ፈልግ

10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ በሮም ከሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. 10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ በሮም ከሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም.   (ANSA)

የቤተሰብ ፍቅር ፣ መለኮታዊ ጥሪ እና የቅድስና ምንጭ መሆኑ ተገለጸ

ከቤተሰብ ፍቅር የሚገኝ ጥሪ እና ቅድስና በሚል ርዕሥ የሚከበር 10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ በሮም ከሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. እንደሚካሄድ ታውቋል። ከፌስቲቫሉ መክፈቻ በኋላ በቫቲካን በሚገኝ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሦስት ቀናት ጉባኤ እንደሚካሄ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በጉባኤው መጨረሻ ማለትም ቅዳሜ ሰኔ 19/2014 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል። በዚህ 10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል ቀናት ውስጥ ዩክሬንን ጨምሮ ከብዙ አገራት የሚመጡ ቤተሰቦች ምስክርነታቸውን የሚሰጡበት መድረክ መዘጋጀቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫል በማስመልከት፣ በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ በቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ምክትል ዋና ጸሐፊዋ በመግለጫቸው፣ ፌስቲቫሉ በሮም ከሰኔ 15 – 19/2014 ዓ. ም. እንደሚካሄድ ገልጸው፣ ከፈስቲቫሉ መክፈቻ በኋላ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሦስት ቀናት ጉባኤ እንደሚካሄድ አስታውቀው፣ ከዩክሬን የሚመጡ ምዕመናንን ጨምሮ ሁለት ሺህ የቤተሰብ ልኡካን ፌስቲቫሉን እንደሚካፈሉት እና ምስክርነታቸውንም የሚሰጡበት ዕድል መመቻቸቱን ገልጸዋል።

የፈስቲቫሉ ርዕሦች

የምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ገብርኤላ ጋምቢኖ በመግለጫቸው፣ በሦስቱ የጉባኤው ቀናት ውስጥ በቤተሰብ እና በጋብቻ ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ በተሰማሩት ሰዎች መካከል እርስ በእርስ የመገናኛ፣ የመደማመጫ እና የማነጻጸሪያ ሰፊ ጊዜ እንደሚኖር ገልጸዋል። ወደ አምስት የሚጠጉ ዋና ዋና የመወያያ ርዕሠ ጉዳዮች በሚቀርቡበት በዚህ ጉባኤ ላይ ወደ ሠላሳ የሚጠጉ የውይይት መድረኮች እና ወደ ስልሳ የሚጠጉ ተናጋሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ ከሚቀርቡ አንዳንድ ዋና ዋና ጭብጦች መካከል፥ በቤተ ክርስቲያን የቤተሰብ ሐዋርያዊ እንክብካቤ መካከል የባለትዳሮች እና የካህናት የጋራ ኃላፊነት፣ በዛሬው ማኅበረሰብ ውስጥ አንዳንድ ተጨባጭ የሆኑ የቤተሰብ ችግሮች፣ የጋብቻ ሕይወት ዝግጅት፣ በቤተሰብ ሕይወት መካከል የሚንጸባረቁ አንዳንድ አዳዲስ ክስተቶች፣ ተግዳሮቶች እና አስቸጋሪ ጥያቄዎች በሚገኙበት የቤተሰብ ሐዋርያዊ አገልግሎት ውስጥ የቤተሰብ ሕይወት አስተማሪዎችን ማዘጋጀት የሚሉ ርዕሦች ይገኙባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን እና ሲኖዶሳዊነት፣ በወጣቶችና በአረጋውያን መካከል ላለው ግንኙነት ትኩረትን መስጠት፣ የቤተሰብ የፍቅር ሕይወትን ሊያጋጥም የሚችል ፈተና፣ የጋብቻ መፍረስ እና ይቅርታን ማድረግ የሚሉ ጉዳዮች በውይይቱ ከሚነሱ ርዕሦች መካከል እንደሆኑ ታውቋል።

