ፈልግ

በሶርያ ውስጥ ከሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ በሶርያ ውስጥ ከሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መካከል አንዱ   (AFP or licensors)

በሶርያ የ11 ዓመቱ ጦርነት ዛሬም የምግብ ዋስትና እንዳይኖር ማድረጉ ተነገረ

በሶርያ ውስጥ መጋቢት 6/2003 ዓ. ም. የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት እና የዩክሬን ጦርነት በሶርያ ውስጥ የምግብ ዋስትና እንዳይኖር ማድረጉ ታውቋል። በሶርያ ውስጥ የረሃብ አደጋ የተደቀነባቸውን ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለመርዳት መሠረተ ልማትን በአስቸኳይ ወደ ነበረበት መመለስ እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ “ኦራዚዮ ራጉሳ” የተሰኘ ረሃብ አስወጋጅ ድርጅት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሶርያ ቢያንስ 12.4 ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ መጋለጣቸው ሲነግር፣ ረሃብን እና የሕጻናትን የተመጣጠነ ምግብ እጦት በመዋጋት ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ በሶርያ ውስጥ መጋቢት 6/2003 ዓ. ም. ተቀስቅሶ ለአሥራ አንድ ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት አውግዟል። ለረሃብ የተጋለጡ ሶርያውያን ቁጥር ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ቁጥር ማደጉን “ኦራዚዮ ራጉሳ” የተሰኘ የረሃብ አስወጋጅ ድርጅት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

እስከ ዛሬ ድረስ በሶርያ ውስጥ ያለው የፍጆታዎች ፍላጎት መጨመር ቤተሰቦች ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን ​​ለመቋቋም ካላቸው አቅም በላይ መሆኑ ታውቋል። በዚህ መሠረት ሀገሪቱ እርስ በእርስ በተሳሰሩ ችግሮች ውስጥ የምትገኝ መሆኑ ታውቋል። በአገሪቱ የሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትም ሶርያውያን ለመኖር በየቀኑ የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ መጠን እንዲያድግ ማድረጉ ታውቋል። አስፈላጊ ፍጆታዎች እንደ ውሃ ፣ ምግብ ፣ ነዳጅ እና መብራት በአማካይ 50 በመቶ ጭማሪ በማሳየታቸው ምክንያት ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆናቸው ቤተሰቦች በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንደማይሆኑ ታውቋል። ሕዝቡ መኖሪያ ቤቱን፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱን እና የውሃ መሠረተ ልማቱን በጄነሬተሮች ለማንቀሳቀስ በቂ ነዳጅ መግዛት እንደማይችል ተገልጿል።

ዛሬ ብዙ ሶርያውያን በቀን ከ4 ሰዓታት ያነሰ የመብራት አገልግሎት የሚያገኑ ሲሆን፣ በተጨማሪም አርሶ አደሮች እርሻቸውን ለማረስ ያላቸው አቅም እጅግ ውስን እንደሆነ፣ እርሽእዎቻቸውን በመስኖ ለማልማት እና ወደ ገበያ ለማጓጓዝ የሚጠይቀው ወጪ ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ ከሆነ፣ በዩክሬን ያለው ጦርነት በሶርያ የእህል አቅርቦት ላይ እጥረትን ሊያስከትል እንደሚችል፣ ይህም እንደ ዳቦ እና ዱቄት ባሉ ዋና ምግቦች ዋጋ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አስታውቋል። ረሃብ አስወጋጅ ድርጅቱ፣ በሶርያ ውስጥ እ. አ. አ ከ 2008 ጀምሮ ተጋላጭ በሆኑ ማኅበረሰቦች መካከል ረሃብን በመዋጋት እና በጤና ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን በመቀነስ፣ አደጋን የመቋቋም አቅምን ለመገንባት እና የረዥም ጊዜ ድጋፍን በማድረግ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። በሶርያ ውስጥ ባለፈው ዓመት ብቻ 1.3 ሚሊዮን ሰዎችን በመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በንፅህና አጠባበቅ፣ የጤና ተቋማትን በማሻሻል እና በምግብ አቅርቦት ላይ ዕርዳታ ማድረጉ ታውቋል። የዓለም ትኩረት እና የገንዘብ ድጋፍ እያሽቆለቆለ ባለበት በዚህ ዓመት 14.6 ሚሊዮን ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ጫና

ዝቅተኛ የዝናብ መጠን የሚያገኙ አካባቢዎች ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ድርጅቱ አስታውሶ፣ በዚህ ዓመት ሶርያ በ70 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ መጎዳቷን አስታውቋል። ይህ ክስተት በቂ ፍሬን ያስገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ ሰብሎች መጉዳቱ ታውቋል። በረሃብ አስወጋጅ ድርጅት የመስክ መረጃ መሠረት፣ እ. አ. አ በ2021 የስንዴ ምርት መጠን ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ እንደ ነበር እና በ2020 ከ 2.8 ሚሊዮን ቶን በታች እንደነበር አስታውቋል። 

የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው ቀውስ

በዩክሬን ያለው ጦርነት መጠነ ሰፊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል ድርጅቱ ገልጾ፣ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ተፅዕኖን እንደሚያሳድር አስታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ገበያዎች ግንኙነት ላይ አለመተማመን እንደሚያስከትል አስታውቋል። ዛሬ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት መለካት እንደማይቻል የገለጸው ድርጅቱ፣ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ውስጥም ተፅእኖ እንደሚኖረ አስረድቷል። ከዩክሬን እና ከሩሲያ በቀጥታ በሚገቡት እና ከሌሎች ሀገራት በሚመጡት የኢነርጂ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን የገለጸው ድርጅቱ፣ በአንድ ወቅት የአውሮፓ ጎተራ ተብለው የተጠሩ ሩሲያ እና ዩክሬን ዛሬ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ ለአውሮፓ አህጉር ማቅረብ እንደማይችሉ ገልጾ፣ ነገር ግን የተለያዩ የሦስተኛው ዓለም አገራት ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ገልጾ፣ የወጪ ንግድ ሲቆም የፍላጎት መጨመርን፣ የአቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ጭማሪ እንደሚያስከትል ድርጅቱ አስረድቷል።

16 March 2022, 16:06