ፈልግ

2018.10.05 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 2018.10.05 Congregazione Generale Sinodo dei Vescovi 

ወጣቶችን በጥሪያቸው ለማገዝ፣ ቤተክርስቲያን ከቤተሰብ ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመስከረም 23 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ከተማ 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ የሚገኝው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ወጣቶች ጥሪያቸውን በጥበብና በማስተዋል እንዲገነዘቡ ለማድረግ ቤተክርስቲያንና የቤተሰብ ክፍሎች በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ ሃሳብ መቅረቡ ታውቋል። ከጳጳሳቱ ሲኖዶስ የተወጣጡት 20 መንፈሳዊ አባቶች የመወያያ ርዕሶችን ተከትለው ባቀረቡት የመጀመሪያ  ዝግጅታቸው እንደገለጹት ወጣቶችን በጥሪያቸው ማገዝ እንዲቻል ቤተክርስቲያንና ቤተሰብ መተባበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የጳጳሳት ሲኖዶስ “ዛሬ ብዙ ሰዎች ስለ ወጣቶች ያወራሉ እንጂ ከወጣቶች ጋር አያወሩም” ያሉትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ 6ኛን ንግግር አስታውሷል። በጳጳሳቱ ሲኖዶስ ሰፊ ውይይት የተደረገበትና ቤተክርስቲያን ከቤተሰብ ጋር በመደጋገፍ መስራት እንደሚያስፈልግ በሚያሳስብ ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ሌላው ርዕሥ ወጣቶች አሁን በደረሱበት የዲጂታሉ ዓለም በመማረክ መጠነ ሰፊ በሆነ የመረጃ ፍሰት ላይ በመውደቅ ትክክለኛ ማንነትንና አቋምን ወደ ማጣት ደረጃ እንዳይደርሱ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል። ዲጂታሉ ዓለም ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ገጽታ ብቻ መመልከት ሳይሆን ወጣቶች በዲጂታሉ ዓለም ማሕበራዊ የመገናኛ መንገዶችን በመጠቀም ጓደኝነትን፣ አንድነትን፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን፣ እውነተኛ የሕይወት ምስክርነትን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ማስተባበርን፣ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎቷን በደስታና በብቃት እንድታበረክትላቸው ጥያቄዎችን ለማቅረብ እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።

ከጎልማሳ ምዕመናን ጋር ገንቢ ውይይት ሊኖር ይገባል፣

ወጣቶች፣ ጊዜን ሰጥተው የሚያዳምጧቸው፣ በፍቅርና በአክብሮት የሚቀርቧቸው፣ ጥሪያቸውን በትክክል እንዲገነዘቡ የሚያግዙ ጎልማሶችን ይፈልጋሉ ያለው የጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ይህን ያሉበት ምክንያት ከጎልማሶች መካከል ወጣቶች በሕብረተሰቡ መካከል ሊኖራቸው የሚገባቸው ተቀባይነትን የሚከለክሉና ወጣቶችን ወደ ተሳሳት አቅጣጫ የሚመሩ እንዳሉ በመገንዘባቸው ነው ብለዋል።

የአምልኮ ሥርዓትና የቅዱሳት ምስጢራት ጥቅም፣

ወጣቶች በቤተክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጎለብቱባቸው እንቅስቃሴዎች ሊኖሩ ይገባል ያሉት የጉባኤው ጳጳሳት፣ ለወጣቶች በሚስማማ መንገድ የተዘጋጁ የአምልኮ ስርዓቶችን ማስተዋወቅ ወይም መዘርጋት እንደሚያስፈልግ አስታውሰው፣ የአምልኮ ሥርዓትን በተመለከተ ወጣቶች የሚደሰቱበትና የሚሳተፉበት የመዝሙር አገልግሎት እንዲኖር አሳስበዋል። በትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ በወንጌል ስብከትና በጋራ በሚቀርቡ ጸሎቶች ላይ ተመሳሳይ ትኩረት እንዲሰጥበት አሳስበዋል። በካህናት በኩል የሚቀርቡ የቅዱስ መጽሐፍት አስተንትኖዎች ወይም ስብከቶች የወጣቶችን ልብና አዕምሮ በመማረክ ለእምነት የሚያበቁ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል። ወጣቶች እነዚህን የመሳሰሉ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ለጓደኞቻቸው በማቅረብ የወንጌል መስካሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ቤተክርስቲያን ማንነቷን የምታውቀው ወጣቶች በቤትክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ለውጥን፣ በመላው ዓለም ሰላምን ማምጣት እንደሚችሉ ስትገነዘብ ነው ብለዋል።

