ፈልግ

በትግራይ ክልል በስደተኛ ጣቢያ የሚገኙ ስደተኞች በትግራይ ክልል በስደተኛ ጣቢያ የሚገኙ ስደተኞች  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ የጉልበት ብዝበዛ ሰለባ ለሆኑ ሕጻናት እና ለኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ጸሎት አቀረቡ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰኔ 06/2013 ዓ.ም በእለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ እንደ ተለመደው እና ዘወት እሁድ እለት እንደ ሚያደርጉት ለዓለም ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት በኢትዮጲያ በሚገኘው የትግራይ ክልል በተፈጠረው ቀወስ ሰለባ ለሆኑ ሰዎች፣ የሜድትራንያን ባህርን አቋርጠው በሚሻገሩበት ወቅት ህይወታቸውን አደጋ ላይ ለሚጥሉ ሁሉ እንዲሁም የጉልበት ብዝበዛ ሰለባ ለሆኑ ሕጻናት ጸሎት ማደረጋቸው ተገለጸ።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እሁድ ሰኔ 06/2013 ዓ.ም የመልአክ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረጉ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ  በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምእመናን ባስተላለፉት መልእክት ሀሳባቸውን የጸጥታ ችግር ወደ ሚታይበት የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በማደረግ  ክልሉ በጣም ድሃውን ለርሃብ ሊያጋልጥ በሚችል ከባድ የሰብዓዊ ቀውስ ይገኛል ብለዋል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል. . .

 “ውድ ወንድሞች እና እህቶች! በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የትግራይ ክልል ህዝብ ጋር በጣም ቅርብ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ፣ እጅግ በጣም ድሃ የሆነውን ህዝብ ለርሃብ ሊያጋልጥ በሚችል ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ተመቷል። ዛሬ ረሃብ አለ፣ እዚያ ረሃብ አለ። ጥቃቱ ወዲያውኑ እንዲቆም ፣ የምግብ እና የህክምና ርዳታ ለሁሉም ተደራሽ መሆኑ እንዲረጋገጥ እና ማህበራዊ መግባባት በተቻለ ፍጥነት እንዲፈጠር አብረን እንጸልይ። በዚህ ረገድ የህዝቡን ስቃይ ለማቃለል የሚሰሩትን ሁሉ አመሰግናለሁ። ለእነዚህ ዓላማዎች ወደ እመቤታችን እንጸልይ” ካሉ በኋላ ከሕዝቡ ጋር “ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ” (ሰላም ለኪ ማርያም) የሚለውን ጸሎት ደግመዋል።

የጉልበት ብዝበዛ ሰለባ ስለሆኑ ሕጻናት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠል ቅዳሜ ሰኔ 05/2013 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን የሚቃወም ቀን ተከብሮ ማለፉን የገለጹ ሲሆን የመጫወት ፣ የማጥናት እና የማለም መብታቸውን የተነፈጉ ሕፃናት ላይ የሚፈጸመውን የጉልበት ብዝበዛ እያየን ዓይናችንን በመጨፈን ዝም ማለት በፍጹም አንችልም ብለዋል። በአለም አቀፉ የሰራተኛ ድርጅት ግምቶች መሠረት ዛሬ ከ 150 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ልጆች ለህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ሰለባዎች እንደ ሆኑ እንደ ሚያሳይ የገለጹት ቅዱስነታቸው ይህ አሳዛኝ ክስተት ነው! "150 ሚሊዮን እስፔንን ጨምሮ ይብዛም ይነስም ከፈረንሳይ እና ከጣሊያን የሕዝብ ቁጥር ጋር አንድ ነው" ሲሉም አክለዋለው ገልጸዋል። ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሳቱ “እኛ ይህንን የዘመናችን ባርነት ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ሁሉንም በአንድ ላይ እናድስ” ብለዋል።

የስደተኞች ችግር

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በመቀጠል በሜድትራንያን ባህር ላይ ለሚከሰቱት በርካታ አደጋዎች መጸለያችንን መቀጠል ይኖርብናል ያሉ ሲሆን እ.አ.አ. የካቲት 18/2015 ዓ.ም ይጓዙበት የነበረው ጀልባ ተሰባብሮ በመስጠሙ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ሰዎችን ለመዘከር በማሰብ የዚህ ጀልባ ስባሪ በሰኔ 06/2013 ዓ.ም ላይ ከሰዓት በኋላ በኦገስታ ሲሲሊ ውስጥ በክብር የሚቀመጥበት ሥነ-ስርዓት እንደሚከናወን ጠቁመዋል። “ይህ የሜድትራንያን ባህር የብዙ አደጋዎች ምልክት የሁሉንም ህሊና መፈታተኑን እንዳይቀጥል እና ግድየለሽነትን የሚያፈርስ የሰው ልጅ እድገትን ይበልጥ የሚደግፍ እና የሚያጠናክር ሊሆን ይገባዋል” ብለዋል። የሜድትራንያን ባሕር በአውሮፓ ውስጥ ትልቁ የመቃብር ስፍራ እየሆነ መምጣቱ ልያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የዓለም የደም ለጋሾች ቀን

ሳምንታዊ መልእክታቸውን ሲያጠናቅቁ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንደ ተናገሩት  ሰኞ ሰኔ 07/2013 ዓ.ም የዓለም የደም ለጋሾች ቀን መሆኑን አመልክተዋል። ርዕሰ-ሊቃነ ጳጳሱ "በጎ ፈቃደኞችን ከልብ አመሰግናለሁ እናም ለጋስ እና ለጋሽነት እሴቶች በማጠናከር እየመሰከሩ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አበረታታችዏለሁ" ብለዋል።

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከእዚህ በታች ያለውን የማጫወቻ ቁልፍ ይጫኑ!
13 June 2021, 13:53