ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮ የገና በዓል የእግዚአብሔርን ልጅ እንድናመልክ ግብዣ የሚያቀርብልን በዓል ነው አሉ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር ረቡዕ እለት በቫቲካን ከሚገኘው የጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ሆነው የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ እንደ ሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 13/2014 ዓ.ም ባደረጉት የጠቃላላ አስተምህሮ የገና በዓል የእግዚአብሔርን ልጅ እንድናመልክ ጥሪ የሚያቀርብልን በዓል ነው ማለታቸው ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳስት ፍራንቸስኮ በእለቱ ያደረጉትን የጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

ዛሬ የገናን በዓል ለማክበር ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ታሪክ ሊረሳው የማይችለውን ክስተት ማለትም የኢየሱስን ልደት ላስታውስ እፈልጋለሁ።

ዮሴፍና ማርያም የንጉሠ ነገሥት ቄሳር አውግስጦስ ትእዛዝ ለመፈጸም ወደ ትውልድ ቦታቸው ሄደው ለመመዝገብ ከናዝሬት ወደ ቤተልሔም ሄዱ። እንደ ደረሱ ማርያም የምትወልድበት ጊዜ ስለቀረበ ወዲያው ማደሪያ ፈለጉ። በሚያሳዝን ሁኔታ ምንም ነገር አላገኙም። ስለዚህ ማርያም በከብቶች በረት እንድትወልድ ተገድዳለች (ሉቃ. 2፡1-7)።

እስቲ እናስብ፣ የአጽናፈ ሰማይ ፈጣሪ ለመወለድ ቦታ አልተሰጠውም! ምናልባት ይህ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ወደ ገዛ ቤቱ መጣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” በማለት እንደተናግረው ሊሆን ይችላል (ዮሐንስ 1፡11)። እናም ኢየሱስ ራሱ  እንደሚለው “ቀበሮዎች ጒድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት ቦታ የለውም”” (ሉቃስ 9፡58) በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል።

የኢየሱስን መወለድ የተናገረ አንድ መልአክ ነበር፤ ይህንንም የተናገረው በወቅቱ ዝቅተኛ ተብለው ለሚጠሩ ለእረኞች ነበር። እናም ሰብአ ሰገል ወደ ቤተልሔም የሚወስደውን መንገድ ያሳየ ኮከብ ነበር (ማቴ. 2፡1፣ 9.10)። መልአክት የእግዚአብሔር መልእክተኞች ናቸው። ኮከቡ አምላክ ብርሃንን እንደፈጠረ ያስታውሰናል (ዘፍ 1፡3) እናም ሕፃኑ “የዓለም ብርሃን” እንደሚሆን፣ ራሱን እንደሚገልጽ (ዮሐ. 8:12, 46) “እውነተኛው ብርሃን የሆነው ሰውን ሁሉ ያበራል” (ዮሐ 1፡9)፣ “በጨለማ ይበራል ጨለማም አላሸነፈውም።” (ዮሐንስ 1፡5)

እረኞቹ የእስራኤልን ድሆች፣ ትሑታን ሰዎች የራሳቸውን ፍላጎት ተገንዝበው የሚኖሩ ናቸው። በትክክል በዚህ ምክንያት ከሌሎቹ በበለጠ በእግዚአብሔር ይታመናሉ። የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖ ሲፈጥር ያዩት የመጀመሪያዎቹ እነርሱ ነበሩ፣ እናም ይህ ገጠመኝ በጥልቀት ለወጣቸው። “ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ” መመለሳቸውን ቅዱስ ወንጌል ይናገራ (ሉቃስ 2፡20)።

ሰብአ ሰገልም በሕፃኑ ኢየሱስ ዙሪያ ናቸው (ማቴ 2፡1-12)። ቅዱስ ወንጌል ነገሥታቱ እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ምን ያህል እንደነበሩ ወይም ስማቸው ማን እንደሆነ አይነግሩንም። በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር በምስራቅ ከሩቅ አገር (ምናልባትም ከፋርስ፣ ከባቢሎን ወይም ከደቡብ አረብ አገራት) መጥተው የአይሁድን ንጉስ ለመፈለግ ጉዞ ጀመሩ፣ በልባቸው እሱን ማምለክ ይፈልጉ ነበር። ሰብአ ሰገል የአረማውያን ሕዝቦችን ይወክላሉ፣በተለይም እግዚአብሔርን በዘመናት የፈለጉትን እና እርሱን ለማግኘት ጉዞ የጀመሩትን ሁሉ የሚወክሉ  ናቸው። እነሱ ደግሞ ሀብታሞችን እና ኃያላንን ይወክላሉ፣ ነገር ግን ለንብረት ባሪያ ያልሆኑትን ብቻ ነው የሚወክሉት፣ እነሱ በያዙት ነገር "ያልተያዙ" ሰዎች ናቸው።

የቅዱስ ወንጌል መልእክት ግልጽ ነው፡ የኢየሱስ ልደት የሰው ልጆችን ሁሉ የሚመለከት ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው።

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ወደ እግዚአብሔር የሚመራን ብቸኛው መንገድ ትህትና ነው። በተመሳሳይ ጊዜ፣ በተለይም ወደ እርሱ ስለሚመራን፣ ትህትና እኛንም ወደ ህይወት አስፈላጊ ነገሮች፣ ወደ እውነተኛው ፍቺው፣ ህይወት በእውነት ለምን መኖር ዋጋ ወደ ሆነችበት በጣም ታማኝ ምክንያት ይመራናል።