ሰፊ እና ጥልቅ የውይይት ርዕሦች ያሉት 10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ፌስቲቫሉ፣ የአባትነት እና የእናትነት ሚና፣ የጉዲፈቻ እና የማደጎ እንክብካቤ እንደ ክርስቲያናዊ ምርጫ፣ በማንኛውም ሁኔታ መካከል ሕይወትን እንዴት መቀበል፣ መንከባከብ እና ማሳደግ እንደሚቻል ማወቅ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚካሄድባቸው ታውቋል። በክርስቲያን ቤተሰብ ተልዕኮ እውቀት ውስጥ ዲጂታሉ ዓለም በቤተሰብ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ፣ ስደት፣ ጎጂ ሱሶች፣ ዓመጽ እና ሥነ ፆታ የሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል። በሁለት የተለያዩ እምነቶች መካከል በሚፈጸም የትዳር ሕይወት ውስጥ ሊቀርብ የሚችል መንፈሳዊ ድጋፍ የሚለውም ከመወያያ ርዕሦች መካከል አንዱ እንደሚሆን ታውቋል።

የቤተሰብ አንድነት ከቤተ ክርስቲያን የአንድነት ዘይቤ አንዱ ነው

በጉባኤው አውድ ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል ሁለቱ በሮም ከተማ በሚገኙ ቁምስናዎች ውስጥ ለውይይት የሚቀርብ ሲሆን፣ ይህም የቤተ ክርስቲያንን የአንድነት ዘይቤ የተከተለ የቤተሰብ አንድነት እና ሁለተኛ ዝግጅት ከቅዱስ ቁርባን ቡራኬ ሥነ ሥርዓት ጋር የሚቀርብ የጉባኤው ተካፋዮች የአስተንትኖ ጊዜ እንደሆነ መርሃ ግብሩ አመልክቷል። የጉባኤው ቀናትም በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በቅድስት መንበር የምእመናን፣ የቤተሰብ እና የሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት በሆኑት በብፁዕ ካርዲናል ኬቪን ፋረል እና በብጹዕ ካርዲናል ደ ዶናቲስ የሮም ሀገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ በሚመሩ የቅዳሴ ጸሎት የሚጀምሩ መሆኑን የጉባኤው መርሃ ግብር አክሎ አስታውቋል።

በቤተሰብ ፌስቲቫል ላይ የሚቀርቡ ምስክርነቶች

ከ10ኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ዓላማዎች መካከል አንዱ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ያሉ አምስት ጥሪዎችን በድጋሚ ለዓለም ማስገንዘብ ሲሆን እነርሱም፥ ለጋብቻ ሕይወት፣ ለቅድስና፣ ለይቅርታ፣ አንዱ ሌላውን ለመቀበል እና ለወዳጅነት መጠራትን ማስገንዘብ መሆኑ ታውቋል። እነዚህን የጥሪ መንገዶችን የተከተሉ የቤተሰብ አባላት በጉባኤው መካከል የሕይወት ምስክርነታቸው እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ እምነትን ለልጆቻቸው የማስተላለፍ ልምድን፣ ከወላጅ ቤተሰብ ባገኙት እምነት እየታገዝ ቆይተው በሞት ከተለዩአቸው በኋላ ዛሬ ለቅድስና የሚዘጋጁ ልጆች እንዳሉ፣ በቤተሰብ መካከል ለተፈጠረው ከባድ ችግር ይቅርታን በመደራረግ ወደ መደበኛው ሕይወት የተመለሰ ቤተሰብ፣ ጦርነትን ሸሽተው የሚሰደዱትን በቤቱ ተቀብሎ ያስተናገደ ቤተሰብ፣ የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉ ባለትዳሮች እምነታቸውን በማስመልከት ያደረጉትን ውይይት የሚያስታውስ የቤተሰብ ሕይወት ምስክርነቶች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ዓለም አቀፍ ቤተሰብ ቀንን አስመልክቶ የሚቀርቡ ዝግጅቶች

10ኛውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀንን በማስመልከት የዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ድረ ገጾችን ያዋቀረ ሲሆን፣ ፍቅር በቤተሰብ የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳንን መሠረት ያደረጉ ሥነ ጽሑፎችን፣ አስተምህሮችን፣ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ዘንድ የቤተሰብ ሕይወትን በማስመልከት የሚቀርቡ ትምህርቶችን፣ በሮም ከተማ የሚገኙ አራቱን ዋና ዋና ባዚሊካዎች የሚያስቃኙ ምናባዊ ጉብኝቶች መዘጋጀታቸው ታውቋል።

01 June 2022, 18:01