ፈልግ

በግሪክ የባሕር ዳርቻ በሜድትርራኒያን ባሕር ላይ ስደተኞችን ጭና የምትሄድ መርከብ ምስል በግሪክ የባሕር ዳርቻ በሜድትርራኒያን ባሕር ላይ ስደተኞችን ጭና የምትሄድ መርከብ ምስል  (AFP or licensors)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ባጡ ሰዎች ማዘናቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ በሜዲትራኒያን ባሕር ውስጥ ከደረሱት እጅግ የከፋ የስደተኞች አደጋ አንዱ የሆነውን ተከትሎ በግሪክ ለሚገኘው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የሐዘን መግለጫ ቴሌግራም ልከዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግሪክ የባሕር ጠረፍ ላይ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ በነበረች መርከብ ላይ የደረሰውን አደጋ በሰሙ ጊዜ፣ በግሪክ ለሚገኘው የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ጃን ሮም ፓውሎውስኪ የሐዘን መግለጫ ቴሌግራም መላካቸው ተገልጿል።

መጀመሪያ ላይ የወጡ ዘገባዎች ቢያንስ 78 ሰዎች ሰጥመው መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን ከ100 በላይ የሚሆኑትን ማትረፍ ተችሏል። በህይወት የተረፉት ግን በጀልባው ውስጥ ብዙ ህጻናትን ጨምሮ እስከ 750 የሚደርሱ ሰዎች ሊኖሩ እንደ ሚችሉ ይናገራሉ። ታዛቢዎች ይህ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቁ የስደተኞች አሳዛኝ ክስተቶች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የቫቲካን ዋና ጸሐፊ በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን  ፊርማ ያረፈበት  የቴሌግራም መልእክት ቅዱስነታቸው የላኩ ሲሆን “በግሪክ የባሕር ጠረፍ ላይ የደረሰው ከባድ የሰው ሕይወት መጥፋቱን በመረዳታቸው እጅግ አዝነዋል” ሲሉ ጽፈዋል።

“ለሞቱት ብዙ ስደተኞች፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና በዚህ አደጋ ለተጎዱት ሁሉ” ከልብ የመነጨ ጸሎት ሲያቀርቡ፣ ቅዱስ አባታችን የተረፉትንና ለመርዳት በሚተጉ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ላይ ጌታ “ጥንካሬ፣ ጽናት እና ተስፋ” እንዲሰጣቸው እንደ ሚማጸኑ የገለጹ ሲሆን ከእዚህ አደጋ ለተረፉት ሁሉ እንክብካቤ እና መጠለያ እንዲሰጣቸው ቅዱስነታቸው ተማጽኗል።

ይህ አሳዛኝ አደጋ

ይህ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ሌላ ቀውስ ነው፣ ነገር ግን እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመርከቧ መንገደኞች፣ እስካሁን የት መግባታቸው ካልታወቁ ሰዎች ጋር ሲወዳደር ይህ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ከደረሰው የስደተኞች የመርከብ አደጋ የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ይፈጥራል።

የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ጣልቃ አልገቡም በሚል ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረባቸው ቢሆንም፣ ባለሥልጣናቱ ግን ሊሰጡ የሞከሩት የዕርዳታ አቅርቦቶች በሙሉ ውድቅ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ብዙ የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ተስፋ ያነሰ እና ተስፋ አስቆራጭ ነው። ከመርከቧ አደጋ የተረፉት አብዛኞቹ ሰዎች ተመሳሳይ ታሪኮችን ነው የሚናገሩት - ተመሳሳይ አሃዝ ያላቸው - በመርከቧ ውስጥ ከተጓዙት መንገደኞች ብዛት ፣ በመርከቧ ውስጠኛ ክፍል ውስጥ የተቆለፉትን ሰዎች ብዛት ጨምሮ ፣ ከእነዚህ ውስጥ 100 የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው፣ ይህ አደጋ አስቃቂ እንዲሆን አድርጓል ተብሏል።

ብዙ ጊዜ የሕገወጥ የሰው ዝውውር የሚያደርጉ ሰዎችን በመርከቧ ታቸኛ ክፍል ውስጥ በመቆለፍ ለመቆጣጠር እና ለማስፈራራት እንደሚሞክሩ ይነገራል።

ምን ተፈጠረ?

የባህር ዳርቻ ጠባቂው እንዳስታወቀው ጀልባዋ ከመስጠሟ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ከቀኑ 8 ሰአት ላይ አከባቢ ላይ ከጀልባዋ ጋር የመጀመሪያ ግንኙነት የተደረገ ሲሆን ምንም ዓይነት የእርዳታ ጥያቄ እንዳልቀረበ ተናግሯል።

የግሪክ የባህር ማጓጓዣ ሚኒስቴር ከጀልባው ጋር በተደጋጋሚ ከተገናኘ በኋላ ምላሹ ወደ ጣሊያን ለመጓዝ እንደሚፈልግ በመግለጽ ቀጥሏል።

መርከቧ ከመስጠሟ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አመሻሹ ላይ የማልታ ባንዲራ የያዘች መርከብ ለመርከቧ ምግብ እና ውሃ ስትሰጥ፣ ሌላ ጀልባ ደግሞ ከሶስት ሰዓታት በኋላ ውሃ ማቅረቧ ተገልጿል።

እሮብ እለት 01፡40 ላይ በጀልባው ላይ ያለ ሰው የመርከቧ ሞተር መበላሸቱን ለግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ማሳወቁ ተነግሯል። ብዙም ሳይቆይ ጀልባው ሙሉ በሙሉ ለመስጠም ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ብቻ ወስዳለች።

16 June 2023, 11:27