ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ 

ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት ወደ አንድነት መድረስ እንችላለን አሉ

የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ በመሥራት ላይ የሚገኝ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ ከጥር 10-17/2015 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ብጹዕነታቸው ከዜና አገልግሎቱ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በመልካምነት እና በፍትህ መካከል ያለውን ግንኙነት በማብራራት፣ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት አሳዛኝነት በመግለጽ የጋራ ውይይቶችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ እና ይህም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ያወረሱንን አስተምህሮን በማስታወስ፣ አንድነት የእምነት ጽንሰ-ሐሳብ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ፤...” (ኢሳ. ምዕ. 1:17) ተብሎ የተጻፈውን ጥቅስ መሪ ቃል ያደረገው የዘንድሮው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ከጥር 10-17/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆይ ታውቋል። መሪ ቃሉንም በኅብረት የመረጡት በቅድስት መንበር የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ የሚሠራ ጳጳሳዊ ጽ/ቤት እና በሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የሚገኝ የአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት መሆናቸውን ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ገልጸዋል።

“መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ” በሚለው ጥቅስ ውስጥ ሁለት ሃሳቦች እንደሚገኙ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፣ እነርሱም የክርስቲያኖች አንድነት እና ለአንድነት የሚደረግ የኅብረት ጸሎት መሆናቸውን ገልጸው፣ “እኛ ሰዎች ብቻችን አንድነትን ማምጣት ስለማንችል፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማምጣት ከጸሎት የተሻለ ነገር የለም” በማለት አስረድተዋል። “ታሪክ አሁንም እንደሚያሳየን፣ ሰዎች መከፋፈልን እና መለያየትን መፍጠር ይችላሉ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፣ አንድነት ሁል ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንደሆነ እና ይህን ስጦታ ለመቀበል ከሁሉ የተሻለ መንገድ ጸሎት መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ክርስቲያኖችን አንድ ለማድረግ በሦስት ነገሮች ላይ በርትቶ መሥራት እንደሚገባ መናገራቸውን አስታውሰው፣ እነርሱም በኅብረት መጓዝ፣ በኅብረት መጸለይ እና መተባበር መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግ በክርስቲያኖች እና በቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች መካከል ፍትህን እንደገና ማግኘት እንደሚገባ አስረድተዋል።

በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፣ “ክርስቲያኖች ሌሎች ክርስቲያኖችን ሲገድሉ መመልከት ወይም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሌሎች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ሲገድሉ መመልከት እጅግ አሳዛኝ ነው” ብለው፣ “ይህም ሃይማኖት መፍትሄ ሊሆን ሲገባው ይልቁንም የችግሩ አካል መሆኑን ያመላክታል” ብለዋል። ብጹዕነታቸው አክለውም ከዚህ አንፃር በክርስቲያኖች መካከል የሚደረግ ውይይት መቀጠል እና መጠናከር እንዳለበት፣ በክርስቲያኖች መካከል ሰላምን ለማንገሥ ከውይይት የበለጠ ሌላ አማራጭ እንደሌለ፣ የዘንድሮው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት መሪ ቃል እንደሚለው፥ የሰላም መሠረቱ ፍትህ እንደሆነ አስረድተዋል። በትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ "የፍትህ ፍሬ ሰላም ነው" የሚል እንደሚገኝ ገልጸው፣ ይህም “‘የፍትህ እና የሰላም ሥራ’ የሚለው የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ፒዮስ 12ኛ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መልዕክት በመሆኑ በጥልቀት ልናጠናው ይገባል” ብለዋል።  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ለክርስቲያኖች አንድነት በርካታ ተግባራትን ማከናወናቸውን ካርዲናል ኮክ ገልጸው፣ ቀደም ሲል እንደ ነገረ-መለኮት ምሁር፣ ከዚያም እንደ ካርዲናል እና እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ብቻ በመነጋገር ሳይሆን ከልዩ ልዩ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ጋርም ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል። በሃብስበርግ ከተማ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1999 ዓ. ም. ፍትህን በማስመልከት ይፋ ያደረጉት የጋራ መግለጫ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደ ነበር ተናግረው፣ የክርስቲያኖች አንድነት የቤተ ክህነት ፖለቲካዊ ጉዳይ ሳይሆን የእምነት ፅንሰ-ሀሳብ እንደሆነ፣ በር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ ዕይታ የክርስቲያኖች አንድነት መሠረቱ፣ እያንዳንዱ የክርስቶስ አካል የሆነው ምእመን በምስጢረ ጥምቀት ያገኘው እምነት እንደሆነ ተናግረው፣ ቅዱስነታቸው በክርስቶስ በማመን መጠናከር እንደሚገባ መፈለጋቸውን ብጹዕ ካርዲናል ኮክ ገልጸዋል። የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ የክርስቲያኖች አንድነት ፅንሰ-ሃሳብ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረተ፣ ብዙ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ተወካዮች ልባቸውን ለዚህ ፅንሰ-ሃሳብ እንዳስገዙ ተሞክሮ ማግኘታቸውን ገልጸው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት አንድነትን እንደገና ማግኘት የሚቻል መሆኑን፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ በመሥራት ላይ የሚገኝ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ አስረድተዋል።

 

23 January 2023, 13:10