ትህትና ብቻ ለእውነት፣ ለትክክለኛ ደስታ፣ አስፈላጊ የሆነውን የማወቅ ልምድ ይከፍትልናል። ያለ ትህትና እግዚአብሔርን እና እራሳችንን ከመረዳት "እንገለላለን”። ሰብአ ሰገል እንደ አለም አመክንዮ እንኳን ጥሩ እና ኃይል የነበራቸው ሰዎች ቢሆኑም ቅሉ ነገር ግን እራሳቸውን ዝቅ አድርገው፣ ሕይወታቸውን ትሁት አድርገውታል እናም በዚህ ምክንያት በትክክል ኢየሱስን ለማግኘት እና እሱን በማወቃቸው ተሳክቶላቸዋል። ትህትናን በመፈለግ በጉዞ ላይ በመነሳት በመጠየቅ አደጋን እንደ ሚገጥማቸው በማወቅ ስህተትን እንደ ሚሰሩ ተገንዝበው ነበር ጉዞዋቸውን የጀመሩት።

እያንዳንዱ ሰው፣ በልቡ ጥልቀት፣ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ተጠርቷል እናም በእርሱ ጸጋ እርሱን ማግኘት ይችላል። ይህንን የቅዱስ አንሴልም (ከ1033-1109 ዓ.ም የኖረ) ጸሎት የራሳችን ልናደርገው እንችላለን፡- “ጌታ ሆይ እንድፈልግህ አስተምረኝ፣ እንደምፈልግም ራስህን ገለጥልኝ፣ ምክንያቱም ካላስተማረከኝና ካላገኛኸኝ ልፈልግህ አልችልም። አንተ እራስህን ካልገለጥክ በስተቀር አንተን ማግኘት አልችልም። አንተን እንድፈልግህ ፍቀድልኝ፣ አንተን በመፈለግ እንድመኝህ ፍቀድልኝ፣ አንተን በመውደድ እንዳገኝህ፣ አንተን በማግኘቴ እንድወድህ ፍቀድልኝ” በማለት እንጸልይ።

 ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ እያንዳንዱ ወንድና ሴት ወደ ቤተልሔም በረት በመመልከት ሥጋ ለለበሰው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰግዱ ዘንድ ልጋብዛችሁ እወዳለሁ።

ድሆችን ከፊት ረድፍ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፣ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ሚሉት “እነርሱን መውደድ አለብን ምክንያቱም በሆነ መንገድ የክርስቶስ ምስጢር በእነርሱ የገለጣልና፣ በእነርሱ ውስጥ - በተራቡ፣ በተጠሙ፣ በስደት ላይ ባሉት፣ በታረዙ፣ በታመሙ፤ በእስረኞች ውስጥ እርሱ ራሱ በምስጢር እንዲታወቅ ፈለገ። ድህነት የእግዚአብሔርን መንግሥት በሙላት ለመያዝ በጣም አስተማማኝ መንገድ ስለሆነ እነርሱን ልንረዳቸው፣ ከእነሱ ጋር ልንሰቃይ እና ልንከተላቸው ይገባናል” ማለታቸው ይታወሳል።

ከዚያም ኮከቡ ለሰብአ ሰገል ጋር እንዳደረገው ሁሉ ሃይማኖታዊ እረፍት የሌላቸው፣ በእግዚአብሔር ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ፣ ወይም ከሃይማኖት ጋር የሚዋጉትን፣ አምላክ የለሽ ሰዎች ከሆኑት ​​ሁሉ ጋር ወደ ቤተልሔም አብሬ ልሄድ እወዳለሁ። የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መልእክትን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡- “ይህ ክብር በእግዚአብሔር ላይ የተመሰረተ እና ፍጹም የሆነ በመሆኑ ለእግዚአብሔር የሚሰጠው እውቅና በምንም መልኩ የሰው ክብር ጠላት እንዳልሆነ ቤተ ክርስቲያን ትናገራለች። […] ከሁሉም በላይ ቤተክርስቲያን መልእክቷ ከሰው ልብ ምስጢራዊ ፍላጎት ጋር የሚስማማ መሆኑን ታውቃለች” (Gaudium et Spes፣ 21)።

በመልአኩ መዝሙር ወደ ቤታችን እንመለስ፡- “ሰላም እርሱ በሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ላይ በምድር ይሁን! ሁሌም ይህንን እናስታውስ፡- “ፍቅር ይህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን እርሱ እንደ ወደደንና ስለ ኀጢአታችን ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን መላኩ ነው፣ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” (1ኛ ዮሐ 4፡10፣19)።

የደስታችንም ምክንያት ይህ ነው፡ ያለ ምንም ውለታ እንደ ተወደድን አውቀን በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደድን መሆናችንን መገንዘቡ መልካም ነው። በተጨባጭ ፍቅር ሥጋን ለብሶ በመካከላችን ለመኖር መጣ። ይህ ፍቅር ስም እና ፊት አለው፣ ስሙ ኢየሱስ ነው፣ እሱ የፍቅር ፊት ነው - ይህ የደስታችን መሠረት ነው።

22 December 2021, 13:25

በቅርብ ጊዜ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የተደረገው ግንኙነት

ሁሉንም ያንብቡ >