ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከህመማቸው አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸው ተገለጸ! ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከህመማቸው አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸው ተገለጸ!  (Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከህመማቸው አገግመው ከሆስፒታል መውጣታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ ከሄርኒያ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በሮም ከተማ በሚገኘው ጄሜሊ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና ከተደረገላቸው በኋላ ከሆስፒታል ወጥተው አርብ ጠዋት ሰኔ 09/2015 ዓ.ም ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል።

የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሆስፒታሉ ሲወጡ መኪናቸውን ለአጭር ጊዜ አስቁመው በቦታው ለተገኙት ሰዎች ሰላምታ ማቅረባቸው ተገልጿል።

የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር ማትዮ ብሩኒ ሐሙስ ሰኔ 08/2015 ዓ.ም በሰጡት አጭር መግለጫ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት ከሆስፒታል እንደሚወጡ ለጋዜጠኞች አስታውቀው እንደ ነበረ ይታወሳል።

ወደ መደበኛ ሁኔታ በመመለስ ላይ

ማቴው ብሩኒ የሊቀ ጳጳሱን የጤና ሁኔታ የሚያረጋግጡ መደበኛ መግለጫዎችን መስጠት መቀጠላቸው የሚታወስ ሲሆን የሕክምና ቡድኑን ሪፖርቶችን በተከታታይ በመግለጽ የቅዱስነታቸው የጤና ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንደመጣ እና "ከቀዶ ጥገና በኋላ ያለው ሁኔታ እየተሻሻለ” መምጣቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

የሰኔ 01/2015ቱን ቀዶ ጥገና ተከትሎ የጳጳሱ የቀዶ ጥገና ሃኪም ፕሮፌሰር ሰርጂዮ አልፊየሪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ምንም አይነት ችግር እንዳልተፈጠረ ገልጸው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመጨረሻ መደበኛ ተግባራቸውን እንደሚቀጥሉ ቢጠበቅም ከባድ ዕቃዎችን ማንሳት እንደሌለባቸው ግን ተናግረዋል ።

በቀዶ ጥገናው እና በቀጣይነት ቅዱስነታቸው ማገገም ምክንያት፣ የጳጳሱ አስተምህሮዎች እና መደበኛ ተግባራት እስከ ሴን 11/2015 እሁድ ድረስ መደበኛ ተግባራቸውን እንደ ማያከናውኑ ተገልጿል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እ.አ.አ ከነሐሴ 2 እስከ ነሐሴ 6/2023 ድረስ የዓለም ወጣቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ወደ ፖርቱጋል እና ከእዚያም በመቀጠል እ.አ.አ ከነሐሴ 31 እስከ መስከረም 04/2023 ዓ.ም ድረስ ወደ ሞንጎሊያ በመሄድ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደ ሚያደርጉ ይጠበቃል።

በጂሜሊ የተደረገላቸው እንክብካቤ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቆይታቸውም የሕክምና ባለሙያዎች ላደረጉት ሙያዊ ብቃት እና "በመድሀኒት ብቻ ሳይሆን በጨዋነት እና በሰብአዊነት የሌሎችን ስቃይ ለማቃለል" ላደረጉት ጥረት ሁሉንም የህክምና ባለሙያዎች አመስግነዋል።

በሮም ውስጥ ትልቁ ሆስፒታል የአጎስቲኖ ጂሜሊ ዩኒቨርሲቲ ፖሊክሊኒክ ለካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት የማስተማር አገልግሎት ጭምር የሚሰጥ ሆስፒታል ነው።

ሆስፒታሉ የተሰየመው ዶክተር እና የስነ-ልቦና ባለሙያ በሆኑት ፍራንችስካዊያን ማሕበር አባል በነበሩት ካህን አባ አጎስቲኖ ጂሜሊ ስም ሲሆን የዩኒቨርሲቲው መስራች እና የመጀመሪያ ዳይሬክተር እርሳቸው እንደ ነበሩም ተገልጿል።

ቅዱስነታቸው እንደ ተለመደው ማንኛውንም ዓይነት ሐዋሪያዊ ጉብኝት ለማድረግ ከሮም ከተማ በሚወጡበት እና ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ቫቲካን በሚመለሱበት፣ እንዲሁም በተጨማሪም በሕይወታቸው እና በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው ውስጥ ተግዳሮቶች በሚያግጥሟቸው ወቅት ቅዱስነታቸው በሮም ከተማ እምብርት ላይ በምትገኘው እና በአውሮፓ በማርያም ስም ከተሰየሙት ባዚልካዎች መካከል በትልቅነቱ በሚታወቀው፣ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ግንባታው እንደተጠናቀቀ በሚነገርለት በሳንታ ማርያ ማጆሬ (Sanat Maria Maggiore) ጸሎት እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በሰኔ 09/2015 ዓ.ም ወደ እዚያው አቅንተው በቀዶ ጥገና ወቅት ማርያም ስላደረገችላቸው መለኮታዊ ጥበቃ ምስጋና ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን ከእዚያን በኋላ ቅዱስነታቸው ወደ ማረፊያቸው ወደ ቫቲካን መመለሳቸው ተገልጿል።

16 June 2023, 11:24