ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎችን በጸሎታችን እንድናግዛቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሯቸው በጠየቁት የግንቦት ወር የጸሎት ሐሳብ፣ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና ልዩ ልዩ ማኅበራት በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሚያበረክቱት የወንጌል ተልዕኮ እና የጋራ ውይይት ለቤተ ክርስቲያንን መታደስ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት ሃሳብ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አንድ ተልዕኮ ያላቸው በርካታ ተነሳሽነቶች

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ከቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የቪዲዮ መልዕክቱ፣ በቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተለያዩ የተልዕኮ ሕይወት መኖራቸውን ገልጿል። ከእነዚህም መካከል ለምሳሌ በፖርቱጋል የስካውት ማኅበር ወጣቶች በሊዝቦን ከተማ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት መስቀል ተሸክመው የሚያደርጉትን ንግደት፣ አዲስ የትምህርተ ክርስቶስ መርሃ ግብርን የሚለማመዱ አባላት በአሜሪካ ከተሞች ጎዳናዎች ላይ በወንጌል አገልግሎት ላይ የተሰማሩትን፣ የሻሎም ሚስዮናውያን እንቅስቃሴ አባላት በማዳጋስካር እና በፊሊፒንስ የሚገኙ የአንድነት እና የነጻነት ሚስዮናውያን እንቅስቃሴ አባላት፣ በብራዚል የሚገኙ የአዲስ አድማስ እንቅስቃሴ ቤተሰቦች፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ማኅበረሰብ አባላት በኬንያ ድሃ መንደሮች ውስጥ የሚገኙ የቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ እንቅስቃሴ ቤተሰቦች፣ ሊቢያን አቋርጠው የሚመጡ ስደተኞችን የሚቀበል የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር አባላት፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ውስጥ በቆሻሻ የተበከሉ የባሕር ዳርቻዎችን የሚያጸዳ የፎኮላር እንቅስቃሴ አባላት፣በዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤው ወቅት ወደ ቅዱስ ቁርባን ፊት በመቅረብ ስግደታቸውን የሚያቀርቡ የቅዱስ ቁርባን ወጣቶች እንቅስቃሴ አባላት እና ሌሎች በርካታ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ወንጌልን በተለያዩ ቦታዎች እና መንገዶች በማወጅ ረገድ ተልዕኮአቸው አንድ መሆኑን አመልክቷል።

በቤተ ክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት መሳተፍ

የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያኗ የጋራ ጥቅም የሚሰጣቸውን ልዩ ተሰጥኦ ተቀብለው ለሐዋርያዊነት እራሳቸውን የሰጡ ሰዎች ቡድኖች ናቸው። እነዚህ ቡድኖች በዋናነት ከምእመናን የተወጣጡ አባላትን ያቀፉ ሲሆን፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነትን ለማበጀት በሚያደርጉት ፍለጋ አንድነታቸውን ያረጋግጣሉ። እንደዚሁም በወንጌል አገልግሎታቸው አማካይነት ከዘመኑ ሰዎች ጋር በየትኛውም ቦታ ውይይታቸውን ያካሂዳሉ።

እነዚህ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች እና ቡድኖች የወንጌልን ማራኪነት እና አዲስነት መግለጽ የሚችሉባቸውን አዳዲስ መንገዶች እንደሚያገኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቪዲዮ መልዕክታቸው ገልጸው፣ እንቅስቃሴዎቹ ልዩ በሚመስሉ ቋንቋዎች እና ተነሳሽነቶች አማካይነት ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያድሱ አስረድተዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከሌሎች የሚለይ መስሎ ቢታይም ነገር ግን ሁሉም ለተመሳሳይ ተልዕኮ በመተባበር አንድ እንደሆኑ፣ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ተነሳሽነትም ዋና ግቡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመገናኘት መሆኑ መዘንጋት የለበትም” ብለዋል።

የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ዓለም አቀፍ፣ ትውልድ አቀፍ እና የባለ ብዙ ጥሪዎች መድረክ ነው

በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሊንዳ ጊሾኒ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች በዛሬው ማኅበረሰቦች ውስጥ ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ስጦታ መሆናቸው ተናግረው፣ በእርግጥም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እና የወንጌልን የምሥራች ለዛሬ ትውልድ ለመመስከር የሚያስችል በየጊዜው የሚታደስ ችሎታ እንዳላቸው፣ ዓለም አቀፍ፣ ትውልድ አቀፍ እና ባለብዙ የሙያ ብቃት ያላቸው እና እራሳቸውን በዝግ ሳይወስኑ ነገር ግን ትክክለኛ የቤተ ክርስቲያን ጥሪ እና ተልዕኮአቸውን በሙላት ለመኖር የተጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከቤተ ክርስቲያን ጋር በስምምነት መጓዝ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለግንቦት ወር እንዲሆን ባቀረቡት የጸሎት ሐሳባቸው፣ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተስማምተው የመኖር አስፈላጊነትን በአንክሮ ተናግረዋል። በአባታዊ ምክረ ሐሳባቸውም የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ከጳጳሳት እና ከቁምስናዎች ጋር በመተባበር አገልግሎታቸውን እንዲያበረክቱ ጋብዘዋል። አደጋው ሊደርስ የሚችለው የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች በራሳቸው ብቻ ተወስነው ሲቀሩ እንደሆነ ተናግረዋል። እያንዳንዱ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በራሱ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ነገር ግን ፍጻሜውን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘትን የሚያበረታታ ቦታ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም ተነሳሽነታቸውን ለዓለም አገልግሎት በመስጠት” መሆኑን አስረድተው፣ አገልግሎትም በራሱ ይህን ሃሳብ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

የተልዕኮን ትርጉም በድጋሚ ለማግኘት ዘወትር መንቀሳቀስ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ፣ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በበኩላቸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ እነዚህ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች ገጽታን መሠረት በማድረግ የስተላለፉትን ሃሳብ መሠረት በማድረግ እንደተናገሩት፣ የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴዎች በወንጌል ተልዕኮአቸው ወቅት የሚያጋጣሟቸውን ተግዳሮቶች ከመንፈስ ቅዱስ በሚያገኙት እገዛ በማሸነፍ በዛሬው ዓለም ውስጥ ላሉ ለውጦች ምላሽ መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ፣ በዕለታዊ ሕይወታቸው፣ በሥራ መስክ፣ በትምህርት ዘርፍ፣ በማኅበራዊ እና ባህላዊ ዓለም ባሉ እውነታዎች ውስጥ ለመኖር እና ወንጌልን ለመመስከር ራሳቸው ብቁ ማድረግ እንዳለባቸው አደራ ብለዋል። አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ በመጨረጫም መላው ካቶሊካዊ ምዕመናን ለዚህ ጠቃሚ ዓላማ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በጸሎት መተባበር እንደሚገባ፣ የጰንጠቆስጤ በዓልን በምንጠባበቅበት በዚህ ወቅት፣ እንደ ቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ ‘የሕይወት መንፈስ፣ የእውነት መንፈስ፣ የሕብረትና የፍቅር መንፈስ ሆይ ና! ቤተ ክርስቲያን እና ዓለም ይፈልጉሃል። አንተ የሰጠሃቸው ፀጋዎች የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆኑ አድርግ!' በማለት በጸሎት እንድንተባበር በማለት መላውን ካቶሊካዊ መመናን በአደራ ጠይቀውናል።      

09 May 2023, 17:13