ፈልግ

በግሪክ በደረሰ የጀልባ አደጋ በደርዘን የሚቆጠሩ ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸው ተነገረ በግሪክ በደረሰ የጀልባ አደጋ በደርዘን የሚቆጠሩ ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸው ተነገረ 

በግሪክ በደረሰ የጀልባ አደጋ በደርዘን የሚቆጠሩ ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸው ተነገረ!

ከአቅም በላይ ስደተኞችን ጭና እንደነበር የተነገረው ጀልባ ተገልብጣ ከግሪክ ውቅያኖስ ላይ ሰምጣለች በተባለው የሀገሪቱ መርከብ በደረሰ ከባድ አደጋ የግሪክ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ከመቶ በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ማትረፍ ቢቻልም ፥ ቢያንስ 59 ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸውን እና ሌሎች ብዛት ያላቸው ስደተኞች እስከ አሁን አለመገኘታቸው ታውቋል። ነገር ግን የፍለጋ እና የማገገሚያ ስራዎች ቀጥለዋል ተብሏል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ አዲስ አበባ

ስደተኞችን ጭኖ ይጓዝ የነበረ ጀልባ ፥ ባለፈው ሰኔ 7 2015 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት፣ በግሪክ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጦ ፥ በርካቶች መሞታቸውን ተከትሎ ግሪክ፥ የሦስት ቀን ብሔራዊ ኀዘን ዐውጃለች።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በግሪክ ከደረሱት አስከፊ አደጋዎች አንዱ እንደኾነ በተገለጸው በዚህ የጀልባ መገልበጥ አደጋ ፥ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ቢረጋገጥም ፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ግን እስከ አሁን ያሉበት ባለመታወቁ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የግሪክ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የጀልባዋ መገልበጥ

ጀልባዋ ከሰመጠች ከጥቂት ሰአታት በኋላ የአሰሳ እና የማዳን ስራ ተጀመረ ፥ ኦፕሬሽኑም ስድስት የባህር ዳርቻ ጥበቃ መርከቦች፣ የባህር ኃይል የጦር መርከብ፣ ወታደራዊ ማመላለሻ አውሮፕላን እና የአየር ሃይል ሄሊኮፕተር፣ በርካታ የግል መርከቦች እንዲሁም ፍሮንቴክስ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ያካተተ ነው።

በጀልባው ተሳፍረው ከነበሩት አብዛኞቹ በ20 ዓመት የዕድሜ ክልል የሚገመቱ ፥ ከግብፅ፣ ሶሪያ እና ፓኪስታን የመጡ እንደኾኑ ተነግሯል። የግሪክ ፕሬዚዳንት ካትሪና ሳኬላሮፑሉ ከአደጋው ተርፈው ካላማታ በተሰኘች የግሪክ ከተማ ወደሚገኝ መጠለያ የተወሰዱትን ስደተኞች ሲጎበኙ ፥ የከተማዋ ከንቲባ ታናሲስ ቫሲሎፖለስ ስደተኞቹን ለመርዳት የተለያዩ አገልግሎቶች እየቀረቡላቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

“ለሁሉም ክብካቤ እያደረግን ነው። መጠለያ፣ መጸዳጃ፣ መታጠቢያ እና ሌላም የሚያስፈልጋቸውን አዘጋጅተናል። ሌሊቱን በዚህ ሲያሳልፉ የሚበሉት እና ለነገ ቁርስ፣ ምሳ እና ራት የሚኾን ምግብም መጥቷል” ነው ያሉት ቫሊሎፖለስ።

ተብሮክ ከተሰኘ የሊቢያ ከተማ ተነሥቶ ወደ ጣሊያን ሲያቀና እንደነበር በተገለጸው ጀልባ ፥ ወደ 750 የሚደርሱ ሰዎች ተሳፍረው እንደነበር ይታመናል ሲል አላርም ፎን የተሰኘ የአደጋ ጊዜ በጎ አድራጎት ተቋም ሲያስታውቅ ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ደግሞ የተሳፋሪዎቹ ቁጥር 400 እንደኾነ ገምቷል።

ግሪክ ጦርነትን ፣ ስደትን እና ድህነትን ሸሽተው የሚሰደዱ በርካታ ሰዎች ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ እስያ እና አፍሪካ እየተነሡ ወደ አውሮፓ ኅብረት ለሚጓዙ ስደተኞች ዋና መተላለፊያ መንገድ ስትሆን፣ በዚህ ዓመት ብቻ 72 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች በአውሮፓ ግምባር ቀደም መዳረሻ ወደሆኑት ጣሊያን፣ ስፔን፣ ግሪክ፣ ማልታ እና ቆጵሮስ መግባታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት እንዳመላከተው ፥ እሮብ በኤጂያን ባህር ላይ የደረሰው አደጋ ህጋዊ የሰዎች ዝውውር ላይ ተጨማሪ ሥራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ አስምሮበታል።

ሆኖም የተደራጁ ወንጀለኞች በአንዳንድ ሀገራት ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት በመጠቀም የአውሮፓ ህብረትን ድንበር አቋርጠው የሚያጓጉዙትን ስደተኞች ቁጥር እየጨመሩ እንደሚገኝ የአውሮፓ ህብረት ፍሮንቴክስ ኤጀንሲ ገልጿል።

 

16 June 2023, 15:45