ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳትን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳትን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በእምነት እንድታድግ መፈለጋቸው ተገለጸ።

የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ስቪያስቶስላቭ ሼቭቻክ ትናንት ሐምሌ 1/2011 ዓ. ም. በቫቲካን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዩክሬይን የምስራቃዊያን የስርዓተ አምልኮን የምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በእምነት እንድታድግ መፈለጋቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ባደረጉት የሁለት ቀን ውይይታቸው ቤተ ክርስቲያናቸው ከቅድስት መንበር እና ከሌሎች የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ በሚያግዙ አዳዲስ መንገዶች መወያየታቸውን ገልጸዋል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል እንዳስገነዘበው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከከፍተኛ የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ያደረጉት ውይይት ዋና ዓላማ ቅዱስነታቸው ለዩክሬን ቤተክርቲያን ያላቸውን የጠበቀ ግንኙነት ለመግለጽ መሆኑ ታውቋል። የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ በማከልም የቅድስት መንበር ከፍተኛ የመማክርት ጉባኤ ረጅም ታሪክ ላለው ለዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊነት፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ የስነ መለኮት እና የሕገ ቀኖና ባሕል፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ለሆኑት ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ያላቸውን ታማኝነት እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ላላቸውን አንድነት አድናቆትን ለማቅረብ መሆኑ ታውቋል።

የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት በእምነት ማደግ እና መለምለም፣

የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ስቪያስቶስላቭ በመግለጫቸው እንዳስገነዘቡት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉት ውይይት ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማሳደግ በሚያግዙ ምቹ ቅድመ ሁኔታዎች ላይ መሆኑን ገልጸዋል ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ በመሰረታት ቤተክርስቲያን ውስጥ ቡሉ እና ጉልህ አንድነትን ማምጣት ነው ብለዋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ስቪያስቶስላቭ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ፍቅር ገልጸው ሌሎችም የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት በእምነት ማደግ እና መለምለም ያስፈልጋል ብለዋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ስቪያስቶስላቭ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉት ውይይት የቤተክርስቲያን ኩላዊነትን የሚገልጹ ከዓለም ዙሪያ የመጡትን ሊቃነ ጳጳሳትን ያሳተፈ ነበር ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ ዩክሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ ግብዣ ቀርቦላቸዋል፣

የዩክሬን ግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ቅዱስነታቸው ወደ ዩክሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውን በጋዜጣዊ መግለጫቸው የገለጹት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ስቪያስቶስላቭ ቅዱስነታቸው ዩክሬንን ቢጎበኟት ላለፉት አምስት ዓመታት በጦርነት ለተሰቃየው የአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ሕዝብ ሰላም ትልቅ ተስፋ ይሆናል ብለዋል።

የሰብዓዊ እና አካባቢያዊ አስቸኳይ እርዳታ፣

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተደረገው ሁለተኛ የውውት ርዕሥ በምስራቃዊ ዩክሬን በጦርነት ምክንያት የተከሰተውን ቀውስ የተመለከተ እንደነበር የገለጹት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ስቪያስቶስላቭ ጦርነቱ በተፈጥሮ ላይ ባስከተለው ቀውስ ምክንያት በሚቀጥሉ ጥቂት ወራት ውስጥ የአካባቢው ሕዝብ የመጠጥ ውሃ እጥረት ሊያጋጥመው እንደሚችል ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
09 July 2019, 17:20