ፈልግ

2018.10.04 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 2018.10.04 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 

15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻ ሰነዱን ይፋ አደረገ።

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ሰብሳቢ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ እንደገልጹት የመጨረሻ ሰነዱ በእርግጥ የሲኖዶሱ አባቶች ከሌሎች የጉባኤው ተካፋዮችና በተለይም ከወጣቶች ጋር የተደረገ የጋራ ውይይት ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ በማከልም መጨረሻ ሰነዱ 364 ገንቢ የሆኑ የማሻሻያ ሃሳቦች የታከሉበት እንደሆነ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

15ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላላ መደበኛ ጉባኤ፣ በወጣቶች ጉዳይ ላይ የተወያየበትን የመጨረሻ ሰነድ ይፋ ማድረጉ ተገለጸ። በቫቲካን ከተማ ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ ወጣቶች፣ እምነት እና ጥሪያቸውን ጥበብና ማስተዋል በተመላበት መንገድ ተገንዝበው ትክክለኛ ውሳኔን እንዲያደርጉ በሚል ርዕስ ሲካሄድ የሰነበተው 15ኛ የጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ትናንት እሑድ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ. ም. የሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ መገባደዱ ታውቋል። የሲኖዶሱ ብጹዓን አባቶች፣ ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2011 ዓ. ም. ባካሄዱት 22ኛ ዙር ጠቅላላ ጉባኤው 12 ምዕራፎች ያሉት ባለ 60 ገጽ የመጨረሻ ሰነድ ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድ አቅርበው፣ ቅዱስነታቸው እንዲታተም ብለው ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ታውቋል። 

ብጹዓን ሲኖዶስ ያዘጋጀው የመጨረሻ ሰነድ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ፣ ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩ ሐዋርያትን በማስመልከት የጻፈውን የወንጌል ክፍል ያስታወሰ መሆኑ ታውቋል። የሲኖዶሱ የመጨረሻ ሰነድ አስቀድሞ ለውይይት በቀረበው የመወያያ ርዕስ ላይ ተጨማሪ ሃሳብ የታከለበት እንደሆነ ሲገለጽ፣ ለጉባኤው በንባብ ያቀረቡትም የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ሰብሳቢ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ፣ በልዩ ዋና ጸሐፊዎቻቸው የሆኑት ክቡር አባ ጃኮሞ ኮስታ፣ ክቡር አባ ሮዛኖ ሳላ እና የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ምክር ቤት አባል የሆኑት ብጹዕ አቡነ ብሩኖ ፎርቴ መሆናቸው ታውቋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ሰብሳቢ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ እንደገልጹት የመጨረሻ ሰነዱ በእርግጥ የሲኖዶሱ አባቶች ከሌሎች የጉባኤው ተካፋዮችና በተለይም ከወጣቶች ጋር የተደረገ የጋራ ውይይት ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮካ በማከልም መጨረሻ ሰነዱ 364 ገንቢ የሆኑ የማሻሻያ ሃሳቦች የታከሉበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ከእነርሱ ጋር ይጓዝ ነበር፣

የብጹዓን ጳጳሳት መጨረሻ ሰነዱ የመጀመሪያ ክፍል ወጣቶች አሁን የሚገኙበትን የኑሮ ሁኔታ፣ ጥንካሬንና ተግዳሮቶችን ያስታወሰ እንደሆነ ታውቋል። ይህም ከወጣቶች የሚቀርቡ ሃሳቦችንና አስተያየቶች፣ ትህትናና ትዕግስት በተሞላበት መንገድ  በማዳመጥ የተዘጋጀ ሰነድ እንደሆነ ታውቋል። ወጣቶች ተደማጭነት እንዲኖራቸው፣ እውቅናን እንዲኖራቸው፣ አብሮአቸው የሚሆን የሕብረተሰብ ክፍል እንዲኖራቸው፣ የሚያቀርቡት ሃሳብና አስተያየት በሕብረተሰብና በቤተክርስቲያን ውስጥ ዋጋና ትኩረት እንዲሰጠው መፈለጋቸው በጳጳሳት ሲኖዶስ ተገልጿል። ብዙን ጊዜ ካህናትና ጳጳሳት በሌሎች የቤተክርስቲያን አገልግሎቶች በመያዛቸው የተነሳ ለወጣቶች በቂ ጊዜን ሰጥተው ለማዳመጥ ይቸገሩ እንደነበር የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ገልጿል። ይህን ችግር ለማቃለል ወጣቱን ትውልድ የሚከታተልና የሚያዳምጥ ከምዕመናን መካከል ወንዶችንና ሴቶችን ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ አስተያየታቸውን አቅርበዋል። ወጣቱ ትውልድ በዘመናችን ከሚንጸባረቀው የግሎባላይዜሽንና የዓለማዊነት ክስተቶች ባሻገር እግዚአብሔርን ለማወቅና መንፈሳዊነትን ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት፣ ለቤተክርስቲያን እድገትና የእምነታቸውን አስፈላጊነት ጠንቅቀው ለማወቅ ትልቅ እገዛ አለው በማለት የሲኖዶሱ አባቶች ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶችና ቁምስናዎች፣

