ፈልግ

ሮም ከተማ ውስጥ የሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል ሮም ከተማ ውስጥ የሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል   (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከሆስፒታል እንደሚወጡ ተነገረ

ሮም ከተማ በሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሕክምና የተደረገላቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ በሚቀጥሉ ጥቂት ቀና ውስጥ ከሆስፒታል እንደሚወጡ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ አስታውቀዋል። አቶ ማቴዮ ብሩኒ የቅዱስነታቸውን የቅርብ ቀናት የሕክምና ክትትል ውጤቶችን በማስታወስ እንደተነገሩት፥ “ቅዱስነታቸው አሁን በመልካም ደረጃ ላይ ይገኛሉ” ብለው የምርመራ ውጤቶችም መደበኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ረቡዕ ግንቦት 30/2015 ዓ. ም. ከዓት በኋላ ሆስፒታል የገቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እስካሁን በተደረገላቸው የሕክምና ዕርዳታ መልካም ውጤቶችን በማስመዝገብ አሁን ላይ በማገገም ሂደት ላይ እንደሚገኙ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ አስታውቀዋል። 

አቶ ማቴዮ ከቅዱስነታቸው የድህረ-ቀዶ ሕክምና ዕርዳታ ሐኪሞች ቡድን ያገኙትን መረጃን መሠረት በማድረግ በሰጡት መግለጫ፥ “ቅዱስነታቸው ሌሊቱን ጥሩ እንቅልፍ እንደሚተኙ፣ የምርመራ ውጤቶችም ችግር የማይታይባቸው በመሆኑ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከሆስፒታል እንደሚወጡ እና ሐኪሞቻቸው ዕቅድ እያወጡ ይገኛሉ" ብለዋል። አቶ ማቴዮ ብሩኒ አክለውም ቅዱስነታቸው በትናንትናው ውሎአቸው ጠዋት እስከ ረፋዱ  የንባብ እና የጽሑፍ ሥራቸውን ሲያከናውኑ ቆይተው ቀጥለውም ወደ ጸሎት ቤት ገብተው ጸሎታቸውን ካደረሱ በኋላ  ቅዱስ ቁርባን ቆርበው መመላሳቸውን ገልጸዋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቀዶ ጥገና ሐኪም ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ በሰጡት መግለጫ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥሩ ሁኔታ በማገገም ላይ እንደሚገኙ እና በተቻለ መጠን ጫናን ከሚፈጥሩ የአካል እንቅስቃሴዎች እንደተገደቡ መናገራቸው ይታወሳል።    

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒም እንደዚሁ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ተይዘው የነበሩ ቀጥሮዎች በሙሉ እስከ ሰኔ 11/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደተሠረዙ መናገራቸው ይታወሳል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጭው ነሐሴ ወር በፖርቱጋል እና በሞንጎሊያ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ እቅድ እንዳላቸው ይታወቃል።

15 June 2023, 09:53