ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ቅድስት ሥላሴ የሚያስተምረን አንዳችን ከሌላው ተለይቶ ፈጽሞ መኖር እንደማይችል ነው አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት በቫቲካን በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚሰበሰቡ መዕመናን በእለቱ በሚነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሰኔ 05/2014 ዓ.ም ያደረጉት አስተንትኖ በወቅቱ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የተከበረውን የቅድስት ሥላሴ በዓል ላይ መሰረቱን ያደረገ አስተንትኖ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን ቅድስት ሥላሴ የሚያስተምረን አንዳችን ከሌላው ተለይቶ ፈጽሞ መኖር እንደማይችል ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በእለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል

“ብዙ የምነግራችሁ ነበረኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም። የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።” (ዮሐንስ 16፡12-15)

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ፣ መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ!

ዛሬ የቅድስት ሥላሴ ክብረ በዓል እየተከበረ ሲሆን በበዓሉ ላይ ተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ ኢየሱስ ሌሎቹን ሁለት መለኮታዊ አካላት አብ እና መንፈስ ቅዱስ አቅርቧል። ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር፡- “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል። እርሱ ከራሱ አይናገርም፤ የሚሰማውን ብቻ ይናገራል፤ እንዲሁም ወደ ፊት ስለሚሆነው ይነግራችኋል፤ 14የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ በማድረግ ያከብረኛል። የአብ የሆነው ሁሉ የእኔ ነው፤ እንግዲህ፣ ‘የእኔ ከሆነው ወስዶ እንድታውቁ ያደርጋል’ ያልኋችሁ ለዚሁ ነው።” (ዮሐ 16፡13-15) ይላል። መንፈስ ቅዱስ ይናገራል ነገር ግን የሚናግረው ስለራሱ እንዳልሆነ እናስተውላለን፡ ኢየሱስን ያውጃል አብንም ይገልጣል። ደግሞም ሁሉን የያዘው እርሱ የሁሉ መነሻ ስለሆነ አብ ያለውን ሁሉ ለወልድ እንደሚሰጠው እናስተውላለን፤ ለራሱ ምንም አይጠብቅም ራሱንም ሙሉ ለሙሉ ለወልድ ይሰጣል። ወይም ይልቁንስ መንፈስ ቅዱስ ስለ ራሱ አይናገርም፣ ስለ ኢየሱስ ተናግሯል ስለ ሌሎችም ይናገራል። አብም ራሱን አይሰጥም ወልድን ይሰጣል እንጂ። አንዱ ለሌላው ክፍት የሆነ ልግስና ነው።

እናም አሁን ስለምንነጋገርበት እና ያለንን እራሳችንን እንመልከት። ስንናገር ሁል ጊዜ ስለራሳችን ጥሩ ነገር መናገር እንፈልጋለን፣ እናም ብዙ ጊዜ፣ ስለራሳችን እና ስለምናደርገው ነገር ብቻ ነው የምንናገረው። "ይህን እና ያንን አድርጌያለሁ..."፣ "ይህ ችግር አጋጥሞኝ ነበር..." እያልን ሁሌም እንደዚህ እንናገራለን። ይህ ሌሎችን በማወጅ ከሚናገረው ከመንፈስ ቅዱስ እና ከአብ ከወልድ ምንኛ የተለየ ነው! እናም ባለን ነገር ምን ያህል እንቀናለን። ያለንን ነገር ለሌሎች ሌላው ቀርቶ በመሠረታዊነት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለሌላቸው ማካፈል ምንኛ ከባድ ነው! ስለ እሱ ማውራት ቀላል ነው፣ ነገር ግን እሱን መተግበር አስቸጋሪ ነው።