ቤተክርስቲያን ለወጣቶች ጥያቄ መልስ ከሰጡባቸው መካከል አንዱ የትምህርት ጉዳይን የተመለከተ ሲሆን ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና ሌሎችም በቤተክርስቲያን የሚተዳደሩ የትምህርት ተቋማት ለወጣቶች የሚሰጡትን የትምህርት ዘርፎችን በማስፋት ለሰዎች ሁለንተናዊ እድገት በተጨማሪ በወንጌል ምስክርነትም ስልጠናን በመስጠት ወጣቶችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አስረድቷል። የተለያዩ ማሕበራዊ ተቋማትን በሚያሳትፉ ጉዳዮች ከእነዚህም መካከል ቤተሰብን፣ ሥራን፣ ቴክኖሎጂን፣ ጸረ ጽንስ ማስወረድን፣ ፍልሰትንና በሌሎች ማሕበራዊ ጉዳዮችም ለወጣቶች ግንዛቤን ለመስጠት ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም የትምህርት ተቋማት እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አስገንዝቦ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የትምህርት ተቋማት በእምነትና ወቅታዊ በሆኑ ጥያቄዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በማብራራትና በማስረዳት፣ የሰው ልጅ ማሕበራዊ አመለካከቶችን፣ ሳይናሳዊ ዘዴዎችን፣ ማሕበራዊ የኑሮ ወግንና ፍትህንም በማስመልከት ወጣቶችን ለማስተማርና ለማነጽ ተጠርታለች ብሏል። በየአካባቢው የሚገኙት ቁምስናዎች የተጠሩበትበትን የተልዕኮ ጥሪን በድጋሚ በማስታወስ ለምእመናን የሚሰጡትን የአገልግሎት ጥራትና ይዘት በማሳደግ፣ በተለይም በትምህርተ ክርስቶስ አሰጣት ላይ ትኩረት በመስጠት ፍሬያማ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ እነደሆነ አሳስበዋል።

ስደተኞች የዘመናችን ንድፍ ናቸው፣

የስደተኞችን ጉዳይ በተመለከተ ሃሳቦችን ያካተተው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻ መልዕክት፣ ስደት በዘማናችን እየተስፋፋ የመጣ ማሕበራዊ ክስተት እንደሆነ አስረድቶ፣ በጦርነት፣ በአመጽ፣ በፖለቲካ አቋማቸውና በእምነታቸው ምክንያት፣ በተፈጥሮ አደጋና በድህነት ምክንያት የሚሰደዱት በወጣትነት ወይም በልጅነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት እንደሆኑ    አስታውሶ፣ እነዚህ ወጣቶች መጨረሻቸው በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋር ወንጀለኞች እጅ እንደሚወድቁ፣ የአደንዛዥ እጾች ተጠቂዎች፣ ስነ ልቦናና የሰውነት ጉዳት እንደሚደርስባቸው ሲኖዶሱ ገልጿል። ከአገራቸው ለሸሹት፣ ከወላጆቻቸው ለተለዩት በርካታ ወጣቶች ቤተክርስቲያን የምታደርገው ርሕራሄ ትልቅ በመሆኑ፣ ወጣቶቹ በሚደርሱባቸው አገሮች መልካም አቀባበል ተደረጎላቸው የተሟላ አገልግሎቶችን የሚያገኙባቸው ተቋማት እንዲከፈትላቸው፣ በእነዚህ ተቋማት አማካይነት እውነተኛ ሰብዓዊ እድገትን የሚያመጡበት መንገድ መዘጋጀት እንዳለበት የጳጳሳት ሲኖዶስ በመልዕክቱ አሳስቧል።  ሲኖዶሱ በማከልም ሰደተኞች ለሚኖሩበት አገር ትልቅ ሃብት ሊሆኑ እንደሚችሉ በመገንዘብ ስደተኛ ተቀባይ አገሮች ስደተኞችን በክብር ተቀብለው እንዲያስተናግዱአቸው፣ ለደህንነታቸው ሕጋዊ ከለላን በመስጠት፣ የአገሩን ባሕልና ስርዓት ተንቅቀው እንዲያውቁ በማገዝ በማሕበራዊ ሕይወት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግና ራሳቸውን የሚችሉበትን ዕድል በክፈት ኣንዳለባቸው አሳስቧል። የጳጳሳቱ ሲኖዶስ በተጨማሪም በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ስደትና መከራ የሚደርስባትን ቤተክርስቲያን በማስታወስ ከስደትና ከመከራ ለማምለጥ ብለው ሳይወዱ ተገደው የሚሰደዱትን በርካታ ምእመናን እንዳሉ አስታውሷል።

