ፈልግ

የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቫቲካን የሚገኘውን የኢትዮጲያ ኮሌጅ ጎበኙ የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቫቲካን የሚገኘውን የኢትዮጲያ ኮሌጅ ጎበኙ 

የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቫቲካን የሚገኘውን የኢትዮጲያ ኮሌጅ ጎበኙ

“ትልቅነቱን የማያውቅ ትልቅ፣ ታሪኩን የማያውቅ ትልቅ፣ ትንሽ መሆኑን አይቀርም”

የኢትዮጲያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክር አብይ አህምድ በጥር 13/2011 ዓ.ም በጣሊያን ይፋዊ ጉብኝት  አድርገው እንደ ነበረ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን ከጣሊያን ጠቅላይ ሚንስትር ከጁሴፔ ኮንቴ ጋር ከነበራቸው ቆይታ በመቀጠል በቫቲካን እንብር ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጲያ ኮሌጅ (የቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም)  መጎብኘታቸው ታውቁዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በሮም ሰዓት አቆጣጥ ከሰዓት በኋላ 3፡30 አከባቢ ከኢትዮጲያ የመጡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዐን ጳጳሳት ብጽዕ ካርዲና ብርሃነየሱስ ሊቃነ ጳጳስት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጲያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባሄ ፕሬዚዳንት፣ የአዲግራት ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ ምድኅን፣ የመቂ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ አብርሃ ደስታ፣ የጅማ ቦንጋ አገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ማርቆስ ገብረመድኅን፣ የሆሳህና አገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ስዩም፣ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት ጉባሄ ጽሕፈት ቤት የሐዋሪያዊ ሥራ አገልግሎት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ክቡር አባ ተሾመ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሐዋሪያዊ አገልግሎት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ክቡር አባ ጴጥሮስ በርጋ እና በርካታ የኢትዮጲያ ኮሌጅ ኢትዮጲያዊያን እና ኤርትራዊያን ካህናት እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ከእርሳቸው ጋር አብረው ለነበሩ ለኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚንስተር የሆኑት ክቡር አቶ ወርቅነህ ገበየውን ጨምሮ ከስድስት የማያንሱ በተለያየ የስልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ባለስልጣናትን ጨምሮ በጉብኝቱ መሳተፋቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። ቫቲካንን በመወከል በጉብኝቱ የአቀባበል ስነ-ስረዓት ላይ የተገኙት በቅድስት መንበር የምስራቃዊያን አብያተ ክርስቲያናትን ጉዳይ በበላይነት የሚከታተለው ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ካርዲናል ሌዎናርዶ ሳንዲሪ ጨምሮ የቀድሞ በኢትዮጲያ የቫቲካን አንባሳደር የነበሩ የእኔታ ቶማሲ ዚልቫኖ መገኘታቸውን ለመረዳት ተችሎዋል።

በግንኙነቱ ወቅት በቅድሚያ የእንኳን ደኽና መጣችሁ መልእክት ካስስተላለፉት ከብጽዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቃነ ጳጳስት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጲያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት በመቀጠል ንግግር ያደርጉት የኢትዮጲያ ፈዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፖብሊክ ጠቅላይ ሚንስተር የሆኑት ዶክተር አብይ አህመድ በንግግራቸው ወቅት እንደ ገለጹት “በቫቲካን ውስጥ የሚገኘውን የኢትዮጲያ ኮሌጅ በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ” መግለጻቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመልክታል።

“የኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጲያ ታላቅ አገር መሆኑዋን ደግማ አሳይታናለች” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉ ጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ አህመድ “ይህ የታላቅነት መገለጫ የሆነ ስፍራ በሚገባው እና ተገቢ በሆነ ሁኔታ ስላልተነገረለት ሰፊው ሕዝብ ብዙም እንደ ማያውቀው” ገልጸው ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ብዙን ጊዜ ስለ ሰላም እና ስለ አንድነት ሲያስተምሩ እንደ ሚሰማ” ክቡር ጠቅላይ ሚንስተር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸው በተጨማሪም “ስለእነደዚህ ዓይነቱ ታሪካዊ ስፍራ ቢነገር መልካም እንደ ሆነ” ጨምረው ገለጸዋል።

“ትልቅነቱን የማያውቅ ትልቅ፣ ታሪኩን የማያውቅ ትልቅ፣ ትንሽ መሆኑን አይቀርም” በማለት ንግግራቸውን የቀጠሉት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተ አብይ አህመድ “እኛ ኢትዮጲያዊያን ብዙ ነገሮች ያሉን ሰዎች ብንሆንም ቅሉ ያሉንን ነገሮች እንኳን በቅጡ ስለማናውቃቸው፣ እንደ ምታውቁት በችግር ውስጥ ሆነን እንድንቆይ ተገደናል” ብለዋል።

“አባቶቻችን ብዙ ቦታ ሄደዋል፣ ኢየሩሳሌም ሄደዋል፣ እዚህም (ቫቲካን) መተዋል፣ ወደ መካ ሄደዋል፣ በዚህም ተግባራቸው ታሪክ ጥለው አልፈዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አመድ “እኛ አሁን ያለን ሰዎች ግን እንኳን ታሪክ ልንሰራ እነርሱ የሰሩት ታሪክ እንኳን ለማየት ጊዜ የለንም” ብለው “አሁን ይህንን የሚያህል ትልቅ ነገር ኢትዮጲያ በቫቲካን ውስጥ እንዳላት ከመቶ ሚልዮን ሕዝቦች ውስጥ ስንቱ ስለዚህ ስፍራ እንደ ሚያውቅ ማወቅ እንደ ሚችግር” ገልጸዋል።

