ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን የሩምቤክ ሀገረ ስብከትን በጎበኟት ወቅ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን የሩምቤክ ሀገረ ስብከትን በጎበኟት ወቅ 

ደቡብ ሱዳን ሕዝቦቿን ከድህነት አውጥታ ዳግም እንደምትወለድ ተገለጸ

በደቡብ ሱዳን የአራት ቀናት ጉብኝት ያደረጉትን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በሀገረ ስብከታቸው የተቀበሉት የሩምቤክ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ፥ ደቡብ ሱዳን ሕዝቦቿን ከድህነት በማውጣት ዳግም እንደምትወለድ ገለጹ። በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ጉብኝት ለማጠቃለል ወደ ሩምቤክ የተጓዙትን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሀገረ ስብከታቸው የተቀበሉት ብጹዕ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ፥ “ደቡብ ሱዳንን በፍጥነት መቀየር ካልቻልን እና የሕዝቧን ሰብዓዊ ክብር መመለስ ካልቻልን ሰላም ሊኖር አይችልም” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የካቲት ወር 2015 ዓ. ም. በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፥ “ቁርጠኝነት ያለው ሁሉን የሚያካትት ውይይት” ያሉትን መርህ በመያዝ፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን የአራት ቀናት ጉብኝት አድርገዋል። ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን ደቡብ ሱዳንን ለሦስተኛ ጊዜ የጎበኟት ሲሆን፥ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኟት እንደ ጎርጎርሳውያኑ በሐምሌ 2022 ዓ. ም. እንደነበር፣ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን ሊያደርጉት ያቀዱትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በጤና ምክንያት በማራዘማቸው እንደነበር ይታወሳል። በኋላም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከየካቲት 3-5/2023 ዓ. ም. ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ባሁኑ የደቡብ ሱዳን ጉብኝታቸው ጁባ፣ ማላካልን እና በመጨረሻም ነሐሴ 11/2015 ዓ. ም. በሩምቤክ ሀገረ ስብከት ባደረጉት ጉብኝት ለአገሪቱ ሰላምን እና እርቅን የተማጸኑበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አቅርበዋል።

ደቡብ ሱዳን ፍርሃት ሥር የሰደዱባት፣ ለብዙ ዓመታት ግጭት እና ብጥብጥ ባስከተለው ጉዳት የተሰቃየች አገር እንደ ሆነች የገለጹት የሩምቤክ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ፥ ሁሉንም የሚያሳትፍ ብሔራዊ ውይይት በአገሪቱ ዜጎች መካከል አንድነትን ማምጣት እንደሚችል፣ ከፍትሕ መጓደል. እና ከአመጽ ጋር የተያያዙ አሳዛኝ ታሪኳንም መለወጥ እንደሚችል አስረድተዋል። “ለአብሮነት እና ለይቅርታ ቦታን መስጠት ያስፈልጋል” አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ፥ እያንዳንዱ ሰው ይህን አሉታዊ ታሪክ ለመቀየር ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረው፥ “ውይይትን ከተግባር ጋር በማዛመድ ቁርጠኝነትን ከቃል ወደ ተግባር ማሸጋገር ይቻላል” ብለው፥ “መልካም ውጤት ሊመጣ የሚችለው ሁሉም ሰው በአንድነት ሲቆም ብቻ ነው” በማለት አረድተዋል።

መለወጥ እና እርቅ

“ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በደቡብ ሱዳን ያደርጉት ጉብኝት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ቀጥሎ የተደረገ ነው” ያሉት አቡነ ክርስቲያን፥ በሁለቱ ጉብኝቶች መካከል ጥልቅ ግንኙነት እንዳለ እና በተለይም ከማኅበረሰቡ ለተገለሉት እና በእኩልነት እጦት ለሚሰቃዩ ሕዝቦች ልዩ ትኩረት በመስጠታቸው ነው” ብለዋል። የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በሩምቤክ ሀገረ ስብከት ከክርስቲያን ማኅበረሰብ፣ ከሲቪል ማኅበራት እና ከከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ጋርም መገናኘታቸው ልዩ ትኩረት የሰጡበት ጉብኝት እንደ ነበር አቡነ ክርስቲያን ገልጸው፥ ብጹዕነታቸው በሩምቤክ ሀገረ ስብከት መገኘት ሩምቤክ እና ደቡብ ሱዳን በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ልብ ውስጥ፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ልብ ውስጥ እንዳሉ የሚያሳይ እና አብረው በኅብረት እንዲጓዝ የሚያበረታታ ነው” ብለዋል

