ፈልግ

የዕድሜ ባለ ጸግነት የዕድሜ ባለ ጸግነት 

“የዕድሜ ባለጸግነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” !

በቫቲካን የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ትናንት ባወጣው ሰንዱ፣ ዕድሜ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን አስረድቶ፣ አያቶች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የሚኖራቸው የሕይወት ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል ተመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ትናንት ይፋ ባደረገው ሰነዱ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ጉዳት ምክንያት የተፈጠረው ማኅበራዊ ሕይወት ወደ ፊት ምን ሊመስል ይችላል በማለት የተለያዩ ሃሳቦችን በማቅረብ ማስተንተኑ ታውቋል።

የልማት ሞዴሉን በድጋሚ መመልከት

የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ ይፋ ባደረገው ሰነዱ ሁለት ርዕሠ ጉዳዮችን በግንባር ቀደምትነት የተመለከተ ሲሆን፣ የመጀመሪያው በሕዝቦች መካከል የሚታየው አንዱ በሌላው የመመካት እና በሕዝቦች መካከል የሚታየው ከፍተኛ የኑሮ አለመመጣጠን መሆናቸውን አስታውቋል። ሰዎች በተመሳሳይ አካባቢ ቢኖሩም የኑሮአቸው ደረጃ የተለያየ በመሆኑ በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ቀድመው የአደጋው ተጠቂ መሆናቸውን ሰነዱ ገልጿል። በመሆኑም ጳጳሳዊ አካዳሚው “ኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ጠቅላላ ሰብዓዊ ወንድማማችነት” በማለት እ.አ.አ ነሐሴ 22/2020 ዓ. ም. ያቀረበውን አስተምህሮን በማስታወስ፣ እስካሁን የተኬደበትን የልማት ሞዴል በድጋሚ መመልከት እንደሚያስፈልግ ሰነዱ አሳስቧል። ከዚህም በተጨማሪ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ እ.አ.አ ታኅሳስ 28/2020 ዓ. ም. ባወጣው ባለ ሃያ ነጥብ መልዕክቱ፣ ጤናማ እና ፍትሃዊ ዓለምን ለመገንባት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን ለሁሉ እንዲደርስ ያስፈልጋል በማለት ማሳሰቡ ታውቋል።

ኮቪድ-19 እና አረጋዊያን

የመጀመሪያው ዙር የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተለያዩ የአረጋዊያን መንከባከቢያ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ለሞት መዳረጉ የሚታወስ ሲሆን በሌላ ወገን ወደ ማዕከሉ መድረስ ያልቻሉና ከቤተሰብ ጋር የሚኖሩ እጅግ በርካታ አረጋዊያን በከፍተኛ ቁጥር ለሞት መዳረጋቸው ይታወሳል። በመሆኑም የአረጋዊያንን ሞት ለመቀነስ የሚያስችል አዲስ የአገልግሎት ዘዴን ማግኘት የሚያስፈልግ መሆኑ ተመልክቷል።

እ.አ.አ በ 2050 ዓ. ም. ዕድሜያቸው ከ 60 ዓመት በላይ የሚሆናቸው ሁለት ቢሊዮን ሰዎች ይኖራሉ

የስነ ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው ይፋ ባደረገው ሰነዱ፣ ማኅበራዊ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ ባወጣው ጽሑፉ ባሁኑ ጊዜ ወንዶችም ሆነ ሴቶች ረጅም ዕድሜን የመኖር ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አስታውቆ፣ ስለዚህ በማኅበረሰባችን ውስጥ የሚታዩ ባሕላዊ፣ ስነ-ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ለውጦችን በአንክሮ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን ያሳስባል ተብሏል። በተባበሩት መንግሥታ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው እ.አ.አ በ 2050 ዓ. ም. በዓለማች ዕድሜያቸው ከ 60 ዓመት በላይ የሚሆናቸው ሁለት ቢሊዮን ሰዎች እንደሚኖሩ አስታውቆ፣ ይህ ማለት በዓለማችን ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ በእርጅና የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ገልጿል። በመሆኑም በየአካባቢያችን እና ከተሞቻችን ውስጥ ለሚገኙት አረጋዊያን አስፈላጊውን እንክብካቤ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑ ተገልጿል።   