“እኔ ዛሬ በዚህ ጉብኝት ትልቅ ትምህርት አግኝቻለሁ አገራችን ታላቅ ናት፣ ታላቅነትዋ ማስጠበቅ እና ማስቀጠል የእኛ የልጆቹዋ ድርሻ መሆኑን ገልጸዋል፣ ቀደም ሲል እንደ ተጠቀሰው የካቶሊክ ቤት ክርስቲያን ስለሰላም እና ስለአንድነት ስታስተምር መቆየቷ ዋና ማረጋገጫ የሚሆነው በወንድም የኢትዮጲያ እና የኤርትራ ሕዝቦች መካከል ጊዜያዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ ቤተ ክርስቲያን ግን እነዚያን ችግሮች ስትቀበል እንደ ወንድማማቾች ሆናችሁ መኖራችሁ በጣም ትልቅ የሆነ ትምህር እንደ ሆነ” ገልጸዋል።

“ኢትዮጲያ እና የኤርትራ ሕዝቦች አንድ የሆኑ ሕዝቦች መሆናቸውን፣ ይህ በጊዜያዊነት የተከሰተ ችግር ፖለቲካዊ በሆነ መልኩ እንደ ሚቀየር” የገለጹት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ወንድማማች ሕዝብ መሆናችንን ግን ሁሌም ማስታወስ ያስፈልጋል” ብለዋል።

“በኢትዮጲያ እና በኤርትራ መካከል በተለየ መልኩ ድንበርን በተመለከተ ችግር ሊፈጠር እንደ ማይገባ” የገለጹት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ቫቲካንን ከመጎብኘታቸው በፊት ከጣሊያን ጠቅላይ ሚንስተር ጁሰጴ ኮንቴ ጋር አድርገውት የነበረውን ቆይታ በማስታወስ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ካደርጉት ውይይት መካከል አንዱ “ምጽዋን እና መቀሌን እንዴት ማገናኘት እንዳለብን ተወይይተን ነበር” ካሉ በኋላ “ማነኛውንም ዓይነት ልማትን በተመለከት ውይይቶች በሚደረጉበት ወቅት ኤርትራን ባማከለ መልኩ እንደ ሆነ ገልጸው የእኛው ሕዝብ የእኛው ወንድሞች በመሆናቸው የተነሳ አብረን ማደግ አለብን የሚል እምነት” እንዳላቸው ጨምረው ገለጸዋል።

“ኤርትራ አድጋ በልጽጋ ቢሆን ኖሮ ሰዎቻችን ወደ ዱባይ ባልሄዱ ነበር፣ ዱባይ ከሚሄዱ ይልቅ ኤርትራ ይቀርበን ነበር፣ ኢትዮጲያ አድጋ በልጽጋ ቢሆን ኖር ኤርትራዊያን ወደ ሌላ አገር ከሚሄዱ ይልቅ ኢትዮጲያ ይቀርባቸው ነበር፣ አብረን ማደግ መበልጸግ ስለምንችል የሁለቱም አገር ሕዝቦች አንድንነት፣ የሁለቱ አገር መንግሥታት ትብብር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይቀጥላል” ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ይህን የሚያጸናው እግዚኣብሔር ነው፣ ይህም እውን የሚሆነው በእናንተ ጸሎት ነው፣ ከእናተ የምንፈልገው ደግሞ ስለሰላም፣ ስለአንድነት፣ ስለአብሮነት ጸሎት እንድታሰቡን ነው” ብለዋል።

“ይህንን ታላቅ ታሪክ አቆይታችኋል፣ ልጆቻችንን እንድታስተምሩ እና እንድታስቀጥሉ፣ ይህንን ካደረጋችሁ ደግሞ ኃልፊነታችሁን ተወጥታችኋል ማለት ነው፣ እኔ በጣም በጣም ኮርቼባችኋለሁ፣ ኢየስሩሳሌምን ለማየት እድል አግቻለሁ፣ ነገር ግን እንዲህ ሆኖ አላገኘሁትም ነገር ግን ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመነጋገር እርሱንም እንደዚህ እናደርገዋልነን፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ታሪክ ነው፣ ይህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ታሪክ ነው፣ ይህ ቤተ ክርስቲያን ሲጠራ ኢትዮጲያ ትጠራላች፣ ኢትዮጲያ ደግሞ የማይመለከተው ሰው የለም፣ የጋራ ታሪካችንን ስላቆያችሁልን እግዚኣብሔር ያክብራችሁ፣ ይህ ተግባራችሁ እንዲቀጥል እየጠየኩኝ፣ በጣም ደስተኛ መሆኔን በመምጣቴ ትልቁ ደስታዬ ይህንን ስፍራ ማዬቴ መሆኑን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ አመሰግናለሁ” ብለዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ንግግራቸውን ካበቁ በኋላ ከዚህ ቀደም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በቫቲካን የሚገኘውን የኢትዮጲያ ኮሌጅ በጎበኘቡት ወቅት ፒያኖ የሙዚቃ መሳሪያ በስጦታ መልክ ካበረከቱ በኋላ ፊርማቸውን ባኖሩበት የክብር መዝገብ ላይ ጠቅላይ ሚንተር ዶክተር አብይ አህመድ ካሳረፉ በኋላ በኮሌጁ የሚገኙትን ኢትዮጲያን እና  ኤርትራዊያን ካህናትን፣ እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶችን ሰላም ካሉ በኋላ ቀጣዩን የቫቲካን ጉብኝት ለማድረግ እና ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ጋር ለመገናኘት ወደ እዚያው ማቅናታቸው ታውቁዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
22 January 2019, 16:22