ፈልግ

ካርዲናል ሳንድሪ፣ በኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ምስረታ 100ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተው፣   ካርዲናል ሳንድሪ፣ በኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ምስረታ 100ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተው፣  

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ “የሰላምን ታላቅነት ለሌሎች መመስከር ይገባል”።

በቫቲካን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ የተቆረቆረበትን 100ኛ ዓመት መታሰቢያ እና የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት ዓመታዊ ክብረ በዓልን በማስመልከት፣ በቅድስት መንበር የምሥራቃውያን ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያናት ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ንግግር አድርገዋል። ጥር 3/2012 ዓ. ም. በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ በዋለው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት ካርዲናል ሳንድሪ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ ሥርዓት ለተገኙት ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፣ በሁለቱ አገራት፣ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የታየው የሰላም ታላቅነት ለሌሎችም ምሳሌ ሊሆን ይገባል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ከሁለቱም አገሮች ክቡራን ካህናት ጋር ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴውን ሥነ ሥርዓት ለመሩት፣ ለብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የብሔራዊ እርቀ ሠላም ኮሚሽን ሰብሳቢ፣ ለብጹዕ አቡነ መንግሥተ አብ ተስፋ ማርያም፣ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት፣ ከሌሎችም ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ሆነው በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት፣ የአበሾች ቤተክርስቲያን ለተገኙት ክቡራን ካህናት እና ክቡራት ደናግል፣ ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች እና ለሁለቱም አገሮች ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ በቫቲካን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ፣
ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ በቫቲካን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ 100ኛ ዓመት መታሰቢያ ላይ፣

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ለተገኙት በሙሉ ባስተላለፉት መልዕክታቸው በሁለቱ አገሮች መካከል የታየውን ሰላም ለሌችም ማዳረስ እንደሚገባ አሳስበው፣ “የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ የእርሱን ታላቅነት እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው፣ በተለይም የቀን እንጀራ ለራባቸው፣ ተስፋ ለጠማቸው፣ መልካም የወደ ፊት ዕድል ለሚመኙ ወጣቶች በሙሉ፣ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን የሰላም እና የእርቅ ጸጋን መስክሩ” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስተላለፉትን መልዕክት አስታውሰዋል። ዘንድሮ የተከበረው የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት ዓመታዊ ክብረ በዓልን ልዩ ያደረገው፣ በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ የተመሠረተበት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል የተከበረበት ዕለት መሆኑ ታውቋል።

በአንድ ቀን ከተከበሩት ሁለት ደማቅ በዓላት መካከል፣ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ በርካታ እንግዶች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በቅድስት መንበር የምሥራቃውያን ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያናት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሲሪል ቫሲል፣ የሐዋርያዊ መንበር ንብረት አስተዳዳሪ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ዶሜኒኮ ካልካኞ እና በኢጣሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ክብርት ዘነቡ ታደሰ መገኘታቸው ታውቋል።

በቅድስት መንበር የምሥራቃውያን ስርዓተ አምልኮን ለሚከተሉ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያናት ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ፣ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመገናኘት፣ ታሪካዊ ጽሑፍችን በማቅረብ እና የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን በመፈጸም የተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓልን አስታውሰው። ያለፈው ቅዳሜ ጥር 2/2012 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን፣ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ቀለሜንጦስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተቀብለው ሰላምታ በተለዋወጡበት ጊዜ ባሰሙት ንግግር “በቫቲካን ከተማ ውስጥ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያዊያን መንፈሳዊ ነጋዲያን መገኘት፣ ከመቶ ዓመታት ወዲህም በኮሌጅ ደረጃ ኢትዮጵያዊያን በቫቲካን ከተማ ውስጥ መገኘት ቤተክርስቲያን እንግዳ ተቀባይ መሆኗን ይገልጻል ብለው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 15ኛ ኢትዮጵያውያን የሚስተናገዱበትን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት ማረፊያ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1919 ዓ. ም. ወደ ኮሌጅ ደረጃ ከፍ ማድረጋቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ቀጥሎም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ፣ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እንዲሆን በማለት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1930 ዓ. ም. የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት መክፈታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው፣ ከሮም ከተማ በብዙ ኪሎ ሜትሮች እረቀት የሚገኙ የእግዚአብሔር ልጆች በሐዋርያት እምነት ተቀራርበው፣ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር በሚገኝበት አካባቢ ለብዙ ዓመታት መጠለያን አግኝተው ኖረዋል” ማለታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ገልጸዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ለምዕመናን ባሰሙት ንግግራቸው፣ ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ፍቅር በተግባር እንደመሰከረ ሁሉ እናንተም “የሰላምን እና የእግዚአብሔርን ምሕረት ታላቅነት ለሌሎችም መስክሩ” ይገባል ብለው፣ ቀዳሚ ሰማዕቱ ቅዱስ እጢፋኖስ እርሱን ለገደሉት ጨካኞች የኢየሱስን ፍቅር እንደመሰከረ ሁሉ እኛም ዘወትር የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የምንመሰክር መሆን ይገባል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ንግግራቸውን ከማጠቃለላቸው አስቀድመው፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ እንዲሁም የሁላችን ጠባቂ እና ተስፋ ወደ ሆነች፣ የእግዚአብሔር እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበው፣ ሁለቱንም አገሮች፣ ኤርትራን እና ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ከፍተኛ ምኞት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
13 January 2020, 17:06