ፈልግ

በሄይቲ ፕሬዚዳንት መገደል የተነሳ በአገሪቷ ከፍተኛ አመጽ መነሳቱ ተገለጸ። በሄይቲ ፕሬዚዳንት መገደል የተነሳ በአገሪቷ ከፍተኛ አመጽ መነሳቱ ተገለጸ። 

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በሄይቲ እየታየ ያለው አመፅ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሄይቲ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ያቀረቡትን አስቸኳይ ጥሪ በመደገፍ በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ ፕሬዚደንት መገደልን ተከትሎ በሄይቲ በጦር መሣሪያ ጭምር ተደግፎ እየተከናወነ የሚገኘውን ወንጀል እና ግጭት እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ሁሉም በዚህ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ ግጭቱን በአስቸኳይ በማቆም ሀገሪቱ የሰላም እና የስምምነት ጉዞ እንድትቀጥል የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ እለት ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም ባቀረቡት ጥሪ ሀገሪቱ የወደቀችበት በሁከት ጭምር የተደገፈ አመጽ እንዲቆም ግጭት የሚፈጥሩ የሄይቲ ፓርቲዎች እና መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ወደ ሰላም እና ስምምነት ጎዳና እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የሄይቲ ፕሬዚዴንት መገደላቸውን ተከትሎ የሀዘን መግለጫዎችን በተከታታይ ማውጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን “የጦር መሣሪያዎችን መፍታት፣ ከሞት ይልቅ ሕይወትን መምረጥ ፣ የሁሉም የጋራ ፍላጎት እና የሄይቲ ሕዝብ ፍላጎት እንዲከበር፣ በወንድማማችነት አብሮ ለመኖር እንዲቻል ጥሪ ያቀረቡትን የአገሪቷን ጳጳሳት ልባዊ ልመና እና ጥሪ እኔም እቀላቀላለሁ” ብለዋል።

እናም “ለተወዳጅ የሄይቲ ህዝብ” ያላቸውን ቅርበት በመግለጽ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ “ሁከትና ብጥብጥ እንዲቆም እና አገሪቱ የሰላም እና የስምምነት ጉዞ እንድትጀምር” ጥሪ አቅርበዋል።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ በማያሚ ከሚገኘው የሆስፒታል አልጋ ላይ ሆነው መልእክታቸውን ያስተላለፉት የሄይቲ ፕሬዚዳንት ማርቲን ሞይስ ባለቤት ባስተላለፉት መልእክት ባለፈው ሰኔ 30/2013 ዓ.ም ረቡዕ ምሽት በፖርት ኦ ፕሪንስ የመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከባለቤታቸው ጋር በታጣቂዎች በጥይት ተመተው የተረፉት የፕሬዚዳንቱ ባለበት ሀገሪቱ መንገዷን እንዳትስት ማሳሰባቸው ተገልጿል።

ቀዳማዊት እመቤት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንደ ነበሩ የጥበቃ ሰራተኞችን አልፎ ቤታቸው ውስጥ በመግባት በቅጥረኞች ነፍሰ ገዳዮች በጥይት ተመተው የነበረ ሲሆን ባለቤታቸው የነበሩ የሄይቲ ፕሬዚዳንት አሥራ ሁለት ጊዜ በጥይት ተመትተው አንድም ቃል ለመናገር እንኳ ጊዜ ሳያገኙ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተገልጿል።

ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው የፕሬዚዳንቱ ባሌበት በሕይወት ተርፈው በአውሮፕላን ወደ አሜሪካ መወሰዳቸው የተገለጸ ሲሆን በማያሚ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላት ይገኛል። በሆስፒታል ውስጥ ሆነው ባስተላለፉት ልዩ መልእክት “አገሪቱ መንገዷን እንድትስት መፍቀድ የለብንም፣ የፕሬዚዳንቱ ደም በከንቱ ፈሶ አይቀርም” ብለዋል።

እስሮች እና እየተካሄደ ያለው ምርመራ

እስካሁን ድረስ አስራ ሰባት የቀድሞ የኮሎምቢያ ወታደሮች እና ሁለት የአሜሪካ ሄይቲያውያን በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ሶስት ሰዎች በጥይት ተገድለዋል። ስምንት የሚሆኑ ፕሬዚዳንቱን ገለዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች አሁንም እየተፈለጉ መሆኑ ተዘግቧል። መርማሪዎች የሄይቲን የፖለቲካ ስርዓት ለመጣል ያተኮረ ከዚህ እብሪተኛ ጥቃት በስተጀርባ ማን እንደነበረ ለማጣራት እየሞከሩ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሄይቲ ባለሥልጣናት ወደ ቀውስ የገባውን ተለዋዋጭ የፖሌቲካ ሁኔታ ለማረጋጋት የሰላም አስከባሪ ወታደሮች እንዲልኩ ለተባበሩት መንግስታት እና ለአሜሪካ ጥሪ አቅርበዋል። የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪዎች ቀደም ሲል እ.አ.አ ከ 2004 እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ በሄይቲ የሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር። ጥሪውን ተከትሎ አሜሪካ ወታደሮቼን አልክም፣ ነገር ግን የኤፍቢአይ እና የሀገር ውስጥ ደህንነት አባላትን ለመላክ ግን ፈቃደኝነቷን ማሳየቷ ተገልጿል።

ከብዙ ጊዜ በፊት ጀምሮ እስከ ዛሬው እለት ድረስ የዘለቀ የሄይቲ የኃይል የተደገፈ የፖለቲካ ታሪክ በግድያ እና በፖለቲካ ውዥንብር መልክ እንደገና እየተከሰተ መሆኑ ምልክቶች እንደ ሚያሳዩ ሁኔታውን የሚከታተሉ ሰዎች ገልጸዋል።

12 July 2021, 10:11