ፈልግ

በፍሊፒንስ የሚገኙ ሕጻናት ልጆች በወርቅ የማውጣት የጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚያስይ ምስል በፍሊፒንስ የሚገኙ ሕጻናት ልጆች በወርቅ የማውጣት የጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚያስይ ምስል  

የተባበሩት መንግስታት-የሕፃናት የጉልበት ብዝበዛ ለማስቆም በሚደረገው ትግል ዓለም እየተሸነፈ ነው ተባለ!

በዓለም ዙሪያ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በቁጥር ወደ 160 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመግለጫው የጠቀሰ ሲሆን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን አክሎ ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ለሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡ ሕጻንት ቁጥር ወደ 160 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፉት 4 ዓመታት ውስጥ ብቻ 8.4 ሚሊዮን ሕፃናት ለአስገዳጅ የጉልበት ብዝበዛ መጋለጣቸውን አክሎ የገለጸው ድርጅቱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጽዕኖዎች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሕጻናት ወደ አስገዳጅ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ የመግባት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል።

አለማቀፍ የሰራተኞች ድርጅት (ILO) እና የተባበሩት መንግስታት የህፃናት ፈንድ ዩኒሴፍ የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ አስመልክቶ ቅዳሜ ሰኔ 05/2013 ዓ.ም የዓለም ፀረ-ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት ሲሆን “የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ-ዓለም አቀፋዊ ግምቶች እ.ኤ.አ. 2020 ዓ.ም አዝማሚያዎች እና የወደፊት ስጋቶች መንገዶች” በሚል ርዕስ ባቀረቡት አዲስ ዘገባ የህጻናትን ጉልበት ብዝበዛ ለማስቆም የተጀመረው ሥራ ግቡን ሳይመታ በመቅረቱ የተነሳ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አስገራሚ በሆነ መልኩ ቀድም ሲል እያሽቆለቆለ የነበረው አሃዝ በመቀልበስ ከፍተኛ የሆነ የቁጥር መጨመር ማሳየቱን እና እ.አ.አ በ 2000 እና በ 2016 ዓ.ም ባሉት አመታት መካከል በ 94 ሚሊዮን ሕጻናት ለአስገዳጅ የጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸው ተገልጿል።

የዓለም የሥራ ድርግት "የማንቂያ ደውል"

“አዲሱ ግምት የማንቂያ ደውል ነው። የአዲሱ ትውልድ ልጆች ለአደጋ ተጋላጭ ሲሆኑ እኛ ዝም ብለን ልንመለከት አንችልም ”ሲሉ የዓለም የሥራ ድርጅ ዳይሬክተር ጄኔራል ጋይ ራይደር ተናግረዋል። ሁሉንም ያካተተ ማህበራዊ ጥበቃ ቤተሰቦች ኢኮኖሚያዊ ችግር ቢገጥማቸውም ልጆቻቸውን በትምህርት ቤት እንዲያቆዩ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። በገጠር ልማት ላይ ያለው ኢንቬስትሜንት መጨመር እና በግብርና ላይ ጨዋ የሆነ ሥራ አስፈላጊ ነው ብለዋል። “እኛ ወሳኝ ጊዜ ላይ ነን እናም ዛሬ በምንወስነው እና በምንሰጠው ማላሽ ላይ የተመረኮዘ ውጤት ነው የሚጠብቀን። በአሁኑ ወቅት በታደሰ ቁርጠኝነት እና ጉልበት የምናደርገው ውሳኔ ሁኔታዎችን ሊቀይር እና የድህነትን እና የህፃናትን የጉልበት ብዝበዛ አዙሪት ይሰብራል ”ብለዋል።

ዩኒሴፍ “ወደ መንገዱ ለመመለስ ጊዜው አሁን ነው”

የዩኒሴፍ ሥራ አስፈፃሚ ሄንሪታ ፎር እንዲሁ ዓለም “የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስቆም በሚደረገው ትግል ውስጥ አቋሟን እያጣች ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ቅዳሜው ሰኔ 05/2013 ዓ.ም የሚከበረው ዓለም አቀፍ የፀረ-የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ቀን ይሆን ዘንድ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ላይ የዓለም የሕጻናት መርጃ ፈንድ የሥራ አስፈጻሚ የሆኑ ሄንሪታ ፎር ባስተላለፉት መልእክት እንደ ገለጹት "ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ በፊት እንኳን በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያውን ጭማሪ ተመልክተናል - እ.ኤ.አ. ከ 2016 ዓ.ም ጀምሮ 8.4 ሚሊዮን ተጨማሪ ሕፃናት ያለ እድሜያቸው የጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል" ብለዋል።