ለዚህም ነው ቅድስት ሥላሴን ማክበር ሥነ-መለኮታዊ ልምምድ ሳይሆን በሕይወታችን ውስጥ አብዮት መፍጠር ማለት ነው። እግዚአብሔር እያንዳንዱ ሰው ለሌላው የሚኖረው ቀጣይነት ባለው ግንኙነት፣ ቀጣይነት ባለው ትብብር፣ ለራሱ ሳይሆን፣ ከሌሎች እና ከሌሎች ጋር እንድንኖር ያነሳሳናል። ለሌሎች ራሳችንን እንድንከፍት ያደርገናል። ዛሬ ህይወታችን የምናምነውን አምላክ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፡ እኔ በእግዚአብሔር አብ እና ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ላይ እምነት እንዳለኝ የምለው እኔ በእውነት ሌሎች እንዲኖሩኝ እንደሚያስፈልገኝ አምናለሁ፣ ራሴን ለሌሎች አሳልፌ መስጠት አለብኝ? ሌሎችን ማገልገል አለብኝ? ይህንን በቃላት አረጋግጣለሁ ወይንስ በህይወቴ አረጋግጣለሁ?

አንድ እና ሦስት አምላክ፣ ውድ ወንድሞች እና እህቶች በዚህ መንገድ መገለጥ አለባቸው - ከቃላት ይልቅ በተግባር መታየት አለበት። የሕይወት ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር በመጽሐፍት ሳይሆን በሕይወት ምስክሮች ይተላለፋል። ወንጌላዊው ዮሐንስ እንደጻፈው “ፍቅር ነው” (1ኛ ዮሐ. 4፡16) ራሱን በፍቅር የሚገልጥ ነው። ስላገኛናቸው ጥሩ፣ ለጋስ፣ የዋህ ሰዎች እናስብ። የአስተሳሰብ እና የአተገባበር መንገዳቸውን ስናስታውስ፣ ትንሽ የእግዚአብሔር-ፍቅር ነጸብራቅ ሊኖረን ይችላል። እናም መውደድ ማለት ምን ማለት ነው? ለእነርሱ መልካምን ለመመኘት እና ለእነርሱ መልካም ለመሆን ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በፊት ከሥሩ ሌሎችን ለመቀበል ለሌሎች ክፍት መሆን ለሌሎች ቦታ መስጠት፣ ለሌሎች በሕይወታችን ቦታ መስጠት፣ ከሥር መሰረታቸው አንስቶ መውደድ ማለት ይህ ነው።

ይህንን የበለጠ ለመረዳት የመስቀል ምልክትን በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ የምንጠራቸውን የመለኮታዊ አካላትን ስም እናስብ፣ እያንዳንዱ ስም የሌላውን መገኘት ይዟል። አብ ለምሳሌ ያለ ወልድ እንዲህ አይሆንም ነበር፣ እንዲሁም ወልድ ሁልጊዜ እንደ አብ ልጅ እንጂ ብቻውን ሊቆጠር አይችልም። መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በበኩሉ የአብና የወልድ መንፈስ ነው። ባጭሩ ሥላሴ የሚያስተምረን አንዱ ከሌላው በቀር ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ነው። እኛ ደሴቶች አይደለንም፣ በአለም ውስጥ ነን በእግዚአብሔር አምሳል ለመኖር፡ ክፍት ለመሆን፣ ሌሎችን እንፈልጋለን እና ሌሎችን መርዳት ያስፈልገናል። እናም ስለዚህ እራሳችንን ይህን የመጨረሻ ጥያቄ እንጠይቅ፣ በዕለት ተዕለት ሕይወት፣ እኔም የሥላሴ ነጸብራቅ ነኝ ወይ? በየቀኑ የማማትበው የመስቀል ምልክት - አብ እና ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ - በየቀኑ የምናደርገው የመስቀሉ ምልክት ለራሱ ሲል ምልክት ነው ወይንስ የእኔን የንግግር ፣ የመገናኘት መንገድ ያነሳሳል? ምላሽ መስጠት፣ መፍረድ፣ ይቅር ባይነት ነዚህ ነገሮች በሕይወቴ ይታያሉ ወይ?

የአብ ልጅ የወልድ እናት የመንፈስ ባለቤት የሆነች እመቤታችን በሕይወታችንም የእግዚአብሔርን ፍቅር ምስጢር እንድንቀበል እና እንድንመሰክር በአማላጅነቷ እርሷ ትርዳን።

12 June 2022, 12:03

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >