ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ በኪዬቭ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ጋር ውይይት ሲያካሂዱ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ በኪዬቭ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ጋር ውይይት ሲያካሂዱ  

ካርዲናል ማቴዎ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ ሆነው ወደ ሞስኮ እንደሚጓዙ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑትን ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒን የሰላም መልዕክተኛ በማድረግ ወደ ሞስኩ እንደሚልኩ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሞስኮ ያላቸው ተልዕኮ በሩስያ እና በዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ለሚገኘው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄን ለማግኘት የሚደረገውን የውይይት ጥረት ለማበረታታት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ማክሰኞ ሰኔ 20/2015 ዓ. ም. ይፋ እንዳረጋገጠው፣ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና በጣሊያን የቦሎኛ ከተማ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ወደ ሞስኮ የሚጓዙት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክተኛ በመሆን መሆኑን አስታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሞስኮ የሚቆዩት ከሰኔ 21 – 22/2015 ዓ. ም. እንደሆነ መግለጫ ክፍሉ አስታውቆ፥ የተልዕኮአቸው ዓላማም በሩስያ እና በዩክሬን መካከል ለሚታየው አሳዛኝ ሁኔታ መፍትሄን በመስጠት ወደ ፍትሃዊ ሰላም የሚያመሩበትን መንገድ ለማግኘት የሚረዱ ምልክቶችን ለማጠናከር መሆኑን መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።

የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ልኡካንን በመምራት ወደ ሞስኮ የሚጓዙት ብጹዕ ካርዲናል መቴዎ ዙፒ ሞስኮን በሚጎበኙበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ በአውሮፓ አህጉር ውስጥ ለሚካሄደው ጦርነት እልባት ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት እንደሚገልጹ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዓለም መሪዎች እና ግለሰቦች ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ ያለማቋረጥ የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል። በዩክሬን ውስጥ ከሩስያ የጦር ኃይል ጋር እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ በማለት በርካታ የሰላም ጥሪዎችን እና የጸሎት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም ወደ ኪዬቭ የተደረገው ጉብኝት

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከሰኔ 21 – 22/2015 ዓ. ም. ድረስ በሞስኮ የሚያደርጉት የሰላም ተልዕኮ ከዚህ በፊት ከዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ከግንቦት 28-29/2015 ድረስ በኪዬቭ ያደረጉት ጉብኝት ቀጣይ እንደሚሆን ታውቋል። ብፁዕ ካርዲናል ማቴው ዙፒ ከዩክሬን ከፍተኛ የመንግሥት ተወካዮች ጋር በኪዬቭ ውስጥ ባደረጉት ስብሰባው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዩክሬን ሕዝብ ያላቸውን አሳቢነት መግለጻቸው ይታወሳል።

ካርዲናሉ ከባለሥልጣናቱ ጋር ባደረጉት ውይይት የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት ለውይይት ቅድሚያ እንዲሰጡ እና ለጦርነቱ ፍትሃዊ መፍትሄ የጋራ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት መስጠታቸው ይታወሳል።ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አቶ ዘሌንስኪ ጋር የተደረገው ውይይትም የሕዝቡን ስቃይ ማቃለል፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመንን መልሶ መገንባት እና ወደ እርቅ ለመድረስ በሚያግዙ እርምጃዎች ላይ ለመወያየት ዕድል መስጠት እንደሚያስፈልግ የሚጠቁም እንደነበር ይታወሳል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒም በውይይታቸው ቫቲካን በዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እና በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ዕርምጃዎች እገዛን ለማድረግ ያላትን ዝግጁነት በድጋሚ ገልጸዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከሰኔ 21-22/2015 ዓ. ም. ድረስ በሞስኮ ቆይታቸው ቅድስት መንበር በሰላም ግንባታ ጥረቶች ላይ በንቃት ለመሳተፍ እና ሰላምን በመወከል ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ለመተባበር ያላትን ቁርጠኝነት ለማጉላት እንደሚፈልጉ ታውቋል።

27 June 2023, 16:29