ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ጋር ሆነው፤ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ጋር ሆነው፤  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ከእንግዲህ ክፍፍል ሊኖር አይገባም”።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ታኅሳስ 2/2012 ዓ. ም. የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን፣ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ቀለሜንጦስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተቀብለው ሰላምታ ተለዋውጠዋል። ቅዱስነታቸው በቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ መቶኛ ዓመት መታሰቢያን በማስመልከት ለሁለቱ አገሮች፣ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ካህናት ደናግል እና ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፣ ጦርነት የሰው እና የንብረት መውደምን እንጂ ምንም ትርፍ አይገኝበትም ብለዋል። በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት የርካታ ሰዎች ሕይወት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ቤተክርስቲያን አሁንም ቢሆን በጦርነት እና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ለሚሰቃዩት ሐዋርያዊ እገዛዋን ማድረግ ይጠበቅባታል ብለዋል። ቅዱስነታችው በማከልም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሁለቱም አገሮች ሐዋርያዊ አገልግሎቶቿን በነጻነት የምታቀርብበት መንገድ እንዲመቻች በማለት ጥሪ አቅርበውል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን ከተማ ውስጥ ከተመሠረተ አንድ መቶ ዓመታት ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ያታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለሁለቱም አገሮች ክርስቲያኖች ያላቸውን ከፍተኛ ፍቅር በንግግራቸው ገልጸው፣ በቫቲካን ከተማ እንብርት የሚገኝ የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ፣ የምስራቅ ቤተክርስቲያ ሥርዓተ አምልኮን በቫቲካን ውስጥ የሚከተል መሆኑን አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮሌጁ ውስጥ እየተስተናገዱ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በመከታተል  ላይ ለሚገኙት ካህናት ካቀረቡት ሰላምታ በተጨማሪ፣ በስፍራው ለተገኙት ለብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል፣ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የብሔራዊ እርቀ ሠላም ኮሚሽን ሰብሳቢ፣ ለብጹዕ አቡነ መንግሥተ አብ ተስፋ ማርያም እና በቅድስት መንበር የምሥራቃውያን አብያተ ክርስቲያናት ተጠሪ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንድሪ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

በቫቲካን ከተማ ውስጥ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያዊያን መንፈሳዊ ነጋዲያን መገኘት፣ ከመቶ ዓመታት ወዲህም በኮሌጅ ደረጃ ኢትዮጵያዊያን በቫቲካን ከተማ ውስጥ መገኘት ቤተክርስቲያን እንግዳ ተቀባይ መሆኗን ይገልጻል ብለው፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 15ኛ ኢትዮጵያውያን የሚስተናገዱበትን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቀዳም ሰማዕት ማረፊያ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ 1919 ዓ. ም. ወደ ኮሌጅ ደረጃ ከፍ ማድረጋቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። ቀጥሎም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ፣ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እንዲሆን በማለት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1930 ዓ. ም. የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤት መክፈታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው፣ ከሮም ከተማ በብዙ ኪሎ ሜትሮች እረቀት የሚገኙ የእግዚአብሔር ልጆች በሐዋርያት እምነት ተቀራርበው፣ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ መካነ መቃብር በሚገኝበት ቦታ ላይ ለብዙ ዓመታት መጠለያን አግኝተው ኖረዋል ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር፣ በሐምሌ ወር 2018 ዓ. ም. በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለዚህም እግዚአብሔርን አመስግነው፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም እንዲወርድ ቀዳሚ ሚናን ለተጫወቱት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ሁለቱንም አገሮች በጸሎታቸው የሚያስታውሱት ቅዱስነታቸው፣ የተገኘው ሰላም በችግር ውስጥ ለወደቁት የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች እፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ገልጸው፣ የጋራ መሠረት ባላቸው ሁለት አገሮች መካከል ከእንግዲህ ወዲህ ክፍፍል ሊኖር አይገባም ብለዋል። ለኮሌጁ ክቡራን ካህናት ባቀረቡት ጥሪ፣ ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ስጦታ በመንፈሳዊ ትምህርቶች በማሳደግ፣ ውስጣዊውን ሆነ ውጫዊውን ቁስል በመጠገን ዘወትር የመልካም ግንኙነት ምሳሌ እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።  

በሁለቱም አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቶቿን በነጻነት የምታቀርብበት መንገድ እንዲመቻች ያስፈልጋል ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወድ የሆነው የአምልኮ ሥርዓቶቿ ሕልውና ተጠብቆላት፣ ወንጌል ለማብሰር የተሰጣትን አደራ በፍሬያማነት መፈጸም እንድትችል ዕድል ሊመቻችላት ይገባል ብለዋል።

ለስደተኞች ሐዋርያዊ እርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል፣

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ውስጥ በርካታ ሕጻናት እና ወጣቶች በድህነት ሕይወት የሚሰቃዩ መሆናቸውን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከሁለቱ አገሮች ተነስተው፣ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ባሕርን አቋርጠው ወደ ባዕድ አገር በሚሰደዱት ወጣቶች ላይ የሞት አደጋ  እና ስቃይ ደርሶባቸዋል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ እነዚህን ወጣቶች ተቀብለው መልካም መስተንግዶ በማድረግ ላይ ለሚገኙ የሁለቱ አገሮች ምዕመናን ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የእስካሁን ጥናቶችን በሥራ ላይ በማዋል፣ ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን ትሁት የሆነ የቸርነት ተግባርን ማበርከት፣ እግዚአብሔርን ልናገለግል በጀመርነው ሕይወት የበለጠ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን በተወለዱበት አገር ይሁን በተሰደዱበት አገር ማበርከት ይቻላል ብለዋል።

በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ግድግዳ ላይ የሚገኝ የኢትዮጵያዊው መንኩሴ አባ ተስፋ ጽዮን (ፔትሮ) ቃላት በቫቲካን ውስጥ ሁል ጊዜ ሲታወስ ይኖራል ብለዋል። አባ ተስፋ ጽዮን በቫቲካን በቆዩባቸው ዓመታት፣ አዲስ ኪዳንን በግዕዝ ቋንቋ ከመጻፍ አንስቶ በርካታ መንፈሳዊ የጥበብ ሥራዎችን ማበርከታቸውን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የኢትዮጵያ ጳጳሳዊ ኮሌጅ ውስጥ ለሚኖሩ የሁለቱ አገሮች ክቡራን ካህናት ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ካህናቱ በየአገሮቻቸው ጥንታዊ የአምልኮ ሥርዓትን በማስተዋወቅ እንደሚገኙ ገልጸው፣ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች፣ ከአይሁድ፣ ከእስልምና እና ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ጋር አብሮ የመኖር ባሕልን ማሳደጋቸውን ካስታወሱ በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች ለሆኑት፣ ከእነዚህም መካከል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትሪያርክ ለሆኑት ለብጹዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ ወንድማዊ ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም የሁለቱ አገሮች ምዕመናን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን ፍቅር የበለጠ እንዲያሳድጉ ብርታትን ሰጥተው ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።                 

11 January 2020, 18:02