ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የቅዱሳን ኅብረት የቤተክርስቲያን አባላት ኅብረት እንዲኖራቸው ያደርጋል አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸሶስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን ከሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ሆነው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም መሰረት ቅዱስነታቸው በጥር 25/2014 ዓ.ም ያደረጉት አስተምህሮ ከዚህ ቀደም በቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት ዙሪያ ላይ ጀምረውት ከነበረው አስተምህሮ ቀጣይ ክፍል እንደ ነበረ የተገለጸ ሲሆን የቅዱሳን ኅብረት ሁሉም የቤተክርስቲያን አባላት ኅብረት እንዲኖራቸው ያደርጋል ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራና እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ በተጠቀሱት ጥቂት፣ ነገር ግን ጠቃሚ መረጃዎች በመመራት የቅዱስ ዮሴፍን ምስል እና እንዲሁም ቤተክርስቲያኒቱ ለዘመናት ስታገለግል በኖረችበት የስብዕና ገፅታዎች ላይ ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ ችለናል፣ ይህንንም በጸሎት እና በአምልኮ ማድመቅ ተችሏል። የቅዱስ ዮሴፍን ምስል ከዚህ ስሜታዊነት (የጋራ ስሜት) በመነሳት ዛሬ ትኩረቴን ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ሊያበለጽግ የሚችል እና ከቅዱሳን ጋር ያለንን ግንኙነትና ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩን ዘመዶቻችንን ጋር ያልንን ግንኙነታችንን ሊቀርጽ በሚችል ጠቃሚ የእምነት አንቀጽ ላይ ላተኩር እወዳለሁ። ይህም ማለት ደግሞ ስለ ቅዱሳን ህብረት ለማውራት እፈልጋለሁ ማለት ነው።

አንዳንድ ጊዜ ክርስትና እንኳን ከክርስቲያን የበለጠ አረማዊ የሆነ አስተሳሰብን በሚያንፀባርቁ የአምልኮ ዓይነቶች ውስጥ ሊወድቅ ይችላል። ዋናው ልዩነቱ ጸሎታችን እና ምእመናን የሚሰጡት አምልኮ በሰው ላይ ወይም በምስል ወይም በዕቃ በመታመን ላይ የተመሰረተ አይደለም፣ ምንም እንኳን ቅዱሳን መሆናቸውን ብናውቅም እንኳ። ነቢዩ ኤርምያስ፡- “በሰው የሚታመን ሰው እርጉም ነው፥ በእግዚአብሔር የሚታመን ሰው ምስጉን ነው” (17፡5፣7) በማለት ያሳስበናል። በቅዱሳን አማላጅነት ወይም በድንግል ማርያም አማላጅነት ሙሉ በሙሉ ስንደገፍ እንኳን፣ እምነታችን ዋጋ የሚያገኘው ከክርስቶስ ጋር ብቻ ሲስተሳሰር ነው። ከእርሱም ጋር አንድ የሚያደርገን ማሰሪያው “የቅዱሳን ኅብረት” የሚል ስያሜ አለው። ተአምራትን የሚያደርጉ ቅዱሳን አይደሉም፣ ነገር ግን በእነሱ አማካኝነት የሚሰራ የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው።

ታዲያ “የቅዱሳን ኅብረት” ምንድን ነው? የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ “የቅዱሳን ኅብረት ቤተ ክርስቲያን ናት” (ቁጥር 946) በማለት ያረጋግጣል። ይህ ምን ማለት ነው? ቤተ ክርስቲያን ለፍጹማን ብቻ ተለይታ የተቀመጠች ቦታ ናት ማለት ነው? አይደለም፡ ይህ ማለት የዳኑ ኃጢአተኞች ማህበረሰብ ነው ማለት ነው ። የእኛ ቅድስና በክርስቶስ የተገለጠ የእግዚአብሔር ፍቅር ፍሬ ነው፣ እሱም በመከራችን ውስጥ እኛን በመውደድ እና እኛን በማዳን፣ ለእርሱ ምስጋና ይግባውና አንድ አካል እንሆናለን ይላል ቅዱስ ጳውሎስ በእርሱም ኢየሱስ ራስ እኛም የተለያየ የአካል ክፍሎቹ ነን (1ቆሮ. 12፡12)። ይህ የአካል ምስል በኅብረት እርስ በርስ መተሳሰር ምን ማለት እንደሆነ ወዲያውኑ እንድንረዳ ያደርገናል፣ “አንዱም የአካል ክፍል ቢሠቃይ” ሲል ቅዱስ ጳውሎስ “ሌሎችም የአካል ክፍሎች ሁሉ አብረው ይሠቃያሉ” በማለት ጽፏል። አንድም አካል ክፍል ቢከበር ሌሎች የአካል ክፍሎችም ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ብልቶች ናችሁ” (1ኛ ቆሮ 12፡26-27)።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ በአጠገባችን ያሉትን ወንድም እና እህት ህይወት የሚነካው ደስታ እና ሀዘን እኔንም እንደሚነካ ሁሉ ህይወቴን የሚነካው ደስታ እና ሀዘን ሁሉንም ይነካል። ከዚህ አንፃር፣ የግለሰብ ሰው ኃጢአት እንኳን ሁልጊዜ ሁሉንም ሰው ይነካዋል፣ እናም የእያንዳንዱ ግለሰብ ፍቅር ሁሉንም ይነካል። በቅዱሳን ኅብረት መሠረት፣ እያንዳንዱ የቤተክርስቲያኑ አባል ከእኔ ጋር በጥልቅ መንገድ ተሳስሯል፣ እና ይህ ትስስር በጣም ጠንካራ ስለሆነ በሞት እንኳን ሊፈርስ አይችልም። በእርግጥም የቅዱሳን ኅብረት የሚመለከተው በታሪክ በዚህ ወቅት ከጎኔ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ጉዞአቸውን ጨርሰው የሞት ደጃፍ የተሻገሩትንም ጭምር ነው። ውድ ወንድሞች እና እህቶች በክርስቶስ ማንም በእውነት ከምንወዳቸው ሊለየን እንደማይችል እናስብ። ከነሱ ጋር አብሮ የመሆን መንገድ ብቻ ይቀየራል ፣ ግን ምንም እና ማንም ይህንን ትስስር ሊያፈርስ አይችልም። የቅዱሳን ኅብረት በምድርና በሰማይ ያሉ አማኞችን በአንድነት ይይዛል።