በሁሉም የጥቃት አይነቶች ላይ ጽኑ አቋምን በመውሰድ፣ እውነትን አጣርቶ በማውጣት ምሕረትን መጠየቅ፣

ስልጣንን፣ ገንዘብንና ሕሊናንም ያለ አግባብ በመጠቀም እንዲሁም በተለያዩ ጾታዎች ላይ ስለሚደርሱት ጥቃቶች ልዩ ትኩረትን የሰጠው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ የጥቃቱ ሰለባ በሆኑት ግለሰቦች ላይ ሊደርስ የሚችል፣ ረጅም ጊዜን የሚወስድ የስነ ልቦና ቁስል እንደሚደርስባቸው አስታውሰዋል። ይህን የመሰለ ጥቃት ለመከላከልና እንዳይደገም የሚያደርግ ደንብ ማውጣት፣ ተግባራዊነቱንም የሚከታተል ክፍል ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብሏል። ጥቃቱን የፈጸሙ ግለ ሰቦችን ወደ አደባባይ ማውጣቱ ቤተክርስቲያን የራሷን ውሳኔ ለማስተላለፍ እጅግ እንደሚረዳት ገልጾ ይህን ለማከናወን እውነተኛ መረጃን በማቅረብ የተባበሩትን ሰዎች ከልብ አመስግኖ፣ ምሕረትን ለማድረግ ፍትህ እንዲኖር ያስፈልጋል ብሏል። በሌላ ወገን ከምዕመናን፣ ከካህናት፣ ከገዳማዊያንና ከጳጳሳት መካከል ሕይወታቸውን ለቤተክርስቲያንና ለወጣቶች አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ አገልግሎት ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን ማዘንጋት እንደማያስፈልግ አሳስቧል።

ቤተስብን ማሰብ ያስፈልጋል፣

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የመጨረሻ ሰነድ ካካተታቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ወጣቶች የሚገኙበት የቤተሰብ ክፍል እነደሆነ ያስታወሱት የብጹዓን ጳጳሳት፣ ቤተሰብ እምነት የሚገልጽበት ቀዳሚ ማዕከል እንደሆነ አስታውሰዋል። በቤተሰብ ውስጥ የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት አባቶችና እናቶች የእምነት እሴቶችን ወደ ሌሎች ዘንድ በማስተላለፍ ረገድ የሚጫወቱት ትልቅ ሚና እንዳላቸው አስታውሰዋል። በወጣቶች መካከል እምነትን በማሰራጨት ከፍተኛ ምስክርነትን የሚሰጡ የዕድሜ እኩያዎች እንደሆኑ የሲኖዶሱ ብጹዓን ጳጳሳት አስታውሰዋል።

በድህነት ምክንያት የሚመጣውን ማግለል በመቃወም ፍትህ ማንገስ፣

ወጣቶች ስራ በማጣት ምክንያት በሚደርስባቸው ድህነት፣ በዘርና በጎሳ ልዩነት ምክንያት በሚደርስባቸው መገለል፣ የአካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ምክንያት ከሕብረተሰቡ መካከል እንደሚገለሉ፣ ቤተክርስቲያን እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች በመገንዘብ በሕብረተሰብ መካከል አንድነትና መተጋገዝ እንዲሰፍን የሚያደርግ ጥሪን በማስተላለፍ የበኩልዋን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባት አሳስበዋል። ቤተክርስቲያን ይህን ጥሪ ስታደርግ ወጣቶች በተግባር እንዲገለጹላቸው በስፋት የሚያቀርቡት ጥያቄዎች ከእነዚህም መካከል በፈቃደኝነት የሚቀርቡ የበጎ አገልግሎት ተግባራትን፣ የአካባቢ ጥበቃን፣ ለማሕበራዊ ጥቅም የሚበጁ የፖለቲካ ስርዓትን በገንባት፣ የፍትህ ግንባታን ማካተት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። 

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ

     

29 October 2018, 15:34