በውጣቶች ዘንድ ብቸኝነት ነግሷል፣

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በማከልም ዛሬ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ወጣቶችን ወደ ቁምስናዎች ይመጣሉ ብለው በማሰብ እጅና እግር ሰብስበው መቀመጥ የለባቸውም ብለው ለውጣቶች የሚገባው ሐዋርያዊ አገልግሎት ወይም ወጣቶችን ማግኘት የሚቻለው ወጣቶች ወደሚገኙበት ሥፍራ በመሄድ እንደሆነ  አሳስበዋል። ወጣቶችን በማሕበራዊ ሚዲያ በኩል ለመቅረብና ለማግኘት ቢሞከርም ይህ ዘዴ ወጣቶችን ከብቸኝነት ስሜት ሊያላቅቅ አልቻለም። ቤተክርስቲያን ልትሰጥ የምትችለውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ሙሉ ሊያደርገው አልቻለም። በትምህርት አሰጣጥ ሂደት ወጣቶች ትክክለኛ የሕይወት አቅጣጫን እንዲከተሉ፣ ምንም እንኳን ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመጡ ባያደርግም የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተመራጭ የትምህርት አሰጣት መንገድ መከተል፣ የማሕበራዊ አስተምሮ አስፈላጊነትንና ጥቅምን ለወጣቶች ማስረዳት ያስፈልጋል። 

የቤተክርስቲያንና የቤተሰብ አንድነት፣

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ በአንክሮ የተመለከተው ሌላው ጉዳይ፣ ወጣቶችን በጥሪያቸው ማገዝ እንዲቻል ቤተክርስቲያንና ቤተሰብ መተባበር ያስፈልጋል የሚል ሲሆን ከለጋ ዕድሜአቸው አንስቶ እስከ ወጣትነት ዕድሜ ድረስ ቤተሰብ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩና እንዲከታተሉ ያስፈልጋል ብሏል። ይህን ለማድረግ በክርስቲያናዊ ጋብቻ የተዋቀረ ቤተሰብ እንደሚያስፈልግ የጳጳሳት ሲኖዶስ እምነቱን ገልጿል። ወጣቶች መልካም ስነ ምግባር እንዲኖራቸው ቤተሰብ የመጀመሪያ ትምሕርት ቤት በመሆን ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ ያለው የጳጳሳቱ ሲኖዶስ፣ የወላጅነትን ሚና በትክክል ለመወጣት፣ ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ በመሆን፣ እምነታቸውን በማውረስ፣ ልጆቻቸው በማንነታቸው እርግጠኛ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ሃላፊነት የሚሰማው ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ሊኖር እንደሚገባ አሳስቧል።

ስደተኞችንና ተፈናቃዮችን ተቀብሎ ማስተናገድ፣

በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መካከል ከተደመጡ ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ በተለያዩ ማሕበራዊ ቀውሶች ምክንያት ተፈናቅነው ለስደት የተዳረጉ ወጣቶች ጉዳይ ሲሆን እነዚህ ስደተኞችም ሆነ ተፈናቃይ ወጣቶች ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት ሰብዓዊ ክብራቸውን እንደሚያጡ የተገለጸ ሲሆን ስደተኞችን በክብር ተቀብሎ  ማስተናገድ፣ ከደረሱበት አገር ማሕበረሰብ ጋር ተስማምተውና ተከባብረው መኖር የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ፣ ስደተኞች በብዛት የሚወጡባቸው አገሮች መግሥታት ድህነትን፣ ጦርነትን፣ አመጽንና ማንኛውንም ማሕበራዊ ቀሶችን ለመቀንስ ጥረት በማድረግ፣ ሕዝቦቻቸው በሰላም የሚኖሩበት አገር ለማድረግ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ወጣቶችን የማዳመጥ አገልግሎት፣

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ንግግራቸውን ያዳመጧቸውና የማዳመጥ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙ በፈረንሳይ የቴዜ ክርስቲያናዊ ማሕበር ተንከባካቢ የሆኑት ወንድም አሎዊስ ሲሆኑ፣ እርሳቸው እንደገለጹት ቤተክርስቲያን ተከታዮችዋን ማዳመጥ ስትጀምር የፍቅር ምሳሌ ትሆናለች ብለዋል።                                      

06 October 2018, 19:19