ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ አመስጋኞች እንድንሆን የቅድስት ማርያምን ዕርዳታ በጸሎት ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
እሁድ መስከረም 27/2016 ዓ. ም. ከማቴ. 21:33-43 ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዚህ የወንጌል ክፍል የተገለጸው የክፉ ገበሬዎች ምሳሌ፥ በወይን አትክልት ገበሬዎች አእምሮ ውስጥ የምስጋና ቢስነት እና የስግብግብነት ሃሳብ ገብቶ የሥራቸው ውጤት ወይም የእርሻው ፍሬ የራሳቸው ብቻ እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ ማድረጉን ገልጸው፥ ገበሬዎቹ አትክልቱን ተንከባክበው መከሩን ከመሬቱ ባለቤት ጋር ከመካፈል ይልቅ ሁሉንም ነገር ለራሳቸው ለማድረግ በመፈለግ የእርሻው ጌታ አገልጋዮችን በማንገላታት በመጨረሻም ልጁን እንደገደሉ አስታውሰዋል።
ምስጋና ቢስነት ወደ ሁከት ይመራል
በምሳሌ ላይ ያስተነተኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ገበሬዎቹ ከእርሻው ላገኙት የላባቸው ፍሬ እና ለተደረገላቸው አያያዝ አመስጋኖች መሆን ሲገባቸው፥ ይልቁንስ ምስጋና ቢሶች እና ስግብግቦች በመሆን በልባቸው ውስጥ የዓመፅ እና የሁከት ስሜት እየሰፋ ሄዶ ሁኔታውን በተዛባ መልኩ እንዲያዩት እንዳደረጋቸው ተናግረው፥ ከእርሻው እንዲጠቀሙ ዕድል የሰጣቸውን የእርሻውን ጌታ የባለ ዕዳነት ስሜት እንዲሰማው ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም የእርሻው ሠራተኞች ከመሆን ይልቅ ነፍሰ ገዳይ ሆነው መገኘታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረው፥ ቀጥለውም በዚህ ምሳሌ አማካይነት ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሰው ሌሎች ያደረጉለትን ዕርዳታ በሚዘነጋበት ወቅት እና በከንቱ ሃሳብ ሲታለል ምስጋና ቢስ እንደሚሆን ለማስታወስ መፈለጉን አስረድተዋል። ምስጋና ቢስነት ባገኙት ወደ አለመርካት፣ ወደ አለመግባባት ወደ ቂመኝነት እና በመጨረሻም ሁከትን እንደሚያስነሳ በመግለጽ፥ ምስጋና ቢስነት ዓመፅን እንደሚፈጥር እና ምስጋናን ማቅረብ ግን ሰላምን መልሶ ሊያመጣ እንደሚችል ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።
'አመሰግናለሁ' ማለትን መማር
ሕይወታችን እና እምነታችን፣ ሁለመናችን እና የራሳችን የምንለው ነገር በሙሉ ከእግዚአብሔር ጸጋ የተገኙ መሆናቸውን ከተገነዘብን፥ እግዚአብሔርን ለጸጋው ምስጋናን እንድናቀርብ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋብዘውናል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ መስከረም 27/2016 ዓ. ም. ያቀረቡትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በጸሎት ሲያጠቃልሉ፥ በነፍሷ እግዚአብሔርን ያከበረች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ ልባችን ውስጥ በየቀኑ በሚበራው ብርሃን አማካይነት ዘወትር አመስጋኞች እንድንሆን እንድታግዘን በመለመን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከምዕመናን ጋር በኅብረት ያቀረቡትን የመልአክ እግዚአብሔር ጸሎት አጠናቀዋል።