ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ መሪነት የተመረጡበትን ዕለት በጸሎት ሲያስታውሱት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ለሐዋርያዊ መሪነት የተመረጡበትን ዕለት በጸሎት ሲያስታውሱት 

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሰኔ እና የሐምሌ ወራት ሐዋርያዊ ተግባራት መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሰኔ እና በሐምሌ ወራት የሚፈጽሟቸውን ሐዋርያዊ ተግባራት መርሃ ግብር የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዓርብ ግንቦት 26/2014 ዓ. ም. ይፋ አድርጓል። ቅዱስነታቸው በሮም ከሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. በሚካሄደው 10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ፣ ከሰኔ 25-30/2014 ዓ. ም. ድረስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ፣ ቀጥለውም ከሐምሌ 17 – 23/2014 ዓ. ም. ድረስ በካናዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍሉ፣ ከሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. በሮም የሚካሄደውን 10ኛ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደሚመሩት ገልጾ፣ በጉባኤው ላይም በመላው ዓለም ከሚገኙ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች እና የቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ተወካዮች እንደሚገኙ አስታውቋል። በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የሦስት ቀናት ጉባኤ እንደሚካሄድ እና ቅዳሜ ሰኔ 18/2014 ዓ. ም. በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ በ11:15 ላይ የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እንደሚመሩ አስታውቋል።      

የሮም ከተማ ባልደረባ የሆኑት ቅዱሳን፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓልን ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር ሆነው ሰኔ 22/2014 ዓ. ም. የሚያከብሩት ሲሆን፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ የሚጀምረውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሚመሩት መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።

ወደ አፍሪካ እና ካናዳ የሚያደርጉት ጉዞ 

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሰኔ 25-30/2014 ዓ. ም. ድረስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን፣ ቀጥለውም ከሐምሌ 17 – 23/2014 ዓ. ም. ድረስ በካናዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። ቅዱስነታቸው ሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ወደ ሁለቱ የአፍሪካ አገሮች ማለትም በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት 37ኛው ዓለም ው ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እንደሚሆን መግለጫ ክፍሉ ገልጾ፣ በኮንጎ ጉብኝታቸው ወቅት የአገሪቱ ዋና ከተማ ኪንሳሻን እና በሰሜን-ኪቩ ግዛት የምትገኝ ጎማ ከተማ እንደሚጎበኙ፣ በደቡብ ሱዳንም የአገሪቱ ዋና ከተማ ጁባን በመጎብኘት፣ ከአገራቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከወጣቶች እና በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢዎቻቸው ከተፈናቀሉ ቤተሰቦች ጋር እንደሚገናኙ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን መርሃ ግብር ዋቢ በማድረግ ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል።      

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከሐምሌ 17 – 23/2014 ዓ. ም. ድረስ በካናዳ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ያስታወቀው የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ፣ በካናዳ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት የአገሪቱ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የጀመረችው የእርቅ ጥረት አካል መሆኑን ገልጾ፣ በዚህ ጥረት በመታገዝ እውነትን ለማግኘት በሚወሰዱ እርምጃዎች አማካይነት፣ ያለፉ ቁስሎችን በመፈወስ እና እርቅን በማውረድ ከአገሩ ቀደምት ነዋሪዎች ጋር ያለውን የባሕል እና የማኅበራዊ ሕይወት ግንኙነት ለማሳደግ፣ የፍቅር እና እርስ በእርስ የመከባበር ባሕልን ለማሳደግ መሆኑን መግለጫ ክፍሉ ገልጾ፣ ቅዱስነታቸው በካናዳ ጉዞአቸው ወቅት ኤድመንተንን፣ ኪቤክን እና ኢቃሉይትን እንደሚጎበኙ አስታውቋል።      

04 June 2022, 16:21