ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ ሌሎችን እንከባከብ፣ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች እንጸልይላቸ አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በታኅሳስ 25/2013 ዓ.ም በቫቲካን በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ ካደረጉ በኋላ እና የእግዚአብሔር መልአክ ማርያምን ያበሰረበትን የብስራተ ከብሬል ጸሎት ከደገሙ በኋላ ባስተላለፉት ሳምንታዊ መልእክት ሌሎችን እንከባከብ፣ በስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ያማያስቡ ሰዎችን ስመለከት ሐዘን ይሰማኛል ማለታቸው ተገልጿል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ውስጥ ምእመናን ሌሎች ሰዎችን በተሻለ ሁኔታ እንዲንከባከቡ በድጋሚ ጥሪ ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን በታመሙ ሰዎች ላይ እና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ የተገደዱ ሰዎች እየደረሰባቸው የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ፣ ጭቆና እና ብዝበዛዎች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሐሳባቸው እና ጸሎታቸው ከእነርሱ ጋር እንደ ሆነ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል።

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እራሳችንን ሌሎችን ለመንከባከብ ይቻለን ዘንድ “ ከአስማታዊ አስተሳሰብ ራሳችንን ማራቅ ይኖርብናል” በማለት የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ 2021 ዓ.ም አዲስ አመት በተጀመረበት ወቅት ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልእክት መናገራቸው ይታወሳል። በወቅቱ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለው ነበር . . .

ነገሮች በጣም የተሻሉ እንደሚሆኑ እናውቃለን ፣ በእግዚአብሔር እርዳታ በጣም አቅመ ደካማ እና በጣም በተጎዱ ሰዎች ላይ በማተኮር ለጋራ ጥቅም በጋራ እንሰራለን። እኛ 2021 ዓ.ም ምን እንደሚጠብቀን አናውቅም፣ ነገር ግን እያንዳንዳችን እና ሁላችንም በአንድ ላይ ማድረግ የምንችለው እርስ በርሳችን መዋደድ እና የጋራ ቤታችን የሆነውን ምድራችንን እና ተፈጥሮን  ለመንከባከብ ትንሽ ተጨማሪ ጊዜ መስጠት ነው ፡፡

ስለበዓላት ብቻ ለሚያስቡ ሰዎች ሐዝናለሁ

አንድ አደጋ አለ በማለት መልእክታቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳቱ ይህም “የራስን ጥቅም ብቻ ለመንከባከብ ፣ ጦርነት ማካሄድ ለመቀጠል ፈተና - ለምሳሌ - በኢኮኖሚው መገለጫ ላይ ብቻ ለማተኮር ፣ በአጋጣሚ ለመጠቀም መፈለግ፣ ማለትም የራስን ደስታ ለማርካት ብቻ መሞከር” የዘመናችን አስከፊ ገጽታ እንደ ሆነ አክለው ገልጸዋል። ይህንን ብተመለከተ ሲናገሩ ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል . . .

በጋዜጣዎቹ ውስጥ አንድ ነገር አንብቤያለሁ - በአንድ ሀገር ውስጥ የትኛው እንደሆነ አላስታውስም፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በቤት ውስጥ የመቆየት አስገዳጅ ሕግ ለማምለጥ እና ጥሩ የሆነ የእረፍት ጊዜ ለማሳለፍ በማሰብ በአንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ብቻ ከ 40 በላይ በሚሆኑ አውሮፕላኖች ተጭነው ከአገር የወጡ ሰዎች እንዳሉ አንብቢያለሁኝ። ነገር ግን እነዚያ ሰዎች ፣ ጥሩ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፣ በቤት ውስጥ ተቆልፈው ለሚገኙ ሰዎች፣ ለሚሰቃዩ ሰዎች ምንም አለማሰባቸው ያሳዝናል፣ ከቤት ባለመውጣታቸው ቢቻ ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለተጋለጡ ሰዎች አላሰቡም። በቃ የራሳቸውን እረፍት ብቻ በማሰብ የራሳቸውን ደስታ ብቻ ለማጣጣም ይጥራሉ። ይህ በጣም የሚያሳምም ጉዳይ ነው።

ዓመቱን በመከራ ውስጥ ሆነው ለሚጀምሩ ሰዎች ቅርብ እንሁን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ መልእክታቸውን ሲቀጥሉ አዲሱን የጎርጎሮሳዊያኑን ዓመት በታላቅ ችግሮች ውስጥ ሆነው ለሚጀምሩት - ህመምተኞች ፣ ሥራ አጦች ፣ በጭቆና ወይም በብዝበዛ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጸሎት ያደረጉ ሲሆን በመጨረሻም ለቤተሰቦች ሰላምታ አቅርበው “በተለይም ትናንሽ ልጆች ባሉበት ወይም ለመውለድ በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ ሰዎች” ሁልጊዜም በተስፋ እንዲጓዙ ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተው መሰናበታቸው ተገልጿል።

03 January 2021, 12:27