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሩምቤክ ሀገረ ስብከት መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ወቅት
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በሩምቤክ ሀገረ ስብከት መስዋዕተ ቅዳሴን ባሳረጉበት ወቅት

“ልዩነትን በማስወገድ እርስ በራሳችን እና ከመላዋ ቤተ ክርስቲያን ጋር መተባበር እና ወደ ዕርቅ መድረስ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ አካል ነው” ያሉት አቡነ ክርስቲያን፥ “ካለፈው ታሪክ ወጥተን በቅድሚያ ከራሳችን ከዚያም ቀጥሎ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ያስፈልጋል” ብለዋል። “እራስን በመለወጥ ላለፉት ዓመታት በደቡብ ሱዳን ማኅበረሰብ ውስጥ የታዩትን አሉታዊ ታሪኮችን ካልቀየርን በስተቀር በሕዝቦቻችን መካከል ሰላም ሊኖር አይችልም” በማለት አክለዋል።

የፍትህ እና የሰላም ማኅበራዊ ስምምነት

በደቡብ ሱዳን ውስጥ ፍትህ እና ሰላም በፖለቲካ ስምምነት ብቻ ሊመጣ አይችልም ያሉት ብጹዕ አቡነ ክርስቲያን፥ ፖለቲካዊ ስምምነት አስፈላጊ ቢሆንም በቂ እንዳይደለ ገልጸው፥ እኛ የሚያስፈልገን የሰዎች ክብር እንዲጠበቅ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ፣ ከሁሉም በላይ መሠረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟላላቸው፣ የትምህርት ዕድል እና የጤና አገልግሎት እንዲሁም ለማኅበራዊ ስምምነት በጋራ መሥራት አለብን” ብለው፥ “ይህ ከሆነ ከድህነት መውጣት ብቻ ሳይሆን አሁን ከሚገኙበት መከራም ሊወጡ ይችላሉ” ብለዋል። ከዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል በመነሳት፣ ተስፋን በማድረግ በእምነት ሂደቶችን ወደ ተግባር በመቀየር፥ ሁሉም ሰው በሚፈልገው ሰላም ውስጥ መኖር እንዲችል ድፍረት እና ታላቅ ጥረት እንደሚጠይቅ ገልጸው፥ የግል ፍላጎቶችን ወደ ጎን በመተው መልካም የሆነውን ለሁሉ ሰው ማድረግ እንደሚገባ አቡነ ክርስቲያን አሳስበዋል።

በደቡብ ሱዳን የሚታይ ታላቅ ድህነት

ከባድ ፈተናዎች ያሉባት ደቡብ ሱዳን፥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እና ተፈናቃዮች የሚገኙባት፣ የኑሮ ውድነት እና ድህነት የሚታይባት፥ ከሕዝቦቿ መካከል ሁለት ሦስተኛው በረሃብ የሚሰቃይባት እና አብዛኛው ሰው መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማግኘት የማይቻልባት አገር እንደሆነች ታውቋል። “በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረውን የአየር ንብረት ለውጥ መርሳት የለብንም” ያሉት ብጹዕ አቡነ ክርስቲያን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው የካቲት ወር በደቡብ ሱዳን ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በመንግሥት ባለ ሥልጣናት ላይ አዲስ ግንዛቤ መፍጠሩን ገልጸዋል። አቡነ ክርስቲያን በማከልም ለውይይት ዕድል መስጠት በብሔራዊ አንድነት መንግሥት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ተቃዋሚ አካላት ጋርም ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት፥ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ፍላጎት ማዳመጥ እንደሚገባ፣ እያንዳንዱ ለራሱ ጥቅም ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ ማሰብን መማር እንደሚገባ ማነሳሳቱን አስረድተዋል። ሰላም ሊመጣ የሚችለው ሰላምን ከሚመርጥ ሕዝብ እንደሆነ የገለጹት አቡነ ክርስቲያን፥ በዚህም መሠረት ትጥቅ መፍታት መጀመር ያለበት ከልብ እንደሆነ እና ከዚያም የጦር መሣሪያ ትጥቅን መፍታት ላይ መድረስ እንደሚገባ ተናግረው፥ እንደ አለመታደል ሆኖ ባሁኑ ወቅት በደቡብ ሱዳን መንደሮች ውስጥ ብዛት ያላቸው የጦር መሣሪዎች እንደሚገኙ በመናገር በደቡብ ሱዳን የሩምቤክ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

19 August 2023, 16:44