ፈልግ

ዓመታዊ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ዓመታዊ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት  

“መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ፤...” (ኢሳ. ምዕ. 1:17)

ዘንድሮ የሚካሄደው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ርዕሥ፣ በአሜሪካ የሚኒሶታ ግዛት የአብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ይፋ አድርጓል። ለአንድ ሳምንት የሚቆየው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ከጥር 10-17/2015 ዓ. ም. እንደ ሆነ ምክር ቤቱ ገልጾ፣ በትንቢተ ኢሳ. ምዕ. 1:17 “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ፤...” ተብሎ የተጻፈውን የጸሎቱ መሪ ጥቅስ አድርጎ መምረጡን አስታውቋል። በተመሳሳይ ሳምንት ሮም በሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ የሚካሂደውን ዓመታዊ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሚካፈሉት ሲሆን፣ ዕለቱም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመለሰበት ዕለት መታሰቢያ መሆኑን የጸሎት ዝግጅቱ መርሃ ግብር አመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ በአሜሪካ ውስጥ የሚካሄደው ዓመታዊ የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት በይፋ የሚከፈተው ጥር 10/2015 ዓ. ም. ሲሆን አዘጋጁም 5.6 ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ያለበት የሚኒሶታ ግዛት የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት ምክር ቤት መሆኑ ታውቋል። ምክር ቤቱ በትንቢተ ኢሳ. ምዕ. 1:17 “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ፤...” ተብሎ የተጻፈውን ጥቅስ የጸሎት ዝግጅቱ መሪ ሐሳብ አድርጎ መምረጡን አስታውቋል። አስተባባሪ ቡድኑ በአውታረ መረብ አማካይነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘ ቢሆንም ብዙዎቹ ቀድሞውኑ የሚተዋወቁ እና በሚኒሶታ ግዛት የአብያተ ክርስቲያናት ቦርድ አባልነት የሠሩ፣ በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ የማኅበረሰብ አንቂ እና መጋቢ ሆነው የሠሩ መሆናቸው ታውቋል።

የጸሎት ሳምንቱን ለማዘጋጀት ስብሰባ ታካሂዷል

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች አንድነት ተንከባካቢ ጳጳሳዊ ምክር ቤት፣ በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የእምነት እና የሕግ ኮሚሽን እና ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን የጸሎት ዝግጅት የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው የሚኒሶታ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮች ከመስከረም 9-13/2015 ዓ. ም. ድረስ በስዊዘርላንድ ቦሴ ከተማ ተሰብስበው መወያየታቸው ይታወሳል። በጸሎት ሳምንት ውስጥ የሚቀርቡ ጽሑፎችን በማርቀቅ የተባበሩት አባላት ታሪካቸውን ማብራራት እና የመፍትሄ ሃሳብ ማግኘት የሚችሉ፣ የተለያዩ የአምልኮ ሥርዓቶችን እና መንፈሳዊ አገላለጻቸውን የሚያውቁ የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች፣ ነባር የአሜሪካ ተወላጆችን እና ስደተኛውን ማኅበረሰብ ያቀፈው የእናቶች እና የአባቶችን፣ የወጣት ወንዶች እና ሴቶች ስብስብ መሆናቸው ታውቋል። 

በሚኒሶታ ቡድን ውስጥ ስደተኞች እና የዘረኝነት ሰለባዎች ይገኙበታል

የቡድኑ አባላት በከተማ ውስጥ እና በከተማ ዳርቻዎች የሚገኙ በርካታ የክርስቲያን ማኅበረሰቦችን የሚወክሉ ሲሆን፣ የልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች ተወካዮች በመሪ ጥቅሱ ላይ በጥልቀት የሚያደርጉት አስተንትኖ በተለያዩ አመለካከቶች ላይ የበለፀገ የአብሮነት ልምድ እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ ታውቋል። በሚኒሶታ ግዛት ውስጥ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተወጣጡ አባላት ቡድን እንደ የዘረኝነት ሰለባ የመዋረድ ልምዳቸው የእግዚአብሔር ልጆች በጎረቤቶቻቸው ላይ ሊያደርጉት የሚችሉት ኢ-ሰብዓዊነት ምስክር እንደሚሆኑ ተስፋ አድርገዋል። የቡድኑ አባላት በማከልም “የእግዚአብሔርን የአንድነት ስጦታ የምንይዝ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ‘ሁላችንም የክርስቶስ ነን’ የሚለውን እውነት እንዳንረዳ እና እንዳንቀምሰው የሚያደርግ መለያየትን እንድናስተካክል እና እንድናስወግድ ጥልቅ ውስጣዊ ፍላጎት አለ” ብለዋል።

በጸሎት ሳምንት ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘት

ለጸሎት ሳምንቱ በወጣው መርሃ ግብር መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 10/2015 ዓ. ም. የሚያቀርቡትን የረቡዕ ዕለት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለታዳሚዎች ካቀረቡ በኋላ እሑድ ጥር 14/2015 ዓ. ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን እንደሚያቀርቡ ታውቋል። በመቀጠልም ጥር 17/2015 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ ከቀኑ አሥራ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ለክርስቲያኖች አንድነት በተዘጋጀው የጸሎት ሳምንት መዝጊያ እና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ጌታ የተመለሰበት ዕለት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን እንደሚመሩ መርሃ ግብሩ አመልክቷል።

16 January 2023, 14:44