ከዚህ አንፃር ከጎኔ ካለ ወንድም ወይም እህት ጋር የምገነባው የጓደኝነት ግንኙነት፣ በሰማይ ካለ ወንድም ወይም እህት ጋርም መመስረት እችላለሁ። ቅዱሳን ብዙ ጊዜ ወዳጃዊ ግንኙነት የምንመሠርትላቸው ወዳጆች ናቸው። ፍቅር ብለን የምንጠራው ከዚህ አንድ የሚያደርገን ፍቅር የምንገልፅበት መንገድ ነው። እናም ሁል ጊዜ ወደ ጓደኛ መዞር እንደምንችል ሁላችንም እናውቃለን፣ በተለይ በችግር ውስጥ ስንሆን እና እርዳታ በምንፈልግበት ጊዜ። ሁላችንም ጓደኞች ያስፈልጉናል፣ በሕይወታችን ውስጥ እንድናልፍ የሚረዳን ሁላችንም ትርጉም ያለው ግንኙነት እንፈልጋለን። ኢየሱስም ጓደኞች ነበሩት እና በሰው ልጅ ልምዱ በጣም ወሳኝ በሆኑ ጊዜያት ወደ እነርሱ ዘወር ብሏል። በቤተክርስቲያኗ ታሪክ ውስጥ አማኙን ማህበረሰብ የሚያጅቡ አንዳንድ ቋሚዎች አሉ፡ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቤተክርስቲያን በእግዚአብሔር እናት እና በእናታችን ማርያም ላይ ያላትን ታላቅ ፍቅር እና ጠንካራ ትስስር ታመለክታለች። ለቅዱስ ዮሴፍም የሰጠችው ልዩ ክብርና ፍቅር ነው። ደግሞም እግዚአብሔር ያለውን እጅግ ውድ የሆነውን ልጁን ኢየሱስን እና ድንግል ማርያምን አደራ ሰጥቶታል። ደጋፊዎቻችን የሆኑት ወንድና ሴት ቅዱሳን - በተሸከምንበት ስም ምክንያት፣ ያለንበት ቤተ ክርስቲያን፣ በምንኖርበት ቦታ፣ ወዘተ የሚሰማን ለቅዱሳን ኅብረት ሁልጊዜ ምስጋና ማቅረብ ነው የሚገባን። ለእኛ ቅርብ ናቸው፣ እናም ይህ በህይወታችን ውስጥ ወሳኝ በሆኑ ጊዜያት ወደ እነርሱ እንድንመለስ ሁል ጊዜ ሊያነቃቃን የሚገባው እምነት ነው።

በትክክል በዚህ ምክንያት፣ ይህንን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በተለይ ከምይዘው እና ለብዙ ዓመታት በየቀኑ ባነበብኩት ለቅዱስ ዮሴፍ ጸሎት ላጠናቅቅ እፈልጋለሁ።

የተከበርከው ፓትርያርክ ቅዱስ ዮሴፍ ኃይሉ የማይቻለውን ነገር የሚቻል የሚያደርግ በዚህ የጭንቀትና የችግር ጊዜ እርዳኝ። ከባድ እና አስጨናቂ ሁኔታዎችን በአንተ ጥበቃ ሥር አድርግ፤ ይህም አስደሳች ውጤት ያስገኝ ይሆናል። የተወደድክ አባቴ፣ እምነቴ ሁሉ በአንተ ነው። በከንቱ ጠራሁህ አይባልና ከኢየሱስ እና ከማርያም ጋር ሁሉንም ነገር ማድረግ ስለምትችል ቸርነትህ እንደ ኃይልህ ታላቅ እንደሆነ አሳየኝ። አሜን።

02 February 2022, 14:05

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >