ፈልግ

በሶርያ የሚካሄድ ጦርነት በአሌፖ ከተማ ያስከተለው ውድመት በሶርያ የሚካሄድ ጦርነት በአሌፖ ከተማ ያስከተለው ውድመት 

ካርዲናል ዘናሪ፣ ሶርያ ከ11 ዓመታት ጦርነት በኋላ የተረሳች አገር መሆኗን ገለጹ

በደማስቆ፣ የቅድስት መንበር እንደራሴ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፣ በአገሪቱ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት የተቀሰቀሰበትን 11ኛ ዓመት በማስመልከት ትናንት መጋቢት 6/2014 ዓ. ም. መልዕክት አስተላልፈዋል። ብጹዕነታቸው በመልዕክታቸው፣ "የሕዝቡ ተስፋ መጥፋት የለበትም" ብለው፣ ብጥብጥን፣ ድህነትን እና ማግለልን በድጋሚ አውግዘዋል። መጋቢት 6/2003 ዓ. ም. በሶሪያ ውስጥ የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት ለግማሽ ሚሊዮን ያህል የሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሶርያ ውስጥ በርካታ ቤቶች ወድመዋል፣ ከፍተኛ የምግብ፣ የውሃ እና የመድኃኒት እጥረት ባለበት ሁኔታ፣ በብጥብጥ እና በዘረፋ ምክንያት ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን በመልቀቅ እየተሸሹ ይገኛል። በሶሪያ ውስጥ ከ 11 ዓመታት በኋላም ግጭቱ አላበቃም። የሶርያ ጦርነት እንደ ሌሎች አገራት ጦርነት ብዙ አልተወራለትም። ብዙ ከተሞች ፈርሰው የቀሩባት ይህች ሀገር በግማሽ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ስታዝን፣ ከ11 ሚሊዮን ተኩል በላይ ተፈናቃይ በአገር ውስጥ እና ወደ ውጭ አገራት ተሰደዋል።

በሶርያ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት የተቀሰቀሰበት 11ኛ ዓመት ለማሰብ በደማስቆ ከተማ ውስጥ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው ጉባኤ ትናንት መጋቢት 6/2014 ዓ. ም. መጀመሩ ታውቋል። ጉባኤው ፣ “ቤተ ክርስቲያን፣ የበጎ አድራጎት ቤት - የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት እና ማስተባበሪያ” በሚሉ የመወያያ ርዕሦች ላይ የሚወያይ መሆኑ ታውቋል።

በጉባኤው መሃል እርስ በእርስ መደማመጥ፣ መወያየት፣ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች የወደፊት እጣ ፈንታ፣ ከሚሉ ርዕሠ ጉዳዮች በተጨማሪ የዚያች አገር ሕዝብ ስቃይን ለማስወገድ በሚያግዙ አስቸኳይ መፍትሄዎች እና ፍላጎቶች ላይም የሚወያይ መሆኑ ታውቋል። በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ፣ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ዘናሪ፣ ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፣    አገሪቱ በብዙሃን መገናኛዎች በኩል እየተረሳች ባለችበት በዚህ ወቅት "የሕዝቡ ተስፋ መሞት የለበትም" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ በሶርያ ውስጥ ጦርነቱ ገና ያላቆመ መሆኑን ገልጸው ላለፉት ሁለት ዓመታት ሶርያ ከመገናኛ ብዙሃን እይታ መሰወሯ ያሳዝናል ብለዋል። መጀመሪያ የሊባኖስን ቀውስ፣ ቀጥሎ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ አሁን ደግሞ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የዓለሙ ማኅበረሰብን ቀልብ ወስዶታል ብለዋል። ተስፋ ከብዙ ሰዎች ልብ ጠፍቷል ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ዘናሪ፣ በተለይም በአገራቸው ላይ ያለው ተስፋ የጨለመባቸው በርካታ ወጣቶች ስደትን መርጠዋል ብለው፣ የሰለጠኑ ወጣቶች የሌሉባት አገር ዕጣ ፈንታ የጨለመ እንደሚሆን አስረድተዋል። 

ከዩክሬን የሚሰደዱ አንዳንድ ቤተሰቦች ብዙ ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ወደ ፖላንድ እንዳይገቡ አሁንም ታግተው መቆየታቸው ሲነገር፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ወዲህ ሶርያ አሁንም አሳሳቢ የሆነ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ የሚታይባት አገር ሆና መቆየቷ ታውቋል። በሶርያ ውስጥ አሁንም የመልሶ ግንባታ እና የኢኮኖሚ ጅምር ምልክቶች እንደሌሉ ሲነገር፣ ከዚህም በላይ ኤኮኖሚያዊ ማዕቀቦች የሕዝቡን ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎት እንደቆየ ታውቋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔ ቁ. 2254 መሠረት የሰላም ሂደቱ የታገደ በመሆኑ ድህነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ ታውቋል።

16 March 2022, 15:56