ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዩክሬይን ግሪክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቋሚ የጳጳሳት ሲኖዶስ አባላት ጋር ሆነው፣  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዩክሬይን ግሪክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቋሚ የጳጳሳት ሲኖዶስ አባላት ጋር ሆነው፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ፣ በሕዝቦቿም መካከል ሕብረት እንዲፈጠር አሳሰቡ።

በተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች እና የጦረነት ቀውስ ውስጥ በምትገኝ ዩክሬይን ሰላም እና የሕዝቦቿ አንድነት እንዲረጋገጥ አሳሰቡ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የተናገሩት ትናንት ዓርብ ሰኔ 28 ቀን/2011 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው የዩክሬይን ግሪክ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቋሚ የጳጳሳት ሲኖዶስ አባላት ባቀረቡት የአደራ መልዕክት መሆኑን የቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ባርባራ ካስቴሊ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። ቅዱስነታቸው ከዩክሬን ጳጳሳት ሲኖዶስ ልኡካን ጋር ባደረጉት ውይይት በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ፣ ቤተክርስቲያንም በጸሎት ሃይል እየታገዘች አንድነቷን ጠብቃ በተለይም በችግር ውስጥ ለወደቁት የቅርብ አለኝታ በመሆን፣ ገር እና ትሁት በመሆን በሕብረት መጓዝ እንዳለባት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በዩክሬን ውስጥ የሚታየውን አለመረጋጋት እና ጦርነት ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በጦርነቱም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ዋጋንም የከፈሉት አቅመ ደካሞች መሆናቸውን ተናግረዋል። በዚያች አገር ለሚቀሰቀስ ጦርነት እና ግጭት ምክንያቶቹ የተለያዩ መሆናቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው አንዳንድ ጊዜ የግጭቶቹ ምክንያት ሃይማኖታዊ የመሆን አዝማሚያም መኖሩን በቫቲካን ተቀብለው ላነጋገሯቸው፣ የምስራቃዊያን ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ የዩክሬን ግሪክ ካቶሊካዊ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ተወካዮች ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በዩክሬን በተቀሰቀሱት ጦርነቶች እና ግጭቶች ሰበብ ሕይወታቸውን ያጡትን፣ የአካል እና የመንፈስ መቁሰል የደረሰባቸውን፣ ከሥራቸው የተፈናቀሉትን እና የተሰደዱትን በሙሉ በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል። አክለውም ለአገልግሎት ለጠራቸው አምላክ በመታመን በአስቸጋሪ ወቅቶች በሙሉ ከምዕመናኑ ጋር የሆነውን የብጹዓን ጳጳስት ሲኖዶስ አመስግነው ሕዝባዊ አደራን የተሸከሙ የመንግሥት ባለስልጣናት ወገናዊነትን ትተው ሕዝባቸውን በታማኝነት ማገልገል የሚችሉበትን ጥበብ ከፈጣሪ ዘንድ በጸሎታቸው የሚለምኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቤተክርስቲያን የተጠራችው ክርስቲያናዊ ተስፋን ለመመስከር እንጂ ተስፋን ለመቁረጥ አይደለም ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህ ተስፋም ሃላፊ፣ ታይቶ የሚጠፋ፣ ብዙን ጊዜ በሕዝቦች መካከል መከፋፈልን የሚያመጣ ዓለማዊ ተስፋ አይደለም ብለዋል። ክርስቲያናዊ ተስፋ ከኢየሱስ ክርስቶስ በሚያገኘው ብርሃን በመታገዝ ጨለማ በዋጠው ሌሊት የትንሳኤው እና የዘለዓለማዊ ሕይወት ብርሃን እንዲበራ ያደርጋል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ከጥቂት ዓመታት በፊት በዩክሬን ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተጀመረውን የሐዋርያዊ አገልግሎት መርሃ ግብርን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት በዩክሬን የሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ጥንካሬን አግኝተው፣ ምዕመናኑም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ዘወትር የሚገናኙበት፣ በዚህም ቤተክርስቲያን የተስፋ ወንጌልን በመመስከር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ እና መስፋፋት ያስፈልጋታል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናን ከምታበረክትላቸው ልዩ ልዩ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች በተጨማሪ በተለይም የስቃይ ህይወትን በመኖር ላይ ለሚገኙት በሙሉ አለኝታነቷን መግለጽ ያስፈልጋል ብለዋል። ቤተ ክርስቲያን ላዘኑት መጽናናትን እና ብርታትን ለመስጠት ዘወትር በሯን ክፍት ማድረግ የምትጠብቅ፣ ጊዜን ሳታባክን የፍቅር ልብን በማሳየት በችግር ላይ የወደቁትን ማዳመጥ ይኖርባታል ብለዋል።                     

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በማከልም የቤተክርስቲያን አንድነት የሚገለጸው በሕብረት ሲጓዙ ነው ብለው ይህም ተመሳሳይ ሃሳብ ካላቸው ጋር ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ከሚያምኑት ሁሉ ጋር መሆን አለበት ብለዋል። የብጹዓን ጳጳሳቱ ሲኖዶስ በሕብረት ለመጓዝ መደማመጥ መሠረታዊ መንገድ እንደሆነ አስረድተው ስሕተቶችን ወይም እንቅፋቶችን ወደ ጎን ከማለት ይልቅ የመፍትሄ መንገዶችን ማግኘት እንደሚያስፈልግ አሳስበው የሕብረት ጉዞ ሲባል እያንዳንዱን ምዕመን የሚያሳትፍ መሆኑንም አስረድተዋል። በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚገኙት የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ከየሃገረ ስብከቶቻቸው እና ቁምስናዎቻቸው ጋር በሕብረት መጓዝ ማለት ከቅድስት መንበር ጋር ያላቸውን አንድነት ያጠናክራል ብለዋል።     

06 July 2019, 16:33