የዕድሜ ባለጸግነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው

ማኅበረሰባችን የዕድሜ ባለጠግነትን የብቸኝነት፣ የቤተሰብ እና የማኅበረሰብ ሸክም አድርጎ ቢመለከተውም፣ ነገር ግን፣ የዕድሜ ባለጠግነት የእግዚአብሔር ስጦታ እና የማኅበረሰቡ ትልቅ ሃብት በመሆኑ ለአረጋዊያን እንክብካቤ ሊደርግላቸው እንደሚገባ ሰነዱ አስታውሶ፣ አረጋዊያንን በሽታ ሲያጠቃቸው አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የኑሮ ደረጃቸውንም ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ሰነዱ አሳስቧል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ቃለ ምዕዳናቸው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ አረጋዊያን ለሞት መዳረጋቸውን አስታውሰው፣ ከእነዚህ አረጋዊያን መካከል በርካቶቹ በቂ እንክብካቤ ያልተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ቃለ ምዕዳናቸው፣ አረጋዊያንን የማይንከባከብ ቤተሰብ በተለይም ከአረጋዊያን ጋር ግንኙነት የሌለው ወጣት ማኅበረሰብ ብቻውን የትም መድረስ እንደማይችል አስገንዝበዋል።

ለአቅመ ደካሞች አዲስ የልማት ዕቅድ ሊዘጋጅ ይገባል

የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ በሰነዱ እንደገለጸው አቅመ ደካማ ለሆኑ አረጋዊያን አዲስ የልማት ዕቅድ እና ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጾ፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ የኑሮ ደረጃዎች ዘላቂነት ያለው የቤት ውስጥ እና የውጭ ዕርዳታዎች ለአረጋዊያን እንዲደረግላቸው አሳስቧል። የአረጋዊያን መኖሪያ ማዕከላት የአገልግሎት ደረጃቸውን ከፍ እንዲያደርጉ፣ በግል የመኖሪያ ቤቶች ለሚኖሩ አረጋዊያን የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት እንዲሻሻል፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸውን ወዳጅነትን ማሳደግ እና እርስ በእርስ የሚገናኙበትን ሥፍራ በማዘጋጀት ለጥያቄአቸው ተገቢ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ሰነዱ አሳስቧል።

በትውልዶች መካከል ግንኙነት ሊኖር ይገባል

አረጋዊያን በደካማነት ዕድሜያቸው ለተቀረው ማኅበረሰብ የሚያበረክቱት የሕይወት ልምዶች በመንፈሳዊ ሕይወት ላይ ትልቅ ድጋፍ ሊሆኑ እንደሚችል የገለጸው የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው፣ የወጣትነት ዘመን ለእግዚአብሔር ክብር የሚሰጥ መሆኑን ገልጾ፣ በዕድሜ ብዛት አቅም የሚደክም ቢሆንም፣ የማሰብ ችሎታ ቢቀንስም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነት እና መመካት ሁል ጊዜ ግልጽ መሆኑን ሰነዱ አስታውቋል።       

ለአረጋዊያን ዋጋን የሚሰጥ የባሕል ለውጥ ሊኖር ይገባል    

በመጨረሻም የስነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው በሰነዱ፣ መላው ማኅበረሰብ፣ መንፈሳዊ ባሕሎችን የሚከተሉ አብያተ ክርስቲያናት፣ የተለያዩ ባሕሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ የስነ-ጥበብ ሰዎች፣ ኤኮኖሚያዊ ተቋማት እና የማኅበራዊ መገናኛ ተቋማት አረጋዊያንን ለማገዝ የሚያስችላቸውን አዳዲስ ሃላፊነቶችን በመውሰድ እና ቆራጥ ውሳኔዎችን በማድረግ በተለይም በቤተሰብ ውስጥ ለሚገኙ አረጋዊያን እንክብካቤን የማድረግ ባሕልን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

10 February 2021, 12:26