በትምህርት ቤቶች መዘጋት ፣ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቤት ውስጥ የመቆየት ግዴታ በተጣለበት ወቅት፣ የሥራ ማጣት ፣ የኑሮ ሁኔታ እና የማኅበራዊ ደህንነት እና የኢኮኖኒ እጦት ቤተሰቦች በጣም ተስፋ በመቁረጥ ወደ “የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የመጨረሻ አማራጭ” እንዲሄዱ አድርጎዋቸዋል ብለዋል።  “አሁን ለሁለተኛ ጊዜ በቤት ውስጥ የመቀመጥ ግዴታ በተጣለበት ወቅት፣ የትምህርት ቤቶች መዘጋት ፣ የኢኮኖሚ መዛባት እና የብሔራዊ በጀቶች መቀነስ” የዓለም የሕጻናት መርጃ ፈንድ የሥራ አስፈጻሚ የሆኑ ሄንሪታ ፎር እንዳሉት “ቤተሰቦች ልብ የሚሰብሩ ምርጫዎችን ለማድረግ ይገደዳሉ” ብለዋል።

የዓለም የሕጻናት መርጃ ፈንድ የሥራ አስፈጻሚ የሆኑ ሄንሪታ ፎር “ይህንን መቀበል የለብንም” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን አክለውም “ወደ መንገዱ ለመመለስ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል። አገራት የገቢ ድጋፍ እርምጃዎችን ለማስፋት “ልጆች ወደነበሩበት ትምህርት ቤት እንዲመለሱ” ጥሪ አቅርበዋል። “መንግስታት እና አለም አቀፍ የልማት ባንኮች ህጻናትን ከጉልበት ሥራ አውጥተው ወደ ት / ቤት እንዲመለሱ በሚያደርጋቸው መርሃ ግብሮች እንዲሁም ቤተሰቦች በመጀመሪያ ይህንን ምርጫ እንዳያደርጉ በሚረዷቸው ማህበራዊ ጥበቃ መርሃግብሮች ላይ በሚያደርጉ ኢንቬስትሜት ላይ ቅድሚያ እንዲሰጡ እንጠይቃለን” ሲሉ ፎር አክለው ገልጸዋል።

የኮቪድ -19 ግትር ያለ እድገት

የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) እና የዓለም የሕጻናት መርጃ ፈንድ (UNICEF) በጋራ ያወጡት ሪፖርት እንደ እንዳመለከተው እ.ኤ.አ ከ 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደ እስያ፣ ፓስፊክ፣ ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን ያሉ አንዳንድ አቅጣጫዎች ባሉበት ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተንሰራፋ የመጣው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛን ለመቀነስ እየተደረገ የሚገኘው ጥረት ለውጥ እንዳይመጣ እያደረገ ነው የሚል ሪፖርት ይፋ አድርገዋል። ሆኖም በተመሳሳይ መልኩ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት የህዝብ ብዛት መጨመር ፣ በተደጋጋሚ ቀውሶች ፣ ከፍተኛ ድህነት እና በቂ የማህበራዊ ጥበቃ እርምጃዎች ባለመከናወናቸው የተነሳ ላለፉት አራት ዓመታት ተጨማሪ 16.6 ሚሊዮን ህፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ መዳረጋቸው ተገልጿል።

ሪፖርቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ 9 ሚሊዮን ተጨማሪ ሕፃናት በወረርሽኙ ምክንያት በ 2022 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ወደ ሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ የመግባት አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል። ወሳኝ የማኅበራዊ ጥበቃ ሽፋን የማያገኙ ከሆነ የግምት አሃዞች እንደ ሚያሳዩት ከሆነ ይህ ቁጥር ወደ 46 ሚሊዮን ከፍ ሊል እንደ ሚችል ይገመታል።

