ፈልግ

የኮንጎ ኪንሻሳ ካቶሊካዊ ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት የኮንጎ ኪንሻሳ ካቶሊካዊ ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ ሥርዓት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ጉብኝት የሰላም እና የተስፋ ምልክት መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሰኔ 25-30/2014 ዓ. ም. ድረስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት 37ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሰላም፣ የተስፋ እና የአንድነት መሆኑን ቫቲካን የቅዱስነታቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብርን ይፋ ባደረገበት ጊዜ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በሁለቱ የአፍሪካ አገራት በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ሦስት ከተሞችን እንደሚጎበኙ፣ ስምንት ንግግሮችን እንደሚያደርጉ እና ሦስት ስብከቶችን እንደሚያቀርቡ፣ ከሕዝባዊ መሪዎች እና የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ከወጣቶች፣ ከተፈናቃዮች እና የአመጽ ሰለባ ከሆኑ ሰዎች ጋር እንደሚገናኙ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል። ቅዱስነታቸው ለረጅም ጊዜ ሲመኙት በቆዩት የሁለቱ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በርካታ ተግባራት የሚጥብቋቸው መሆኑ ተግልጿል። ይህን የአብያት ክርስቲያናት አንደነት የሰላም ጉብኝት፣ በእንግሊዝ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዌልቢ እና    የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ መሪ የሆኑት ክቡር ዶ/ር ያን ግሪንሺልድስ የሚካፈሉት መሆኑ ታውቋል።

የጉዞ መጀመሪያ ሰኔ 25/2014 ዓ. ም. ነው

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ቅዳሜ ግንቦት 20/2014 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው ዘገባው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት 37ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚጀምረው፣ ቅዳሜ ሰኔ 25/2014 ዓ. ም.፣ በሮም ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል መሆኑን አስታውቋል።

ቅዱስነታቸው ከስድስት ሰዓት ተኩል የአየር ላይ ጉዞ በኋላ ወደ ኪንሳሻ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚደርሱ ያስታወቀው የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዘገባው፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት እና የሃይማኖት መሪዎች ኣቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ወደ አገሪቱ ቤተ መንግሥት እንደሚያመሩ አስታውቋል። የአገሪቱ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ፌሊክስ ሺሴኬዲ በቤተ መንግሥት ተገኝተው ለቅዱስነታቸው የክብር አቀባበል ካደረጉላቸው በኋላ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት እና ዲፕሎማሲዊ አካላት ጋር በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ሥፍራ ተገናኝተው የሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የመጀመሪያ ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። በተመሳሳይ ዕለት በአገሪቱ ከሚገኙ የኢየሱሳውያን ማኅበር አባላት ጋር በቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ስብሰባን በማድረግ የመጀመሪያውን ቀን እንደሚደመድሙ የጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

በኪንሻሳ ውስጥ ከቀሳውስት ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን እና ስብሰባን ያካሂዳሉ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሐዋርያዊ ጉብንታቸው ሁለተኛ ቀን በሆነው እሑድ ሰኔ 26/2014 ዓ. ም. በኪንሻሳ ከተማ በሚገኝ ንዶሎ አውሮፕላን ማረፊያ የሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ከመሩ በኋላ፣ በሥፍራው ከተገኙት ምዕመናን ጋር ሆነው የእኩለ ቀን የመልአከ ገብርኤል ጸሎትን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል። ከሰዓት በኋላ በሚኖራቸው ጊዜ ከአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና ከትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎች ጋር ኪንሳሻ ከተማ በሚገኝ በኮንጎ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ውስጥ እንደሚገናኙ ታውቋል።       

ቅዱስነታቸው በሰሜን ኪቩ የሚያደርጉት ጉብኝት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሰኞ ሰኔ 27/2014 ዓ. ም. በሰሜን-ኪቩ ውስጥ ወደምትገኘው የጎማ ከተማ በአውሮፕላን እንደሚጓዙ ያስታወቀው የጉብኝታቸው መርሃ ግብሩ፣ በአገሪቱ ምስራቃዊ ግዛት በታጣቂ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈናቀሉበት አካባቢን እንደሚገበኙ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ወደ ጎማ ከተማ ከረፋዱ አራት ሰዓት ከሩብ ላይ ከደረሱ በኋላ ቀትር ላይ በኪቡምባ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል። የሰሜን ኪቩ ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ በሆነች ቤኒ ውስጥ ከሰዓት በኋላ ከጥቃት ሰለባዎች ጋርም እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

