ፈልግ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ  

ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የዩክሬን የሰላም ተልዕኮ ለማሳካት ወደ ዋሽንግተን መጓዛቸው ተገለጸ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከሐምሌ 10-12 /2015 ዓ. ም. ድረስ ለሥራ ጉብኝት ወደ አሜሪካ መዲና ዋሽንግተን ተጉዘዋል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ዋሽንግተን ያደረጉት ጉዞ ዋና ዓላማ በዩክሬን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት በሚያስከትለው አስከፊ አደጋዎች ላይ ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን ለመለዋወጥ በተለይም አቅመ ደካማ በሆኑት ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ስቃይ ለመቅረፍ እና ሰብዓዊ እርምጃዎችን ለመደገፍ ያለመ እንደሆነ ቅድስት መንበር አስታውቃለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ በመሆን ከዚህ በፊት ወደ ሁለቱ አገራት ማለትም ወደ ዩክሬይን እና ሩስያ በመሄድ የሰላም ጥረት ማድረጋቸው የሚታውስ ሲሆን፥ ጥረታቸውን አሁንም በመቀጠል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመወከል ወደ አሜሪካ የተጓዙት በስቃይ ውስጥ በምትገኝ የምሥራቅ አውሮፓ አገር ዩክሬይን ውስጥ ያለውን ጦርነት እና ውጥረት ለማቃለል እንደሆነ ታውቋል።

በሰብዓዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ ያሉ ጥረቶችን መደገፍ

የቅድስት መንበር መግለጫ እንዳረጋገጠው፥ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ዋሽንግተንን የሚጎበኙት በዩክሬይን ሰላምን ለማስፈን ከታቀደው ተልዕኮ አንፃር መሆኑን ገልጾ፥ በወቅታዊው አሳዛኝ ሁኔታዎች ላይ ተወያይተው ሃሳቦችን እና አስተያየቶችን ለመለዋወጥ እና ለጦርነት አደጋ ለተጋለጡት በተለይም በሕጻናት ላይ የሚደርሱ አስከፊ አደጋዎችን ለመቅረፍ የሚደረጉ ሰባዓዊ ጥረቶችን ለመደገፍ ያለመ እንደሆነ መግለጫው አስታውቋል። እንደ ቀደሙት የሰላም ተልዕኮዎች ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ዋሽንግተን የተጓዙት ከቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ባለስልጣን ጋር መሆኑን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።

የከዚህ በፊት ተልዕኮዎች

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከዚህ በፊት ከግንቦት 28-29/2015 ዓ. ም. ድረስ በኪዬቭ ከዩክሬይኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው በሰላም ጥረት ላይ መወያየታችው ሲታወስ፣ ቀጥለውም በሞስኮ ከሰኔ 21 – 22/2015 ዓ. ም. ድረስ ባደረጉት ጉብኝት ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ኪሪል ጋር ዩክሬይን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እና ውጥረት የሚረግብበትን የሠላም መንገድ ተወያይተው መመለሳቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ሁለቱ አገራት ያደርጉትን የሰላም ተልዕኮ በማስመልከት ቅድስት መንበር በግንቦት ወር 2015 ዓ. ም. መግለጫ መስጠቷም ይታወሳል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እንዳብራሩት፥ የካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ተልዕኮ ዓላማ የሽምግልና ጥረቶችን ቶሎ ለመጀመር ሳይሆን ነገር ግን ከሁሉም በላይ ለሰላም ጥረቶች ምቹ የሚሆኑ መንገዶችን ለመደገፍ መሞከር እና ወደ ሰላም ጎዳና ሊያመሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በሮም ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ እንደተናገሩት፥ የቅድስት መንበር ተነሳሽነት ከሩሲያ እና ዩክሬን በተጨማሪ እንደ አሜሪካ እና ቻይና ከመሳሰሉት ሌሎች አገራት ጋር የሚደረግ የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚችል መግለጻቸውም ይታወሳል።

ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ኪዬቭ ያደረጉት ጉዞ

ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ከግንቦት 28-29/2015 ድረስ በነበራቸው ቆይታ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ፣ ከዩክሬይን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ከሆኑት አቶ ዲሚትሮ ሉቢኔትስ እና እንዲሁም ከአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት አባላት እና የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር ውይይቶችን አካሂደው መመለሳቸው ይታወሳል። “የእነዚህ ውይይቶች ውጤት በሰብዓዊነት ደረጃ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሚያግዙ መንገዶችን ለመፈለግ እና የሚወሰዱ እርምጃዎችንም ለመገምገም እንደሚያግዝ ጥርጥር የለውም” በማለት ቫቲካን ማስታወቋ ይታወሳል።

ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሞስኮ ያደረጉት ጉብኝት

ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከዩክሬይን ቀጥለው በሞስኮ ያደረጉት የሦስት ቀናት ጉብኝት የተለያዩ ስብሰባዎችን ያካሄዱበት እንደነበር ይታወሳል። ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባይገናኙም ነገር ግን ከሩሲያ ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የፕሬዝዳንቱ ረዳት ከሆኑት ዩሪ ኡሻኮቭ እና በሩሲያ ፌዴሬሽን የሕፃናት መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ማርያ ሎቮቫ-ቤሎቫ ጋር ረጅም ውይይት አድርገው መመለሳቸው ይታወሳል። ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሁለቱ አገራት ውስጥ ያደረጓቸው ውይይቶች የሰላም ጥረቱ ሰብዓዊ ገጽታን እና የሚፈለገውን ሰላም ለማስፈን የሚያስችል መሆን አለበት የሚል እንደ ነበር ታውቋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ተልዕኮዋቸውን የጀመሩት በቭላድሚር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል ፊት ቆመው ባቀረቡት ጸሎት እንደነበር ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በተጨማሪም ቅድስት መንበር ሰላማዊ መፍትሄን ሊያመቻች ይችላል ያለችውን ፍሬያማ ስብሰባ ከሞስኮ እና ከመላው ሩስያ ፓትርያርክ ከሆኑት ከብፁዕ ወቅዱስ ኪሪል ጋር በማድረግ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሰላምታ አድርሰው መመለሳቸው ይታወሳል።  ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሩሲያ በነበራቸው የ72 ሰዓታት ቆይታ ከሩሲያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ እና ከካህናት ማኅበራት ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ቀጥለውም ከአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አባላት እና የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች ጋርም መገናኘታቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ በተጨማሪም በሞስኮ በሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ካቴድራል ውስጥ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት መምራታቸው ይታወሳል።

ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉት ውይይት

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዩክሬይን እና በሞስኮ ካደረጓቸው ጉብኝቶች ተመልክሰው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ በሮም የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ መሥራች የሆኑት አቶ አንድሪያ ሪካርዲ ባሳተሙት አዲስ መጽሐፍ የምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ በኪዬቭ እና በሞስኮ ባደረጓቸው የመጀመሪያ ዙር የሰብዓዊነት ተልዕኮ ወቅት የተወሰዱ እርምጃዎችን በማስመልከት ገለጻ አድርገዋል። ከሰላም ተልዕኮዋቸው መልስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸውን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በተልዕኮዋቸው መካከል ቅድሚያ የተሰጠበት ጉዳይ ሕፃናትን እና ሌሎች ችግር ውስጥ የወደቁትን ሰዎችን መርዳት መሆኑን አስምረውበታል። ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ለሰላም ያላቸውን ተስፋ በገለጹበት ንግግራቸው፥ የሰላም ጥረታቸው ለሕጻናት ከሚደረግ ዕርዳታ እንደሚጀምር ገልጸው፥ ሩስያ ውስጥ የሚገኙ የዩክሬይን ሕጻናትን ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀው፣ ቀጣዩ የሰላም ጥረታቸው በዩናይትድ ስቴትስ መዲና ዋሽንግተን ውስጥ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

 

18 July 2023, 17:07