በኮርቪ -19 የተፈጠረው ተጨማሪ የኢኮኖሚ መደናገጦች እና የትምህርት ቤቶች መዘጋት ቀደም ሲል በልጆች የጉልበት ሥራ ላይ ያሉ ሕፃናት ረዘም ላለ ሰዓት መሥራት ወይም በከፋ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ ሊያስገድዳቸው ይችላሉ ፣ ብዙዎች ደግሞ በተጎጂዎች መካከል ሥራ በማጣት እና ገቢ በማጣት ወደ አስከፊ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዓይነቶች ሊገቡ ይችላሉ በማለት ሪፖርቱ ገልጿል።

በሁሉም ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ ሴቶች ልጆች አንጻር ሲታይ በልጆች የጉልበት ሥራ ውስጥ የተሳተፉ ወንድ ልጆች ቁጥር ከፍ ያለ ነው። ከሁሉም ወንድ ልጆች አንጻር ሲታይ 11.2 ከመቶ የሚሆኑት ወንድ ልጆች በሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ ተጠቂ የሆኑ ሲሆን ይህ አሃዝ ከሁሉም ሴቶች ልጆች ጋር ሲነፃፀር በጉልበት ብዝበዛ ላይ የተሰማሩ ሴቶች 7.8 በመቶ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ በጾታ አንጻር ሲነጻጸር የጉልበት ሥራ ውስጥ ያሉ ወንዶች ልጆች በ 34 ሚሊዮን ሴቶችን ይበልጣሉ። ሕፃናት በጉልበት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ሲባል በየሳምንቱ ለ 21 ሰዓታት ወይም ከዚያ በላይ በቤት ውስጥ ወይም በሌላ የሥራ መስክ ላይ ሕጻናት ተሳትፈው ሲገኙ ነው፣ የእድሜ ክልሉ ደግሞ ከ 5 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ባሉ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ለአስገዳጅ የሕጻናት የጉልበት ሥራ ሲደረጉ እንደ ሆነ ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።

በገጠር አካባቢዎች የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በጣም የተለመደ ነው። ከ 37.3 ሚሊዮን የከተማ ሕፃናት ጋር ሲነፃፀር በገጠርማ አከባቢዎች በሕፃናት ጉልበት ሥራ ውስጥ የተሳተፉ 122.7 ሚሊዮን የገጠር ልጆች አሉ። በገጠር አካባቢዎች የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ (13.9 በመቶ) ሲሆን በከተማ ከሚገኘው (4.7 በመቶ) አሃዝ ጋር ሲነጻጸር በከተሞች ከሚገኘውን አሃዝ በሦስት እጥፍ ይበልጣል።

በሴቶች እና በወንድ ሕጻናት ልጆች ላይ የሚፈጸመው የሕጻናት የጉልበት ብዝበዛ በግብርና ሥራዎች ላይ መከሰቱን ቀጥሏል። በሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ውስጥ ከነበሩት ሕፃናት ሁሉ ከ 70 በመቶ በላይ ፣ በአጠቃላይ 112 ሚሊዮን ሕፃናት በግብርና ሥራ ላይ ይገኛሉ።

ዋነኛው እና ትልቁ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ድርሻ የሚወስደው እና የሚከሰተው በቤተሰብ ውስጥ ነው። ከሁሉም የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ 72 ከመቶው እና ከ 83 ከመቶ ድርሻ የሚወስደው ደግሞ ከ5 አመት እስከ 11 አመት የእድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሕጻናት ጉልበታቸውን የሚበዘበዙት በቤተሰብ ውስጥ በተለይም በቤተሰብ የእርሻ ማሳዎች ወይም በቤተሰብ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ውስጥ ይከሰታል።

የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ በተደጋጋሚ ሕጻናቱ ከትምህርት ቤት ውጭ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል። የግዴታ ትምህርት የዕድሜ ክልል ውስጥ ቢወድቅም በልጆች የጉልበት ሥራ ውስጥ እንዲሳተፉ በመደረጋቸው የተነሳ ከትምህርት ገበታቸው እየተገለሉ ይገኛሉ።  

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከእዚህ በታች ያለውን የማጫወቻ ቁልፍ ይጫኑ!
11 June 2021, 15:31