ቤኒ ከተማ እና አካባቢዋ በኢቦላ ወረርሽኝ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ክፉኛ የተጠቃች፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በርካታ ጥቃቶች እና አሰቃቂ ድርጊቶች የተፈጸሙባት፣ አፈና እና ዘርፊያ እንዲሁም ሚሊሻዎች እና ሠራዊቱ ከፍርድ ቤት ሥርዓት ውጪ በራካታ ግድያዎችን የሚፈጸሙባት አካባቢ መሆኗ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎማ ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኝ የእንግዳ መቀበያ ማዕከል፣ ከአመጹ ተጠቂዎች ጋር ከአንድ ሰዓት በላይ ቆይታ ካደረጉ በኋላ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ማታ አሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ ወደ ኪንሻሳ እንደሚመለሱ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማግሥቱ፣ ማክሰኞ ሰኔ 28/2014 ዓ. ም. ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ እንደሚያቀኑ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ቅዱስነታቸው ጉዞአቸውን ወደ ደቡብ ሱዳን ከማቅናታቸው አስቀድመው በኪንሻሳ የ "ሰማዕታት ስታዲዬም" ውስጥ ከወጣቶች እና ከትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎች ጋር ከተገናኙ በኋላ ኮንጎን በመሰናበት ከካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ከብጹዕ አቡነ ዌልቢ እና ከስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ መሪ ከሆኑት ከያን ግሪንሺልድስ ጋር ወደ ደቡብ ሱዳን በማምራት በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ወደ ጁባ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ሲደርሱ በአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት እና የሃይማኖት ተወካዮች የክብር አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ የአገሪቱ ፕሬዚደንት አቶ ሳልቫ ኪር በቤተ መንግሥታቸው የክብር አቀባበል የእንደሚያደርጉላቸው ታውቋል። በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኝ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የሃይማኖት እና የፖለቲካ ባለስልጣናት በመጋቢት ወር 2011 ዓ. ም. የሰላም ስጦታን ለመለመን ወደ ቫቲካን በመጡ ጊዜ፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ የጳጳሳት መኖሪያ ቤት ውስጥ አቀባበል ማድረጋቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአገሪቱ ቤተ መንግሥት ውስጥ የክብር አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚደንት ከአቶ ሪያክ ማቻር፣ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ከዲፕሎማሲያዊ አካላት ጋር በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ሥፍራ ውስጥ ተገናኝተው ንግግር እንደሚያደርጉላቸው ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ከተፈናቃዮች ጋር ይገናኛሉ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ረቡዕ ሰኔ 29/2014 ዓ. ም. ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ላይ በጁባ ከተማ በሚገኝ መጠለያ ውስጥ የሚኖሩትን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚገበኟቸው ታውቋል። በመቀጠልም ከደቡብ ሱዳን የኢየሱሳውያን ማኅበር አባላት ጋር በሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ እንደሚገናኙ እና ከቀትር በኋላ በጁባ ከተማ በሚገኝ ቅድስት ቴሬዛ ካቴድራል ውስጥ ለአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል። ማታ አሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ፣ የቀድሞ የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ መሪ በነበሩ እና የደቡብ ሱዳን ቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት በነበሩት በ"ጆን ጋራንግ" መታሰቢያ ሐውልት ሥፍራ በሚደረግ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሚሳተፉ ታውቋል።

ከመስዋዕተ ቅዳሴው በኋላ ጉዞ ወደ ሮም

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ወደ ሮም ከመመለሳቸው በፊት በ"ጆን ጋራንግ" መታሰቢያ ሐውልት አካባቢ በተዘጋጀው ሥፍራ፣ ሰኔ 30/2014 ዓ. ም. ጠዋት የመጨረሻ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ታውቋል። ቅዱስነታቸው ከመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ ሥርዓት በመቀጠል ለስንብት ወደ ጁባ አውሮፕላን ማረፊያ ከመጡ በኋላ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ተደርጎላቸው፣ በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ አምስት ሰዓት ከሩብ ላይ ወደ ሮም ተጉዘው በተመሳሳይ ዕለት በሮም የሰዓት አቆጣጠር ማታ አሥራ ሁለት ከአምስት ደቂቃ ላይ ወደ ሮም ፊውሚሲኖ አውሮፕላን ማረፊያ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

30 May 2022, 17:57