ። ይህንን ለማድረግ የሚረዳን ጸሎት፣ ቃሉንና ምስጢራትን በተለይም ምስጢረ ንስሐ እና ቅዱስ ቁርባንን ስናዘወትር፣ እርሱን ለማዳመጥ፣ ወደ እርሱ ለመጸለይ፣ ቃሉን እና ምስጢራትን ማዳመጥ ዓይኖቻችንን በኢየሱስ ላይ እንድናተኩር ይረዳናል።

ይህ ደግሞ ጥሩ የዐብይ ጾም ውሳኔ ነው፡ እንግዳ ተቀባይ አመለካከትን ማዳበር፣ "ብርሃንን ፈላጊዎች" መሆን፣ የኢየሱስን ብርሃን ፈላጊዎች በመሆን፣ በጸሎትም ሆነ በሰዎች ውስጥ የኢየሱስን ብርሃን ልንፈልግ ይገባል።

እንግዲያውስ ራሳችንን እንጠይቅ፡- አይኖቼ ከእኔ ጋር ሊጓዝ ወደሚመጣው ክርስቶስ ላይ ያተኩራሉ ወይ? እናም ይህን ለማድረግ ለዝምታ፣ ለጸሎት፣ ለስግደት ቦታ እሰጣለሁ ወይ? በመጨረሻም፣ በእኔ እና ባጋጠሙኝ ወንድሞችና እህቶች ውስጥ የሚንፀባረቀውን የኢየሱስን ትንሽ ጨረሮች እሻለሁ ወይ? እናም ለዚህም እሱን ማመስገን ትዝ ይለኛል ወይ?

በእግዚአብሔር ብርሃን የምትበራ ማርያም ይናችን በኢየሱስ ላይ እንዲያተኩር እና እርስ በርሳችን በመተማመን እና በፍቅር እንድንተያይ እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን።

26 February 2024, 09:53

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >