ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ እንደ ቅድስት ትሬዛ የትህትናን መንገድ መከተል ይኖርብናል ማለታቸው ተገለጸ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ በቫቲካን ሆነው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በግንቦት 30/2015 ዓ.ም ያደረጉት አስተምህሮ ከእዚህ ቀድመ “ለስብከተ ወንጌል ያለው ፍቅር፡-የምእመናን ሐዋርያዊ ቅንዓት” በሚል ዐብይ እርዕስት ጀምረውት ከነበረው አተምሮ ቀጣይ እና ክፍል 16 አተምሮ እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን በእዚህ መስረት በእለቱ “የሕፃኑ ኢየሱስ ቅድስት ትሬዛ፣ የተልእኮዎች ጠባቂ” ምስክርነት በሚል ንዑስ አርእስት ባደረጉት የተቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ቅድስት ትሬዛ የትህትናን መንገድ ልንከተል ይገባናል ማለታቸው ተገልጿል።

 በእለቱ የተነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚከተለው ነበር

“ከእናንተ መካከል አንዱ መቶ በጎች ቢኖሩትና ከእነርሱ አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በሜዳ ላይ ጥሎ የጠፋውን እስኪያገኝ ድረስ ሊፈልገው የማይሄድ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ተሸክሞ፣ ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹንም በአንድነት ጠርቶ፣ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ይላቸዋል። እላችኋለሁ፤ እንደዚሁም ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ፣ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል (ሉቃስ 15፡4-7)።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡርና እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቃላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አስተናድተነዋል፣ ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የመንፈሳዊ ተልእኮዎች ሁለንተናዊ ጠባቂ የሆነችው የሕፃኑ ኢየሱስ የቅድስት ትሬዛ ቅርሶች እዚህ ከፊታችን ይገኛል። ለወንጌል አገልግሎት ያላትን ቅናዓት እና ፍቅር፣ በሐዋርያዊ ቅንዓት ላይ እያሰላሰልን ይህ ቢደረግ መልካም ነው። እንግዲያው ዛሬ የቅድስት ትሬዛን ምስክርነት እንዲረዳን እንፍቀድ። የተወለደችው ከ150 ዓመታት በፊት ነው፣ እናም በዚህ አመታዊ ክብረ በዓል ሐዋርያዊ መልእክት ስለሷ ልጽፍ አስቤ ነበር።

እሷ የመንፈሳዊ ተልእኮዎች ጠባቂ ነች፣ ነገር ግን ወደ ተልእኮ አልተላከችም ነበር። ህይወቷን ርሷን ዝቅ በማድረግ እና ደካማ እንድሆነች አድርጋ በመቁጠር የምትመራ የቀርሜሎስ መነኩሴ ነበረች፡ እራሷን “ትንሽ የአሸዋ ቅንጣት” በማለት ገልጻለች። ጤንነቷ የተጓደለ ስለነበረ በ24 ዓመቷ ከእዚህ ዓለም በሞት ተለየች።ሆኖም ሰውነቷ ታምሞ የነበረ ቢሆንም ልቧ ንቁና ሚስዮናዊ ነበር። ፍላጎቷ ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት እንደነበረ እና ለጥቂት አመታት ብቻ ሳይሆን በቀሪው ህይወቷም ሆነ እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ አንድ መሆን እንደምትፈልግ “በማስታወሻ ደብሯ” ላይ ባሰፈረችው ጹሁፍ ትናገራለች። ቅድስት ትሬዛ ለብዙ ሚስዮናውያን “መንፈሳዊ እህት” ነበረች፡ በደብዳቤዎቿ፣ በጸሎቷ እና ለእነሱ የማያቋርጥ መስዋዕት በማቅረብ አብሯቸው ተጉዛለች። ሳትታይ ለመንፈሳዊ ተልዕኮዎች አማለደች፣ ልክ እንደ ሞተር፣ ምንም እንኳን የተደበቀ ቢሆንም፣ ለተሸከርካሪው ወደፊት እንዲራመድ ኃይል እንደሚሰጥ ማለት ነው። ነገር ግን ጓደኞቿ መነኮሳት ብዙ ጊዜ አልተረዷትም ነበር፣ ከነሱ "ከጽጌረዳዎች ይልቅ እሾህ" ተቀበለች ነገር ግን ሁሉንም ነገር በፍቅር፣ በትዕግስት ተቀበለች፣ እነዚህን ፍርዶች እና አለመግባባቶች እንኳን ከህመሟ ጋር አቀረበች። እናም ይህንን በደስታ አደረገች፣ ለቤተክርስቲያኗ ፍላጎቶች፣ ስለዚህም፣ እንደተናገረችው፣ “ጽጌረዳዎች በሁሉም ላይ ይወድቃሉ” በተለይም በጣም ሩቅ በሚገኙት ላይ ብላ ነበር።

