ፈልግ

ለግንቦት ወር የቀረበ የጸሎት ሃሳብ ለግንቦት ወር የቀረበ የጸሎት ሃሳብ  

የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ወንጌልን በስፋት መመስከር እንደሚችሉ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለግንቦት ወር እንዲሆን ብለው ያቀረቡት የጸሎት ሃሳብ መሠረት በማድረግ፥ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ወንጌልን በሩቅ ለሚገኙትም ጭምር በስፋት መመስከር እንደሚችሉ ተገልጿል። ይህን የገለጹት፥ በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሊንዳ ጊሶኒ ሲሆኑ፣ በገለጻቸውም በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት 540,000 ወጣቶች ፍላጎታቸውን እንዳሳዩ እና ከ196 አገሮች የተውጣጡ እንዲሁም በፌስቲቫሉ ላይ በበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ለማገልገል 16,300 ወጣቶች ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለግንቦት ወር በማለት በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፥ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ለዛሬው ዓለም ስጦታ እና ሃብት ናቸው ማለታቸው ይታወሳል። የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው ስጦታ እንደሆኑ፣ “ወጣቶችን፣ ቤተሰብን እና ድሆች በማኅበራዊ መገናኛዎች እና በትምህርት አገልግሎት በኩል ወንጌልን እንዲመሰክሩ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡ ልዩ ጸጋዎች ናቸው” ማለታቸውን በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሊንዳ ጊሶኒ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።

 በሩቅ ያሉትን መድረስ

ወ/ሮ ሊንዳ ስለ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ሲናገሩ፥ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች የቅዱስ ወንጌልን እሴቶች እንደሚመሰክሩ፣ ብዙውን ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን አውዶች ርቀው የሚገኙ ሰዎችን ለማግኘት እንደሚጥሩ፣ እንክብካቤን እንደሚያደርጉላቸው እና የእምነት መንገዶችን እንዲያውቁ ድጋፍ እንደሚሆኑላቸው ገልጸዋል። ድንበሮችን በማቋረጥ ቤተ ክርስቲያን መድረስ በማትችልባቸው ቦታዎች ለሚቀበሏቸው ሕዝቦች የሚገባ ቋንቋዎችን ይዘው እንደሚደርሱ አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም በቪዲዮ መልዕክታቸው የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ አባላት ከፍተኛ የፈጠራ ችሎታ እንዳላቸው መናገራቸውን ያስታወሱት ወ/ሮ ሊንዳ፣ "ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው የፈጠራ ችሎታቸውን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ያውቃሉ" በማለት ተናግረዋል። አክለውም ዓለም አቀፋዊነት የእነዚህ ቡድኖች አንዱ መለያ ባህሪ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መናገራቸውንም አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የወጣቶች እውነተኛ ፍላጎት

ወ/ሮ ሊንዳ ጊሶኒ በቃለ ምልልሱ ላይ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ሌላው በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ሊካሄድ የታቀደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ሲሆን፣ የሚካሄደውም ከሐምሌ 25-30/2015 ዓ. ም. መሆኑን አስረድተዋል። ለዚህ "መንፈሳዊ ጉዞ" ብዙ ወጣቶች በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ወ/ሮ ሊንዳ፣ ጥቂት የአሃዝ መረጃዎችን ለመስጠት ያህል፣ እስካሁን 540,000 ወጣቶች ፌስቲቫሉን ለመሳተፍ ፍላጎታቸውን እንደገለጹ እና የሚመጡትም ከ196 አገራት መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ 16,300 ወጣቶች ፌስቲቫሉ ላይ በበጎ ፈቃደኞች ለማገልገል ፈቃደኛ መሆናቸውን እና ከ660 በላይ ብጹዓን ጳጳሳት እነዚህን ወጣቶች አጅበው እንደሚመጡ ገልጸዋል። ከመጨረሻው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በኋላ አራት ዓመታት እንደተቆጠሩ የገለጹት ወ/ሮ ሊንዳ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. በፓናማ መከበሩን አስታውሰው፣ ቀጥሎ በነበሩት ዓመታት ወረርሽኙ እና በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱት ጦርነቶች ምክንያት ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም በታላቅ የቴክኖሎጂ ዕድገት በቤታቸው እንዲቆዩ የተገደዱት በርካታ ወጣቶች እንደገና ፊት ለፊት ለመገናኘት ታላቅ ፍላጎት ያደረባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ወጣቶች የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ወደ ዓለም ለማድረስ የታዘዙ ናቸው

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ስሜት በወጣቶች ሕይወት ወስጥ መቀነሱን የገለጹት ወ/ሮ ሊንዳ ጊሶኒ፣ ነገር ግን ይህ ልምድ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በሚሰበስብበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ በልዩ መንገድ በሚሰጠው የጸጋ ስጦታ ብርታትን ሊያገኝ እንደሚችል እና ወጣቶች እግዚአብሔርን እና የምሥራቹን ቃል ወደ እኩዮቻቸው ለማድረስ የታዘዙ መሆናቸውን፣ በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ወ/ሮ ሊንዳ ጊሶኒ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል። 

17 May 2023, 16:32