ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በክርስቲያኖች መለያየት እግዚአብሔር እንደሚያዝን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከጥር 10-17/2015 ዓ. ም. ሲከበር በቆየው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን መርተዋል። ረቡዕ ጥር 17/2015 ዓ. ም. ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የተመለሰበት ዓመታዊ በዓል የተከበረበት ዕለት እንደነበር ታውቋል። ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ እግዚአብሔር በክርስቲያኖች አለመግባባት እና ግፍ በተሞላው መስዋዕትነት እንደሚያዝን አስታውሰው፣ ሁሉም ሰው ልቡ ተለውጦ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሚፈልገው ሙሉ አንድነት ለማደግ እንዲተባበር አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እግዚአብሔር አምላክ፣ በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት አማካይነት በሚሰጠን ምክር፥ በክርስቲያኖች መካከል በሚታዩ ግድ የለሽ አለመግባባቶች፣ ከእርሱ ይልቅ የራሳችንን ራዕይ ስናስቀድም እና ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በሚያደርሱት የጦርነት እና የአመጽ መከራዎች ልቡ እንደሚያዝን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ስለዚህ አመለካከታችንን ለውጠን፣ ሌሎችን በራስ ዕይታ ብቻ ሳይሆን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕይታ መመልከት እንዳለብን አሳስበው፣ “በጸጋው ተለውጠን በጸሎት፣ በአገልግሎት እና በውይይት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደሚፈልገው ሙሉ አንድነት መድረስ እና ማደግ የምንችለው በጋራ በመሥራት ነው” በማለት፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የተመለሰበት መታሰቢያ ዕለት በተካሄደው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት ማጠቃለያ ላይ ተናግረዋል። 

በሮም የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አጽም በሚገኝበት በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ውስጥ በቀረበው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት መዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት አባቶች የተገኙ ሲሆን፣ የጣሊያን እና የማልታ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖሊካርፖስ፣ እንዲሁም በሮም የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ማዕከል መሪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ያን ኤርነስት ጋር በመሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ለዓመታዊው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎት ሳምንት መሪ ቃል እንዲሆን ከትንቢተ ኢሳ. ምዕ. 1:17 የተመረጠውን እና “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ” ተብሎ የተጻፈውን ጥቅስ በማሰማት መልዕክት አስተላልፈዋል። “አሳዛኝ እና አስጨናቂ ወሬዎች ዛሬም አልጠፉም” ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በምንኖርበት በዛሬው ዘመን ለመከራ የተጋለጥነው ለምንድን ነው?” ብለን መጠየቅ ይኖርብናል ብለዋል።

ለለውጥ የቀረበ ምክር

“ነቢዩ ኢሳያስ በትንቢታዊ ቃሉ ይመክረናል፣ ለለውጥም ይጋብዘናል" ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ እግዚአብሔር በሚወዳቸው ሕዝቦች ላይ ቁጣውን ለምን ላከባቸው?" በማለት ጠይቀዋል። ከትንቢተ ኢሳይያስ መጽሐፍ እንደምናነበው፣ እግዚአብሔር የሚፈልገው ወደ መቅደሱ በስሙ የሚቀርበውን ዕጣን እና ቍርባን ሳይሆን፣ የተገፉት እንዲረዱ፣ ለድሆች ፍትሕ እንዲሰጥ እና ለመበለቲቱ እንዲሟገቱላት የሚጠይቅ መሆኑ አስታውሰዋል። በነቢዩ ዘመን፣ ባለጠጎችና ብዙ መስዋዕቶችን ያቀረቡ የነበሩ በእግዚአብሔር የተባረኩ ተደርገው ሲቆጠሩ ድሆች ግን ይናቁ እንደ ነበር ቅዱስነታቸው አስታውሰው፣ እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ ሁኔታ በዘመናችንም በገሃድ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዓን የሃይማኖት አባቶች ጋር በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዓን የሃይማኖት አባቶች ጋር በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ

ባለመግባባታችን እግዚአብሔር አዝኗል!

“ነገር ግን ይህ ሁሉ እግዚአብሔርን አለመረዳት ይገልጻል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ድሆች ብፁዓን እንደሆኑ ሲያውጅ እና በመጨረሻው የፍርድ ቀን ምሳሌም እራሱን ከተራቡት፣ ከተጠሙት፣ ከመጻተኞች፣ ከድሆች፣ ከታመሙት እና ከእስረኞች ጋር እንደሚያስቀምጥ ገልጸው፣ “የእግዚአብሔር ቁጣ የመጀመሪያው ምክንያት፣ የእርሱን ምሳሌነት ባለመከተላችን ነው” በለዋል።

ራሳችንን ታማኞች ነን ብለን ስንጠራ፣ ራእያችንን ከእርሱ ራእይ ስናስቀድም፣ ከሰማዩ ይልቅ ምድራዊ ፍርድን ስንከተል፣ በውጫዊ ገጽታ ብቻ ስንረካ እና እርሱ ለሚጨነቅላቸው ሰዎች ግድ የለሾች ስንሆን፣ እግዚአብሔርም በዚህ የተነሳ የሚያዝን መሆኑን አስረድተዋል።

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሆነው ሰው ላይ የሚፈጸመው የረከሰ ዓመፅ

“እግዚአብሔር የሚከፋበት ሁለተኛው እና ከባዱ ምክንያት፣ ‘የረከሰ ዓመፅ’ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ስለ "ወንጀል እና ስለ ረከሰ በዓል፣ እንዲሁም ደምን ስለሚያንጠባጥቡ እጆች" እንደሚናገር አስታውሰው፣ ሰው ሠራሽ ለሆነው ቤተ መቅደስ ክብር እየተሰጠው ነገር ግን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሆነው ሰው ላይ በሚፈጸም ግፍ ምክንያት እግዚአብሔር መቆጣቱን አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፥ "ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በሚያካሂዱት ጦርነቶች እና የዓመፅ ድርጊቶች እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሚሰቃይ መገመት እንችላለን" ብለዋል።

እምነት፣ የብሔርተኝነት አመጽ እና የውጭ ጥላቻን አይፈቅድም

የንጉሡን ጭካኔ በመቃወም በጾም ወቅት ሥጋን ሊያቀርብለት ወደ ንጉሡ ዘንድ የሄደውን ቅዱስ ሰው ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ንጉሡ በሃይማኖት አክባሪነቱ ቁጣውን በመግለጽ ሥጋውን ለመብላት አሻፈረኝ ባለ ጊዜ ቅዱሱ ሰው፣ ይህ የእግዚአብሔርን ልጆች ለመግደል ያላቅማማ፣ ነገር ግን የእንስሳትን ሥጋ ለመብላት ለምን ተቸግሯል?” ብሎ መጠየቁን አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው አክለውም፣ ምንም እንኳን "መንፈሳዊነት እና የሥነ-መለኮት ዕድገት" በቂ ምክር ቢሰጥም፣ አንዳንድ ሰዎች ከሚከተሉት እምነት ፍቃድ እንደተሰጣቸው እና ብርታትን ያገኙ ይመስል፣ ጨካኝ ብሔርተኝነትን ለሚደግፉት፣ የጥላቻ አስተሳሰቦችን ለሚያራምዱት፣ ንቀትን አልፎ ተርፎም እንግልትን ለሚመርጡት በሙሉ፥ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን በመጥቀስ ከድርጊታቸው እንዲመለሱ ምክራቸውን በመለገስ፣ “የሐዋርያው ​​ጳውሎስን ምሳሌ በመከተል በእኛ ላይ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ከንቱ እንዳይሆን ከፈለግን ጦርነትን፣ ዓመፅን እና ኢ-ፍትሐዊነትን በሁሉም ሥፍራ መቃወም አለብን” ብለዋል።

ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ከክፉ ወደ በጎነት መሸጋገር ያስፈልጋል!

በትንቢተ ኢሳ. ምዕ. 1:17 “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ. . .” ተብሎ የተጻፈውን የዘንድሮው የክርስቲያኖች አንድነት የጸሎተ ሳምንት መሪ ጥቅስን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ይህ ጥቅስ ከዚህ ቀደም በሰሜን አሜሪካ ነባር ተወላጆች እና በአፍሮ አሜሪካውያን ላይ የተፈፀመውን ኢ-ፍትሃዊነት ለማስታወስ ከሚኒሶታ ግዛት በመጡ የምዕመናን ቡድን መመረጡን ገልጸው፣ ንቀት እና ዘረኝነት ላለበት፣  አለመግባባት ለሚታይበት እና ክፉ ዓመፅ ለሚካሄድበት ለዚህ ዓለም የእግዚአብሔር ቃል፥ “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትህን እሹ፤...” (ኢሳ 1፡17) በማለት እንደሚመክር አስታውሰው፣ እነዚህን መጥፎ ተግባራት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ከክፋት ወደ በጎነት መሸጋገር ያስፈልጋል! በማለት ምክራቸውን ለግሠዋል።

ከእግዚአብሔር ጋር በመሆን በኅብረት ለወጥን ማምጣት ይቻላል!

“ስህተቶችን ከመረመርናቸው በኋላ ምሕረትን እንድናገኝ እግዚአብሔር እንደሚፈልግ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ከኃጢአታችን ሊያነጻን የሚችለው እርሱ ብቻ እንደሆነ እና ይህን ለማድረግ ቃል መግባቱን አስታውሰው፣ "ለእግዚአብሔር ካለን ቸልተኝነት እና በውስጣችን ካለን ዓመፅ በኃይላችን መላቀቅ አንችልም" ብለዋል። የሐዋርያው ​​ጳውሎስ ሕይወት እንደሚያስታውሰን የመለውጣችን ምንጭ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ብቻውን ምንም ማድረግ እንደማንችል፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር በመታመን በኅብረት ከቆሙ ሁሉን ነገር ማድረግ እንደሚቻል እና እግዚአብሔርም የእርሱ ተከታዮች እንዲለወጡ መጠየቁን አስታውሰዋል።

መለወጥ የሚለው ቃል ብዙ የተደጋገመ እና በሚገባ ለመረዳት ቀላል እንዳልሆነ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ መለወጥ ለሕዝቦች የሚቀርብ፣ ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ትርጉም ያለበት ጥያቄ መሆኑን በመግለጽ፣ ክርስቲያኖች ወደ አንድነት የሚያደርጉት የለውጥ ጉዞ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚያስፈልገው እና ይህም የሚሆነ የእርሱን ምሕረት ስንገነዘብ፣ ሁላችንም በሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ላይ የምንመካ መሆናችንን ስንገነዘብ፣ በእሱ ዕርዳታ በእውነት አንድ መሆን እንችላለን" በማለት ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመፈጽም ላይ
ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከብጹዓን ጳጳሳት ጋር የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመፈጽም ላይ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት የሚከተሉ ክርስቲያኖችን እናመሰግናለን!

እንደ ክርስቲያኖች “የአመለካከት ለውጥ” እንድናደርግ ተጠየቀናል ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “የሕዝቦች ብርሃን” የተሰኘውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጥቀስ “በመላው ዓለም ተበታትነው የሚገኙት ምእመናን በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ኅብረት አላቸው” የሚለውን በማስታወስ፣ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በመካሄድ ላይ ስለሚገኘው ሲኖዶስዊ ጉዞ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ የኅብረት ጉዞ በርካታ ክርስቲያኖች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ አባላት፣ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በምታካሂደው ሲኖዶሳዊ ጉዞ ለመሳተፍ በመጀመራቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የምንሠራው ለራሳችን ሳይሆን ለእግዚአብሔር መንግሥት ነው!

“በኅብረት እንድንጓዝ እና በመንፈስ ቅዱስ አንድ እንድንሆን የጋበዙን ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በቅርቡ ያረፉት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ፥ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ከእግዚአብሔር ጋር ካለን የጠበቀ ግንኙነት መጀመር እንደሚገባ እና ሌላውን ሰው በግል እይታ ብቻ ሳይሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ እይታ ጋር መመልከት እንደሚገባ እና “አንድ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅ ከሆነ የእኔም ወዳጅ ነው” ማለታቸውን በማስታወስ፣ ለመለወጥ የሐዋርያው ቅዱስ ​​ጳውሎስን ዕርዳታ እና የእርሱን የማይበገር ድፍረት በጸሎት ጠይቀዋል። 

በጉዟችን ለእግዚአብሔር መንግሥት ሳይሆን ወገን ለሆነው ብቻ መሥራት ቀላል ነው” ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ትዕግሥት እና ተስፋ በጠፋበት በዚህ ዘመን፣ ክርስቲያኖች በሙሉ በኅብረት በአንድ መንበረ ታቦት ዙሪያ ሆነው ጸሎታቸውን ሲያቀርቡ አንድነታቸውን እንደሚያገኙ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ከጥንት ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያኑ የሰጠው ብቸኛዋ አንድነት ይህ እንደሆነ አስረድተዋል።

በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች
በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ተወካዮች

በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያቸው፣ በጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ያቀረቧቸው ሐሳቦች ሁሉንም ሰው እንደሚረዳ ተስፋ በማድረግ፣ በእግዚአብሔር ተመርተን፣ በጸጋው ተለውጠን በጸሎት፣ በአገልግሎት፣ በውይይት እና በመተባበር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሚፈልገው ፍጹም አንድነት ለመድረስ በኅብረት እንሠራለን ብለዋል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት፣ የክርስቲያኖች የተዋህዶ ፓትርያርክ ተወካይ እና የጣሊያን እና የማልታ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖሊካርፖስ፣ በሮም የካንተርበሪው የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ተወካይ ለብጹዕ አቡነ ያን ኤርነስት እና ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ሰላምታቸውን አቅርበው፣ በመቀጠልም ከመላው የዩክሬን አብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ድርጅቶች ምክር ቤት አባላት “ጠንካራ ትብብር” ያላቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ከምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለመጡት ተማሪዎች፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማጎልበት ከሚሠራው ከቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ጋር ከሚተባባሩ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የባሕል ትብብር ኮሚቴ ምሁራን ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። እንዲሁም ለቦሲ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ተወካዮችም ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በመጨረሻም ቀጣዩ የካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ ዋዜማ ላይ በሚደረግ የጋራ ጸሎት ላይ ለሚሳተፉት ወንድም አሎይስ እና ለታኢዜ ወንድሞች በሙሉ ከፍ ያለ የወንድማማችነት ሰላምታ ልከውላቸዋል።

በሥነ ሥርዓቱ መዝጊያ ላይ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ በመሥራት ላይ የሚገኝ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ፣ ዋና ጸሐፊያቸው ከሆኑት ከሊቀ ጳጳስ ብሪያን ፋሬል ጋር በመሆን ሰላምታቸውን አቅርበዋል።  “መልካም ማድረግን ተማሩ፣ ፍትህን ፈልጉ” የሚለው የጸሎት ሳምንቱን መሪ ቃል ጥልቅ ትርጉም እንዳለው፣ “የእምነት ቁርጠኝነት በለውጥ መንፈስ መሞላት እንዳለበት እና ሁላችንም ለለወጥ የተጠራን መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ኮክ አስታውሰዋል። “ሰላም የፍትህ ፍሬ ናት” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኮክ፣ በተጨማሪም ለክርስቲያኖች አንድነት ለምናደርገው ጥረትም እንደሚያግዛቸው ገልጸው፣ “እኛ ክርስቲያኖች መብታችንን መመልከት ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና ማኅበረሰቦች የሰጣቸውን ስጦታዎች እና ባለጠግነቶችን በምስጋና የምናደንቅ ከሆነ በመካከላችን ሰላምን እናገኛለን” ብለዋል። ፍቅር ብዙሃንነትን እና አንድነትን እንደሚያስታርቅ፣ በክርስቲያኖች መካከል የሚገኙ ልዩነቶች ባይሽርም ነገር ግን ከውስጥ ሆኖ ፍሬን በሚያፈራ ጥልቅ አንድነት ላይ ኅብረትን እንደሚያሳድግ፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ለማሳደግ በመሥራት ላይ የሚገኝ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽ/ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ለጸሎቱ ተካፋዮች ምስጋናቸውን ሲያቀርቡ
ብጹዕ ካርዲናል ኩርት ኮክ ለጸሎቱ ተካፋዮች ምስጋናቸውን ሲያቀርቡ
26 January 2023, 16:44