ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥  

ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ የዩክሬይን ሕጻናትን ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታወቁ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክተኛ ሆነው ከሰኔ 21-22/2015 ዓ. ም. ድረስ ሞስኮን ጎብኝተው የተመለሱት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ ሩስያ ውስጥ የሚገኙ የዩክሬይን ሕጻናትን ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዩክሬይን መዲና ኪዬቭ እና በሞስኮ ካደረጉት ጉብኝታቸው መልስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ በሮም የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ መሥራች የሆኑት አቶ አንድሪያ ሪካርዲ ሰላምን በማስመልከት ባሳተሙት አዲስ መጽሐፍ የምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይም ተገኝተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በመጽሐፉ የምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በኪዬቭ እና በሞስኮ ባደረጓቸው የመጀመሪያው የሰብዓዊ ተልዕኮ ወቅት የተወሰዱ እርምጃዎችን በማስመልከት ገለጻ አድርገዋል።

በዩክይሬን መዲና ኪዬቭ እና በሞስኮ ካደረጓቸው ጉብኝቶች ሲመለሱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸውን የገለጹት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቦሎኛ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ አንድሪያ ሪካርዲ ካሳተሙት አዲስ መጽሐፍ የምርቃ ሥርዓት ቀደም ብሎ ሮም በሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ባደረጉት ቆይታ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በዚህ ወቅትም በዩክሬይን መዲና ኪዬቭ እና በሞስኮ ካደረጉት ጉብኝታቸው መልስ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ካርዲናሉ ወደ እነዚህ ሁለቱ አገራት ባደረጓቸው ጉዞ ወቅት ቅድሚያን በመስጠት የተወያዩበት ቀዳሚ ርዕሥ፥በጦርነቱ ምክንያት በጣም ለተቸገሩት እና በሩሲያ ለሚገኙ የዩክሬይን ሕጻናት ሰብዓዊ ዕርዳታን ማድረስ በሚቻልበት ስልት ላይ እንደነበር አስረድተዋል። “ሩስያ ውስጥ የሚገኙ ሕጻናት ወደ ትውልድ አገራቸው ዩክሬይን መመለስ መቻል አለባቸው” ያሉት ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ “የሚቀጥለው እርምጃ በመጀመሪያ ልጆቹ የሚገኙበትን ሁኔታ መመልከት፣ ከዚያም እንዴት ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ማጤን ነው” ብለዋል።

በመጽሐፉ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የታሪክ ተመራማሪ፣ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ፕሬዚዳንት እና እንዲሁም ጋዜጠኛ አቶ ማርኮ ዳሚላኖ፣ ፕሮፌሰር ጁሴፔ ዴ ሪታ እና ፕሮፌሰር ዶናቴላ ዲ ቼዛሬ መገኘታቸው ታውቋል። ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ አቶ አንድሪያ ሪካርዲ ሰላምን በማስመልከት የጻፉት አዲሱ መጽሐፍ የምንኖርበትን ጊዜ በማስገንዘብ ጠቃሚ እገዛን እንደሚያበርክት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በማከልም፥ አዲሱ መጽሐፍ ውስብስብነት ያለባቸውን የጦርነት መፍትሄዎች ለመፈለግ እገዛ እንደሚያደርግ፣ “እንዲያውም ጦርነት ዘወትር የሁሉም ወገን ሽንፈት ነው” ሲሉ አክለዋል። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ሰዎች ከግለኝነት አስተሳሰብ ወጥተው የጋራ ሕይወትን የሚለማመዱበት መንገድ ማሳየትን ማወቅ ይኖርባታል ብለዋል።

የመጽሐፉ ደራሲ እና የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ መሥራች አቶ አንድሪያ ሪካርዲ፥ “ሰላም ምን እንደሆነ ማሰብ ያለብን ጊዜ አሁን ነው” ብለው፣ ጦርነት አስከፊ መዘዞችን በማስከተል የሰዎችን ጠቅላላ ሕይወት ወደ ገደል ይከታል ብለዋል። አቶ አንድሪያ ሪካርዲ አክለውም፥ ሰዎች ለጦርነት ያላቸው ፍርሃት እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸው፣ “ትልቁ ችግር ለጦርነት የነበረንን አስፈሪ ስሜት እና ለሰላም የነበረንን ተነሳሽነት እንደገና መልሶ ማግኘት ነው” ብለዋል። የሰላም ጥረት የት እንደሚገኝ የጠየቁት አቶ አንድሪያ ሪካርዲ፥ በአሁኑ ወቅት በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ በርካታ የሰላም ጥረቶች አልፎ አልፎ እንደሚታዩ ጠቁመው፥ “በእነዚህ የሰላም ጥረቶች በመታገዝ ማኅበረሰብን እና ብዝሃነትን እንደገና ለመገንባት ተጠርተናል" ብለዋል።

በፖለቲካው አቅጣጫ መልካም አስተሳሰቦች እና ሰፋ ያሉ ዕይታዎች ያስፈልጉናል ያሉት አቶ አንድሪያ ሪካርዲ፥ በዲፕሎማሲው ላይ ሰፊ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባ፣ የጦርነትን አስከፊነት በሚገባ ለመረዳት ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት እና ናዚዎች በአይሁዳዊያን ላይ የፈጸሙትን የጭካኔ ተግባር በማስታወስ የሠላም ባሕልን ማሳደግና ይህ ባሕል በሕዝቡ መካከል እንዲስፋፋ ማድረግ አለብን ብለዋል።

05 July 2023, 16:15