ፈልግ

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በፖላንድ ይኖሩ በነበሩ አይሁዳዊያን ላይ ከተፈጸመ ዘር የማጥፋት እና የስቃይ ተግባራት መካከል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በፖላንድ ይኖሩ በነበሩ አይሁዳዊያን ላይ ከተፈጸመ ዘር የማጥፋት እና የስቃይ ተግባራት መካከል  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ታሪክ እራሱን ዛሬ በዩክሬን መድገሙን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 28/2015 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀጥለው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ለተገኙት ምዕምናን ንግግር አድርገዋል። በጦርነት ውስጥ የምትገኝ ዩክሬንን በድጋሚ አስታውሰው፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስፈሪ ክስተት በድጋሚ ዛሬ በዩክሬን ላይ ማንዣበቡን ገልጸው፣ በላቲን የአምልኮ ሥርዓት አቆጣጠር መሠረት ሐሙስ ኅዳር 29/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን የእመቤታችን ንጽሕት ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ምዕመናንን በማስታወስ፣ ዩክሬን ውስጥ በጦርነት ለሚሰቃዩት መጽናናትን እንድታስገኝ እመቤታችንን በጸሎት እንዲጠይቋት አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፣ በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በማስመልከት ታዳሚዎችን በድጋሚ አስታውሰዋል። "ታሪክ እራሱን ዛሬም ይደግማል!" ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በፖላንድ ሉብሊን ከተማ በሚገኝ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ማዕከል፣ የካቶሊክ እና የአይሁድ እምነቶች ግንኙነት ምሥረታን አስመልክት በተዘጋጀው በዓል ላይ ለተገኙት የፖላንድ ምዕመናን መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጸዋል። የመታሰቢያ በዓሉ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች በፖላንድ አይሁዶች ላይ ያካሄዱት የጭፍጨፋ ተግባርንም ማስታወሱ ታውቋል።

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት አስፈሪነት

እ. አ. አ. በ 1942 እና በ 1943 መካከል ያለው የዕቅዱ አፈፃፀም ናዚዎች በጀርመን የአይሁድ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመፈጸም ያደረገውን ሙከራ አስከፊነት የሚያሳይ እንደ ነበር ተገልጿል። በአጠቃላይ 1.7 ሚሊዮን የሚጠጉ አይሁዶች በቤልዜክ፣ በሶቢቦር እና በትሬብሊንካ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በጅምላ መገደላቸው ይታወሳል። በራይንሃርድ ካምፖች ላይ በተደረገው ኦፕሬሽን ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የፖላንድ፣ የሮማ እና የሶቪየት የጦር እስረኞች ሰለባ መሆናቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለታዳሚዎቹ ባሰሙት ንግግርም፥ የዚህ አሰቃቂ ክስተት ትውስታ የሰላም ውሳኔዎችን እና እርምጃዎችን ሊያነሳሳ ይገባል ብለዋል።

በስቃይ ውስጥ ለምትገኝ ዩክሬን የሚደረግ ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህም በተጨማሪ ከጣሊያን ልዩ ልዩ ሀገር ስብከቶች ለመጡት መንፈስዊ ነጋዲያን ባደረጉት የሰላምታ ንግግራቸው በዩክሬን በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት አስከፊነት ተናግረዋል።የላቲን የአምልኮ ሥርዓት በሚከተሉ ካቶሊክ ምዕመናን ዘንድ ሐሙስ ኅዳር 29/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን የንጽሕት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በጦርነት ስቃይ ውስጥ ለሚገኝ የዩክሬን ሕዝብ የእግዚአብሔር እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንድታጽናናቸው እንዲጸልዩ ጠይቀዋል።

07 December 2022, 16:16