አሁን እጠይቃለሁ፣ ይህ ሁሉ ቅንዓት፣ ይህ ሚስዮናዊ ጥንካሬ፣ እና ይህ የማማለድ ደስታ ከየት መጣ? ትሬዛ ወደ ገዳሙ ከመግባቷ በፊት የተከሰቱት ሁለት ክፍሎች ይህንን እንድንረዳ ይረዱናል።

የመጀመሪያው ህይወቷን የቀየረችበትን ቀን ማለትም እ.ኤ.አ. በ1886 በገና በዓል ወቅት እግዚአብሔር በልቧ ተአምር የሰራበትን ቀን ይመለከታል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ትሬዛ 14 ዓመት ይሞላታል። ታናሽ ልጅ እንደመሆኗ መጠን እቤት ውስጥ ባሉ ሰዎች ሁሉ እንክብካቤ ተደርጎላት ነበር። ከመንፈቀ ሌሊት ቅዳሴ ስትመለስ ግን በጣም የደከመው አባቷ ሴት ልጁ ስጦታዋን ስትከፍት “ጥሩ ነገር ያለፈው አመት ነው!” ብሎ ነገራት። በጣም ስሜታዊ የሆነች እና በቀላሉ በእንባ የምትሞላ ትሬዛ ተጎዳች እና ወደ ክፍሏ ሄዳ አለቀሰች። እሷ ግን በፍጥነት እንባዋን አፍና ወደ ታች ወረደች እና በደስታ ተሞልታ አባቷን የምታስደስት እሷ ነበረች። ምን ተፈጠረ? በዚያች ሌሊት ኢየሱስ በፍቅር ራሱን ሲያዳክም ነፍሷ በረታች፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከራስ ወዳድነቷና ከራስ ርኅራኄዋ እስር ቤት ወጣች። “ፍቅር ራሷን ለመርሳት ወደ ልቧ እንደገባ” ይሰማት ጀመር።  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ እግዚአብሔርን እንዲያገኙ ለሌሎች ያላትን ቅንዓት አቀናች፣ እና ለራሷ ማጽናኛ ከመፈለግ ይልቅ “ኢየሱስን ለማጽናናት [በነፍስ] እንዲወደድ” ለማድረግ ተነሳች። ምክንያቱም እንደ ቴሬዛ፣ የቤተክርስቲያን ሊቅ “ኢየሱስ በፍቅር ታምሟል እና [...] የፍቅር በሽታ በፍቅር ካልሆነ በቀር ሊፈወስ አይችልም” ብላ ነበር። ይህ እንግዲህ የዕለት ተዕለት ውሳኔዋ ነበር፡- “ኢየሱስን እንዲወዱ” ለሌሎች መማለድ። እሷም እንዲህ ስትል ጽፋለች፣ “ነፍሶችን ማዳን እና ራሴን ለእነሱ መርሳት እፈልጋለሁ፡ ከሞትኩ በኋላም ልታደጋቸው እፈልጋለሁ” ብላም ነበር። ብዙ ጊዜ “ሰማዬን በምድር ላይ መልካምን በመስራት አሳልፋለሁ” ብላለች።

የመልካሙን እረኛ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ቅንዓቷ በተለይ ለኃጢአተኞች ማለትም “በሩቅ ላሉት” ይመራ ነበር። ይህ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ ተገልጧል። ቴሬዛ በአስፈሪ ወንጀሎች ሞት የተፈረደበት ኤንሪኮ ፕራንዚኒ ትብሎ ስለ ሚታወቀው ወንጀለኛ ሰው ሰማች፣ በሦስት ሰዎች አሰቃቂ ግድያ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል እናም አንገቱ በሰይፍ እንዲቀላ ተወስኗል። ነገር ግን የእምነትን መጽናናት መቀበል አልፈለገም። ትሬዛ ወደ ልቧ ወሰደችው እና የምትችለውን ሁሉ አደረገች፡ በወንድማማችነት ርህራሄ “ምስኪን ፕራዚኒ” ብላ የጠራችው እሱ ትንሽ የንስሃ ምልክት እንዲያሳይ እና ለእግዚአብሔር ቦታ እንዲሰጥ በሁሉም መንገድ መንፈሳዊ ለውጥ እንዲያመጣ ጸለየች። ትሬዛ በጭፍን የታመነችበት ምሕረት። ግድያው ተፈጽሟል። በማግስቱ ትሬዛ በጋዜጣ ላይ እንዳነበበችው ፕራንዚኒ ራስ ቅሉ ከመቀላቱ በፊት በድንገት ተመስጦ ዞሮ ብሎ በአጠገቡ የነበረው ካህን ይዞት የነበረውን መስቀል ያዘ። ካህኑም መስቀሉን ለፕራዚኒ ሰጡት፣ እርሱም ተቀብሎ ኢየሱስ የተወጋበትን ቅዱስ የሆኑ ቁስሎቹን 3 ጊዜ ሳመ። ቅዱሱም “ከዚያም ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ ለሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል ብሎ የተናገረውን የምሕረት ፍርድ ለመቀበል ነፍሱ አሳልፎ ሰጠ።  

በፍቅር የሚንቀሳቀስ የምልጃ ኃይል እንዲህ ነው፥ የተልእኮ ሞተር እንዲህ ነው! በእውነቱ ትሬዛ የሚስዮናውያን የድጋፍ ጠባቂ ሆነች - ረጅም ርቀት የሚጓዙ፣ አዲስ ቋንቋ የሚማሩ፣ መልካም ስራዎችን የሚሰሩ እና በአዋጅ የተካኑ ብቻ አይደሉም። እንዲህ አይደለም። ሚስዮናዊ ማለት ባለበት ቦታ የእግዚአብሔር ፍቅር መሣሪያ ሆኖ የሚኖር ማንኛውም ሰው ነው። ሚስዮናውያን በምሥክርነታቸው በጸሎታቸው፣ በአማላጅነታቸው ኢየሱስ እንዲያልፍ ሁሉን የሚያደርጉ ናቸው።

ይህ ሐዋርያዊ ቅንዓት ነው፣ ሁል ጊዜ እናስታውስ፣ ሃይማኖት ማስለወጥ ወይም በመገደብ ፈጽሞ የማይሠራ፣ ነገር ግን በመሳብ እንጂ፡ አንድ ሰው ክርስቲያን የሚሆነው በአንድ ሰው ስለተገደደ ሳይሆን በፍቅር ስለተነካ ነው። ብዙ መንገዶች፣ ዘዴዎች እና አወቃቀሮች በመኖራቸው፣ አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ከሆነው ነገር ትኩረትን የሚከፋፍሉ፣ ቤተክርስቲያን እንደ ትሬዛ ያሉ ልቦች፣ ሰዎችን ወደ ፍቅር የሚስቡ እና ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ ልቦች ያስፈልጋታል። እራስ ወዳድነታችንን የምናሸንፍበት እና ኢየሱስ እንዲታወቅ እና እንዲወደድ የማማለድ ስሜት እንዲሰጠን ይህንን በቅድስት ትሬዛ አማላጅነት እንለምነው።

07 June 2023, 11:09

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >