ፈልግ

የሄይቲ ፕሬዚደንት የነበሩ ክቡር አቶ ጆቬኔል ሞይሴ የሄይቲ ፕሬዚደንት የነበሩ ክቡር አቶ ጆቬኔል ሞይሴ 

የሄይቲ ፕሬዚደንት ግድያ አገሪቱን በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የከተታት መሆኑ ተገለጸ

የሄይቲው ፕሬዚደንት ጆቬኔል ሞይሴ ግድያን ተከትሎ አገሪቱ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ መሆኗን በሄይቲ የፊዴይ ዶኑም ማኅበር አባል ማዳሌና ቦስኬቲ ገልጸዋል። የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጆሴፍ በበኩላቸው ፕሬዚደንቱን የተገደሉት ባዕዳን ታጣቂዎች ሳይሆኑ አይቀርም በማለት ገምተዋል። በሄይቲ የፎርት ሊቤርቴ ከተማ ጳጳስ በበኩላቸው በአገሪቱ ውስጥ የሕዝቡ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አንችልም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሄይቲን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመሩ የተሾሙት አሪያል ሄንሪ ለዜጎቻቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ፕሬዚደንት ጆቬኔል ሞይሴን የገደሉት ስፓኒሽ ቋንቋ የሚናገሩ የውጭ አገር ታጣቂዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ታጣቂዎቹ ሰኔ 29/2013 ዓ. ም ከሰዓት በኋላ ወደ ፕሬዚደንቱ መኖሪያ ቤት ገብተው ጥቃት መፈጸማቸው ታውቋል። በጥቃቱ በጽኑ ቆስለው ወደ ሆስፒታክ የተወሰዱት የፕሬዚደንቱ ባለቤትም መሞታቸው ታውቋል። የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ጆሴፍ ድርጊቱን አውግዘው ጥቃቱ “የጥላቻ ፣ ኢሰብአዊና አረመኔያዊ ድርጊት” በማለት ገልጸውታል። ከግድያው በኋላ የአገሪቱ ጸጥታ ምክር ቤት ካካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በኋላ ባወጣው መግለጫ ፖሊስ እና የታጠቁ ኃይሎች ሥራቸውን እየሰሩ ስለሆነ ህዝቡ እንዲረጋጋ በማለት ጥሪ አቅርቧል።

በዓለማችን ውስጥ እጅግ ድሃ ከሚባሉ አገራት መካከል የምትመደብ፣ እ. አ. አ በ2010 ዓ. ም በደረሰባት የመሬት መንቅጥቀጥ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ሰዎች የሞቱባት፣ በሦስት መቶ ሺህ ዜጎቿ ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ የደረሰባ ሄይቲን ድህነት የጎዳት እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሣሪያ የታጠቁ አሸባሪዎች የተስፋፉባት አገር መሆኗት ታውቋል። እ. ኤ. አ በ 2017 ዓ. ም. ስልጣን ላይ የተቀመጡት ጆቬኔል ሞይሰ እ. ኤ. አ. ከጥር ወር 2020 ዓ. ም. ጀምሮ አገሪቱት ያለ ፓርላማ ምርጫ በአዋጅ ብቻ ሲያስተዳድሩ መቆየታቸው ታውቋል። አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ በመጭው መስከረም 16/2014 ዓ. ም. ዜጎች በሕገ-መንግስታቸው ላይ የሚያደርጉትን ሕዝበ ውሳኔን፣ ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫን እንዲመሩ ክቡር አቶ አሪያል ሄንሪ መሰየማቸው ታውቋል። በአገሪቱ ሊካሄድ የታቀደው ሕዝበ ውሳኔ እና ምርጫ በኮቪድ-19 ወረርሽ ምክንያት ሁለቴ ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

ምላሾቹ

በሄይቲ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች መዘጋታቸው፣ የውጭ አገራት ዲፕሎማቶችም ለደህንነት ሲሉ ሠራተኞቻቸው ማስጠንቀቃቸው ታውቋል። አሜሪካም በበኩሏ ጥቃቱ “አሰቃቂ” ነው በማለት አውግዛ የሄይቲን ሕዝብ እና መንግሥት ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን ገላጻለች። ስፔንም በበኩሏ ጥቃቱን ማውገዟ ሲታወቅ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ፔድሮ ሳንቼዝ የፖለቲካ ኃይሎች በመተባበር መፍትሄን እንዲያገኙ አሳስበዋል። የዶሚኒካን ሪፓብሊክ በበኩሉ ከሄይቲ ጋር የሚያገናኝ ድንበሯን መዝጋቷ ታውቋል።

"ስልጣን በጦር መሣሪያ ታጣቂዎች እጅ ነው"

በሄይቲ ለሃያ ዓመታት ያህል የኖሩት የፊዴይ ዶኑም ማኅበር አባል የሆኑት ማዳሌና ቦስኬቲ በአገሪቱ የተከሰተው የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ እንዳልሆነ ገልጸው፣ አገሪቱ እየተመራች ያለችው በፖለቲካ ኃይሎች ሳይሆን በጦር መሣሪያ ታጣቂዎች መሆኑን አስረድተው በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ በአገሪቱ ምን እንደሚከሰት በውል ለማወቅ ያዳግታል ብለዋል። 

“ወደዚህ ደረጃ እንደርሳለን ብለን በጭራሽ አላሰብንም”

በሄይቲ የፎርት ሊቤርቴ ከተማ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ አልፎንስ ኬስኔል ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በታጣቂዎች የተገደሉት እና የአገሪቱ ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ጆቬኔል ሞይሴ በቅርቡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሰየማቸውን አስታውሰው ቢሆንም ወደ ሥራ ሳይሰማሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ከቅርብ ቀናት ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ የጦር መሣሪያ ታጣቂዎች ቁጥር መበራከቱን እና ውጥረት መኖሩን አስረድተዋል። ባሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ መረጋጋት የሚታይ ቢሆንም እየሆነ ላለው ነገር የሕዝቡ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አዳጋች ነው ብለዋል። 

08 July 2021, 16:32