ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ባደረጉበት ወቅት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ባደረጉበት ወቅት  

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ እግዚአብሔር ከነድካማችን ይወደናል፣ የልባችንን በር እንክፈትለት አሉ!

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ዘወትር እሁድ እለት ከቫቲካን ሆነው በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው አስተንትኖ እንደሚያደርጉ የሚታወቅ ሲሆን በእዚህ መሰረት ቅዱስነታቸው በታኅሳስ 25/2013 ዓ.ም ያደረጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ በእለቱ ከዮሐንስ ወንጌል ተወስዶ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ መሰረቱን ያደረገ ሲሆን እግዚአብሔር ከነድካማችን ይወደናል፣ የልባችንን በር እንክፈትለት ማለታቸው ተገልጿል። በእለቱ ቅዱስነታቸው ያደረጉት አስተንትኖ በሚከተለው የቅዱስ ወንጌል ቃል ላይ መሰረቱን ያደረገ ነበር፣ ቃሉም እንዲህ ይላል.. .

“በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሮአል፤ ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ ምንም የለም። ሕይወት በእርሱ ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማውም አላሸነፈውም።

ከእግዚአብሔር የተላከ ዮሐንስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ። ሰዎች ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ፣ ስለ ብርሃን ምስክር ሆኖ ለመቆም መጣ፤ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱ ራሱ ብርሃን አልነበረም። ለሰው ሁሉ ብርሃን ሰጪ የሆነው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም እየመጣ ነበር።

እርሱ በዓለም ውስጥ ነበረ፤ ዓለም የተፈጠረው በእርሱ ቢሆንም እንኳ፣ ዓለም አላወቀውም። ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፤ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጆች የመሆን መብት ጣቸው። እነዚህም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ፣ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።

ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን።

ዮሐንስም፣ “ ‘ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ በፊት ስለ ነበረ ከእኔ ይልቃል’ ብዬ የመሰከርሁለት እርሱ ነው” በማለት ጮኾ ስለ እርሱ መሰከረ። ከእርሱ ሙላት ሁላችንም በጸጋ ላይ ጸጋ ተቀብለናል፤ ሕግ በሙሴ በኩል ተሰጥቶ ነበር፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል መጣ። ከቶውንም እግዚአብሔርን ያየ ማንም የለም፤ ነገር ግን በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው አምላክ እርሱ ገለጠው” (ዮሐንስ 1፡1-18).

ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደ ሚከተለው አሰናድተነዋል ተከታተሉን።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከተከበረበት የገና በዓል በኋላ ባለው በእዚህ ሁለተኛው ሳምንት እለተ ሰንበት ላይ የተነበበው የእግዚአብሄር ቃል የኢየሱስን ሕይወት አንድ ክፍል የምያቀርብልን ሳይሆን፣ ነገር ግን ከመወለዱ በፊት ስለ ነበረው ሁኔታ ይናገራል። ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት ስለ ኢየሱስ አንድ ነገር ለመግለጥ ወደ ኋላ ይመልሰናል። እርሱ ከሁሉም በላይ ይህን የሚያደርገው በዮሐንስ ወንጌል መግቢያ ላይ ነው፣ እሱም “በመጀመሪያ ቃል ነበረ” (ዮሐ 1፡1) በማለት ይጀምራል። “በመጀመርያ” የሚለው በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰው የመነሻ የመጀርያ ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመርያ ቃል ነው፣ እሱም በተመሳሳይ መልኩ በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀስ ሲሆን ይህም የፍጥረት አፈጣጠር  ታሪክ  የሚጀምርበት “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ 1፡1) የሚለው ቃል ነው። የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እንደ ሚነግረን በገና በዓል ወቅት ያሰላሰልንበት ሕጻኑ ኢየሱስ ከዚህ በፊት እንደ ነበረ፣ ነገሮች ከመፈጠራቸው በፊት ፣ ከአጽናፈ ሰማይ በፊት ኢየሱስ እንደ ነበረ ይተርክልናል።  እሱ ከቦታ እና ከጊዜ በፊት ነበረ። ሕይወት ከመታየቱ በፊት “በእርሱ ሕይወት ነበረች” (ዮሐ. 1፡4)።

ቅዱስ ዮሐንስ “ቃል” በማለት ይጠራዋል። በዚህ ምን ሊነግረን ይፈልጋል? ቃላት ለመግባባት ያገለግላሉ - መቼም ብቻችንን አንነጋገርም፣ ከአንድ ሰው ጋር ነው የምንነጋገረው። አሁን ኢየሱስ ከመጀመሪያው አንስቶ ቃል በመሆኑ የተነሳ ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መገናኘት ይፈልግ ነበር ማለት ነው፣ ይህ ማለት ደግሞ ከእኛ ጋር ሊነጋገር ይፈልጋል ማለት ነው። የአብ አንድያ ልጅ (ዮሐንስ 1፡14) የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን ውበት ልነግረን ይፈልጋል ፤ እሱ “እውነተኛው ብርሃን” ነው (ዮሐንስ 1፡9) እናም ከክፉው ጨለማ ሊለየን ይፈልጋል። ህይወታችንን ያውቃል እናም ሁል ጊዜም እንደወደደን ሊነግረን የሚፈልገው “ሕይወት” ነው (ዮሐንስ 1፡ 4)። የዛሬው አስደናቂ መልእክት ይኸውላችሁ - ኢየሱስ ዘላለማዊ የእግዚአብሔር ቃል ነው ፣ እርሱ ዘወትር ስለእኛ የሚያስብ እና ከእኛ ጋር ለመግባባት የሚፈልግ አምላክ ነው።

ይህን ለማድረግ ከቃላት ባሻገር ይሄዳል። በእውነቱ በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ማዕከል ውስጥ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ” (ዮሐንስ 1፡14) በማለት ይናገራል። ሥጋ ሆነ ፤ ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን “ሥጋ” የሚለውን ቃል ለምን ይጠቀማል? የምያምር ቃላት ተጠቅሞ “ሰው ሆነ” ማለት ሲችል ለምንድነው “ሥጋ” የሚለውን ቃል የተጠቀመው? የለም ፣ ሥጋ የሚለውን ቃል የተጠቀመው በደካማነቱ እና ለጥቃት ተጋላጭነትን በመላበስ የእኛን ሰብዓዊ ሁኔታ የሚያመለክት ስለሆነ ነው። ድክመቶቻችንን በቅርበት ለመንካት እግዚአብሔር እራሱን ደካማ አድርጎ እንዳቀረበ ይነግረናል። ስለዚህ ጌታ ሥጋ ከለበሰበት እለት አንስቶ  በሕይወታችን ውስጥ ለእርሱ እንግዳ የሆነ ምንም ነገር የለም። እሱ የሚንቀው ነገር የለም ፣ ሁሉንም ነገር ከእሱ ጋር መካፈል እንችላለን። ውድ ወንድሞቼ፣ ውድ እህቶቼ እግዚአብሄር እዛው ባላችሁበት ሁኔታ፣ በድከመቶቻችሁ ውስጥ፣ እፍረት በሚሰማችሁ ነገሮች ውስጥ እንኳን ሳይቀር እንደሚወዳችሁ ለመናገር ቃል ሥጋ ለብሶ መጣ።

ሥጋ ለበሰ፣ ወደ ኋላ አልተመለሰም። እሱ የእኛን ሰብአዊነት እንደ ምንለብሰው እና ስንፈልግ እንደ ምናወልቀው ልብስ አድርጎ አልወሰደም። የለም በፍጹም እንዲህ አላደረገም፣ ራሱን ከሥጋችን አላገለለም። እናም በጭራሽ ከእሱ አይለይም፣ አሁን እና ለዘላለም እርሱ ከሰው ሥጋ አካል ጋር በሰማይ ይኖራል። እርሱ ለዘላለም ከሰብአዊነታችን ጋር ተቀላቅሏል፣ ተጋብቷል ማለት እንችላለን። በእውነቱ ቅዱስ ወንጌል በመካከላችን ሊኖር እንደመጣ ይናገራል። ሊጎበኘን የመጣው ከእኛ ጋር ሊኖር ፣ ከእኛ ጋር ሊቀመጥ አይደለም።፡ ታዲያ ከእኛ ምን ይፈልጋል? ከእርሱ ጋር የበለጠ ቅርበት እንዲኖረን ይፈልጋል። ደስታን እና ሀዘንን ፣ ምኞቶችን እና ፍርሃቶችን ፣ ተስፋዎችን እና ሀዘኖችን ፣ ሰዎችን እና ሁኔታዎችን ከእርሱ ጋር እንድንካፈል ይፈልጋል። እናድርገው ፣ ልባችንን እንክፈት ፣ ሁሉንም ነገር እንንገረው። የእግዚአብሔርን ርህራሄ ለመቅመስ በትውልዱ ትእይንት ፊት በዝምታ ቆም እንበል ፣ እራሱን ቅርብ አደረገ ፣ ሥጋ ለብሶ ሰው ሆነ። እናም ያለ ፍርሃት ወደ እኛ ፣ ወደ ቤታችን ፣ ወደ ቤተሰባችን ፣ ወደ ድክመቶቻችን እንጋብዘው። ይመጣል፣ ሕይወትን ይለወጣል።

ቃሉ ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነበት የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ከእኛ ጋር ለመኖር የልባችንን በር ለሚያንኳኳው ለኢየሱስ ልባችንን እንድንከፍተለት እና እንድንቀበለው ትረዳን ዘንድ አማላጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል።

03 January 2021, 14:02